ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ አስር – ክፍል ሰባት

ጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር ላይ ደርሷል። ይህ ምእራፍ በእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ካገኙ የአጨዋወት አቀራረቦች አንዱ የሆነው ካቴናቺዮን ከስር መሠረቱ ጀምሮ ያለፈባቸውን መንገዶች ይመለከታል። የዛሬው መሰናዶም ካለፈው ሳምንት የቀጠለ ነው።


             

በ1960ዎቹ አጋማሽ ወደ ኢንተር ከመምጣቱ በፊት በመሐል-አጥቂነት ሚናው ይታወቅ የነበረው ጂያንሺንቶ ፋኬቲ የግራ መስመር ተከላካይ ተደርጎ እንዳሻው ወደ ፊት እየሄደ እንዲያጠቃና የተጋጣሚ ቡድን የመስመር አጥቂዎችን ባሉበት እንዲያፍን ወይም በራሳቸው የሜዳ ክልል እንዲቀሩ እንዲያስገደድ ኃላፊነት ተጣለበት፡፡ ጃየር በቀኝ መስመር ከተከላካዩ በርኚች ፊትለፊት ይሰለፍ ጀመር፡፡ በእርግጥ እርሱ ቀድሞም ቢሆን የስፍራው ምርጥ ተጫዋች አልነበረም፡፡ ነገርግን በጥብቅ ክትትል ወይም ውልፍት በማያስብል ቁጥጥር ውስጥ ሆኖ የሚሻውን እንቅስቃሴ ማድረግ ስለማይችል ከፊትለፊቱ ሰፊ ክፍተት እንዲያገኝ ወደኋላ አፈግፍጎ መጫወት ተጠበቀበት፡፡

በሄሬራው ኢንተር የግራ መስመርም ተመሳሳይ የማጥቃት ዝንባሌ የሚያሳይ ተጫዋች ነበር፡፡ ከፋኬቲ ፊት እጅግ ፈጣን ወይም የቡድኑ የማጥቃት መዘውር ባይሆንም አስደማሚ የፈጠራ ክህሎት የታደለው ኮሮሶ ይሰለፋል፡፡ ተጫዋቹ በተጋጣሚ ቡድን ባላጋራዎች ጥብቅ አደረጃጀት የተዘጋን የተከላካይ ክፍል የማስከፈት ብቃቱ ያስገርም ነበር፡፡ እርሱ የቡድኑን የኋላና የአማካይ ክፍል ከፊት መስመር ተሰላፊዎች ጋር የማገናኘት ተልዕኮ ነበረው፡፡ ካርሎ ታኚን ከዚያም ፍራንኮ በዲን ከተከላካይ ክፍሉ ፊት በመሆን ቡድኑን በመምራትና በመከላከል ላይ ያተኩራሉ፡፡ ከእነርሱ አጠገብ ሰፊ ዕይታ እንዲሁም ልኬታቸውን የጠበቁና ያልተዛነፉ ረዣዥም ቅብብሎችን በመከወን የሚታወቀው ሱአሬዝ ከአጥቂዎቹ ጀርባ በመገኘት የጨዋታውን ግለት ይቆጣጠራል፡፡ ይህ እንግዲህ በጊዜው ኢንተር ልክ የኳስ ቁጥጥሩን በወሰደበት ቅጽበት የሚተገብረው አይነተኛ አጨዋወት ነበር፡፡ ያኔ  ኢንተሮች ሁለት አይነት የተለመዱ የሜዳ ላይ እቅዶች ነበሯቸው፡፡ አንደኛው ኳሷን ይዞ ከፊት ለፊቱ በሚያገኘው ሰፊ ክፍተት አፈትልኮ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለሚገሰግሰው ጃየር ማቀበል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኳሷን ለሱአሬዝ መተው ነበር፡፡ ይህ የአጥቂ አማካይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የመቀባበያ መስመሮችን አልያም አማራጮችን በማጤን የሚያክለው አልነበረም፡፡ እርሱ ኳሷ እግሩ ሥር ስትገባ በጥልቅ ወደኋላ ካፈገፈገ የአማካይ ስፍራ ሆኖ እንከን አልባ በሆነ የማቀበል ችሎታው ለሳንድሮ ማዞላ ይልክለታል፡፡ ካልሆነ ደግሞ ለቡድኑ የመሃል አጥቂ ቤኒያኒሞ ዲ-ጂያኮሞ ወይም ኦውሬሊዮ ሚላኒ ያሻግርላቸዋል፡፡ በእርግጥ ሁለቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች በተፈጥሮ ክህሎት የታደሉ ባይሆኑም  ስል ነበሩ፡፡ ይህም ካልተሳካ ሱአሬዝ ከቀኝ መስመር እየተነሳ በሜዳው ቁመት ወደ መሃል እየገባ (Cut-Inside) የማጥቃት ሒደቱን ለሚያግዘው ጃየር ጥሩ ኳሶች ይመግበዋል፡፡” በማለት ማራዴይ የያኔውን የኢንተር ተጫዋቾች ሚና በዝርዝር ያብራራል፡፡

ፋኬቲ የክለቡ ቁልፍ ተጫዋች ነበር፡፡ በወቅቱ የሄሬራ ቡድን ለሚቀርቡበት የአጨዋወት አሉታዊ ክሶችና ተቃውሞዎች ማርገቢያው የእርሱ ምርጥ ብቃት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ” እኔ የካቴናቺዮ አጨዋወት ሥልትን አግኝቻለሁ፤ ችግር የተፈጠረው ሌሎች ቡድኖች ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ የእኔን ቡድን ለመምሰል አልያም እንደ’ኔ ቡድን ለመጫወት ሲጥሩ ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች በእኔ ቡድን አማካኝነት የሚተገብረው ካቴናቺዮ ውስጥ ያለውን የማጥቃት መርህ ማካተት አልሞከሩም፡፡ አዎ- እኔ በጠራጊ-ተከላካይነት (Sweeper) ሚና ፒቺ ነበረኝ፡፡ ነገርግን ቀደም ሲል በዓለም እግርኳስ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የመሃል አጥቂዎችን ያህል ግቦች የሚፈበርክ ፋኬቲን የመሰለ የመስመር ተከላካይ (Full-Back) የነበረውም በእኔ ቡድን ነው፡፡” ይላል ሄሬራ፡፡ በእርግጥ የአሰልጣኙ አስተያየት እውነታው የጎላ ቢሆንም መጠነኛ ግነት ይስተዋልበታል፡፡ ፋኬቲ በሊጉ ባለ-ሁለት አሃዝ ግቦች ያስቆጠረው በአንድ የውድድር ዘመን ብቻ ቢሆንም በግራ መስመር ላይ ያሳይ የነበረው አስገራሚ ብቃት እና ፈጣን እንቅስቃሴ ሄሬራ ከሊቤሮ በተጨማሪ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን እግር-በ-እግር የሚከታተሉ አራት ተከላካዮቾችን (Defensive Markers) እንደሚጠቀም በመናገር ለሚተቹት ሰዎች ግራ አጋቢ ምስል ፈጥሮባቸዋል፡፡

በ1963፣ 1965 እና 1966 ኢንተሮች የሴሪአውን ዋንጫ አሸነፉ፡፡ የ1964ቱም ያመለጣቸው ከቦሎኛ ጋር ባደረጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከተሸነፉ በኋላ ነበር፡፡ በ1964 እና 1965 የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮናን በበላይነት አጠናቀው ትልቅ ድል ተቀዳጁ፡፡ በ1967ም የፍጻሜ ተፋላሚ ለመሆን በቁ፡፡ በዚህም ሳቢያ የሄሌኒዮ ሄሬራ የአጨዋወት ሲስተም ውጤታማነት አጠያያቂ የመሆኑ ጉዳይ እያከተመ ሄደ፡፡  ሻንክሌይ ሄሬራን እና የሚከተለውን ካቴናቺዮ  የመጥላቱ ምስጢር ከውጤት ጋር ብቻ የተያያዘ  አልያም ዓለም ካወቀው ጥብቅ የመከላከል አጨዋወት (Perceived Defensiveness) አልነበረም፡፡ ችግሩ ከጨዋታው ዘይቤ ጀርባ የሚነሳ ድብቅ ሴራ መኖሩ ነበር፡፡

ሄሬራ በባርሴሎና ሳለም በጭፍን አሉባልታዎች ሲቸገር ሰንብቷል፤ በአሰልጣኙ ተንኳሽ ባህርይ ቅር የተሰኙ ጋዜጠኞች ” መድሃኒት ቀማሚው ባለዋንጫ” ሲሉ ያንጓጥጡት ነበር፡፡ የወቅቱ ተጫዋቾች ግን እነዚህን በማስረጃ ያልተደገፉ ክሶች አስተባብለዋል፤ የሚከተለውን ምስክርነትም ሰጥተዋል፡፡ ” ሄሬራ በስራው ቆራጥ  የነበረ ቢሆንም ጨዋታ አዋቂም ነው፡፡ የተጫዋቾቹን ምርጡንና ከፍተኛውን ብቃት እንዴት ማውጣት እንዳለበት ያውቃል፡፡ አበረታች መድሃኒቶች እንደሚሰጠን የሚነገሩበት ወሬዎች ተራ እንቶፈንቶዎች ናቸው፡፡ እርሱ በጣም ጎበዝ የሥነ ልቦና ባለሙያ ነበር፡፡” ይላል በሄሬራ ዘመን ከባርሴሎና የወጣቶች ማዕከል የተገኘው ስፔናዊው አማካይ ፉስቴ፡፡ 

ሄሬራ ተጫዋቾቹ ኃይልና ጉልበት ያገኙ ዘንድ የተከለከሉ አበረታች መድሃኒቶችን እንዲወስዱ ያስገድድ እንደነበረ የሚናፈሱበትን ሐሜቶች በቀላሉ ሊገላገላቸው አልቻለም፡፡ የሳንድሮ ማዞላ ታናሽ ወንድም ፌሩሲዮ ማዞላ በጻፈው ግለ ታሪክ ላይ የቀረበው ከሁሉ የከፋው ነበር፡፡ ፌሩሲዮ ያን ያህልም የተጋነነ የእግርኳስ ተጫዋችነት ክህሎት አልነበረውም፡፡” ሄሬራ ተጫዋቾችን በምን መልኩ ይይዝ እንደነበር በአይኔ በብረቱ አይቻለሁ፡፡ ሄሌኒዮ ሄሬራ ራሱ ምላሳችን ላይ የምናስቀምጠው አበረታች ክኒን ያቀርብልን ነበር፡፡ ለዋናው ቡድን ተጫዋቾች ከመስጠቱ በፊት እኛ ተጠባባቂዎቹ ላይ የመድሃኒቱን አዋጭነት በተግባር ለማረጋገጥ ሞክሯል፡፡ አንዳንዶቻችን ክኒኖቹን ቀስ ብለን እንተፋቸዋለን፡፡ እንዲያውም ወንድሜ ነው መድሃኒቱን የመውሰድ ፍላጎት ከሌለኝ ወዲያው ወደ መጸዳጃ ቤት ሄጄ እንድተፋው የመከረኝ፡፡ ውሎ ሲያድር ሄሬራ ክኒኖቹን እየዋጥናቸው እንዳልሆነ ሲረዳ በቡና ቀላቅሎ ይሰጠን ጀመር፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የሄሬራ ቡና (ll Caffe Herrera) በኢንተር እየተለመደ መጣና መደበኛ ሆነ፡፡” ይላል ፌሩሲዮ ማዞላ፡፡ ሳንድሮ ግን እነዚህን ሃሜቶች በሃይለኛው ይቃወማቸዋል፤ በተለይ በወንድሙ አማካኝነት በተሰራጩት አሉባልታዎች ተማሮ ቤተሰባዊ ግንኙነቱን እስከመገደብ ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ ወሬዎቹ መስፋፋታቸውን አላቆሙም፡፡ እውነት ባይሆኑ እንኳ የአሉባልታዎቹ በፍጥነት መዛመት የክለቡን ምሥል አጉድፏል፡፡ ወሬዎቹ ሰፊ አመኔታ ማግኘት መቻላቸው ደግሞ   ሄሬራ ስኬትን ፍለጋ ምን ያህል ርቀት ሊጓዝ እንደሚችል በሰዎች ዘንድ ስለሰፈነው አስተሳሰብ ማሳያ ሆኗል፡፡

በሄሬራው ኢንተር ታክቲክ፣ ሥነ-ልቦና፣ የቡድን እምነት ወይም ባህል ተዋህደዋል፡፡ አሰልጣኙ የእርሱ ቡድን ታክቲካዊ አቀራረብ ሙሉ በሙሉ መከላከል ላይ ያመዘነ እንዳልሆነ የሚከራከረው ምናልባት አሳማኝ ምክንያት ኖሮት ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የቡድኑ አጠቃላይ አዕምሯዊ አቋም ላይ አሉታዊ ገጽታ እንዳረበበ ሊደበቅ አይችልም፡፡ <ዘ-ኢታሊያን ጆብ> በተሰኘው መጽሃፋቸው ላይ ጂያን ሉካ ቪያሊና ጋብሬሌ ማርኮቲ የጣልያንን እግርኳስ ስለወረረው ባላንጣን የመጠራጠር ይዘት በሰፊው አትተዋል፡፡ በሄሬራው ኢንተር ሁሉም ተጋጣሚ ቡድን የጠላት ያህል እንዲታይ መደረጉ ተስተውሏል፡፡ ይህ አይነቱን እሳቤ የመቀበል ፈቃደኝነት ማሳየቱ ደግሞ እንደ ቻፕማን ያሉትን አሰልጣኞች የሚያስጨንቅ ይሆናል እንጂ ለሑጎ ሜይዝል መሰሎቹ ሐሳባውያን ግድ የሚሰጣቸው አይመስልም፡፡ ጂያኒ ብሬራ ከሌሎች ምልከታ አፈንግጦ አዘወትሮ ጣልያኖች መከላከል ላይ የተመሰረተ እግርኳስ (Defensive Football) መጫወት እንዳለባቸው ይሞግታል፡፡ ለዚህም የሃገሪቱ ተጫዋቾች በተፈጥሮ ካላቸው ደካማ አካላዊ ጥንካሬ አንጻር በአካል ብቃቱ ረገድ እጅግ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው መሆናቸውን በመንስኤነት ይጠቅሳል፡፡

በጣልያን እግርኳስ አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት ተገቢ ባልሆኑ እና የጨዋታ ህግጋቱ በማይፈቅዱ ዘዴዎች የመጠቀም ልማድ (Gamesmanship) እየተለመደ ሄደ፡፡ ከ1967ቱ የኢንተርና ሴልቲክ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ የፍጻሜ ፍልሚያ በፊት ሄሬራ በግል ጀት ወደ ግላስኮው አቅንቶ የሴልቲክና ሬንጀርስን ግጥሚያ በአይብሮክስ ለመታደም ችሏል፡፡ ሄሬራ ከጣልያን ወደ ስኮትላንድ ከመብረሩ አስቀድሞ ከአይብሮክሱ ጨዋታ በኋላ ጆክ ስቴይንን ይዞ በመመለስ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ኢንተር ከጁቬንቱስ የሚያደርገውን የጣልያን ደርቢ እንዲመለከት ለስቴይን ግብዣ አቅርቦለት ነበር፡፡ ብልሁ ስቴይን ግን ይህን ግብዣ ተማምኖ ቀደም ብሎ ያዘዘውን ቲኬት ለማሰረዝ አልቸኮለም፡፡ ሄሬራ ግላስኮው ሲደርስ አውሮፕላኗ ለስቴይን ግዝፈት እጅግ በጣም አነስተኛ እንደሆነች በማሳወቅ ሰበብ ፈጥሮ ቃሉን አጠፈ፡፡ የስቴይን ጥንቁቅነት እዚህ ጋር ዋጋ ኖረው፡፡ ኢንተሮች ታክሲና የስታዲየም መግቢያ ቲኬቶችን ለጆክ ስቴይን ለማድረስ የገቡትን ቃልም ማሳካት አልሆነላቸውም፡፡ በመጨረሻም ስኮትላንዳዊው የወቅቱ የሴልቲክ አሰልጣኝ የጣልያን ደርቢን ለማየት የስታዲየም መግቢያ በር ላይ ያለውን ጥበቃ የሚያሳምን ሰው አስፈልጎት አንድ ጋዜጠኛ የመግቢያ ካርዱን ተጠቅሞ ሊያስገባው ችሏል፡፡

እነዚህ እንዲያው ለመጥቀስ ያህል የሚነሱ አብነቶች ይሁኑ እንጂ ኢንተሮች ለተጫዋቾቻቸው አበረታች እንክብሎችን ከማቅረብ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ክሶች ሲቀርቡባቸው እና የጨዋታ ውጤት በማጭበርበር ቅሌት ስማቸው ሲብጠለጠል ሄሬራ ልቡን አደንድኖ በግትርነቱ ጸንቷል፡፡  በጭካኔው ዘልቋል፡፡ አሰልጣኙ ከኤሲ-ሚላን ከመጫወታቸው አስቀድሞ ማምሻው ላይ የጉዋሪን አባት ሞተው እንኳ ለተጫዋቹ መርዶውን ለመንገር የጨዋታውን መጠናቀቅ ጠብቋል፡፡ በ1969 ኢንተርን ለቆ የሮማ አሰልጣኝ ከሆነ በኋላ  የመዲናዋ ክለብ የፊት መስመር ተሰላፊ ጁዪላኖ ታኮላ በአርጀንቲናዊው አሰልጣኝ የተጫዋቾች አያያዝ አማካኝነት ለህልፈት ተዳርጓል፡፡ ተጫዋቹ ለጥቂት ጊዜያት ታሞ ከከረመ በኋላ በጉሮሮው የግራና ቀኝ የእንጥል እጢዎች ላይ የቀዶ ጥገና አድርጎ ምንም የጤና መሻሻል ሳያሳይ ህይወቱ አልፋለች፡፡ ከአጥቂው ሞት በኋላ በተካሄዱ ተጨማሪ ምርመራዎች ጁዪላኖ በልብ ድካም መያዙን አረጋግጠዋል፡፡ ሄሬራ በሴሪ-ኤው ውድድር ቶኮላን ለመጨረሻ ጊዜ የመሰለፍ እድል የሰጠው በሳምዶሪያው ጨዋታ ቢሆንም ከአርባ አምስት ደቂቃዎች በላይ ሜዳ ላይ ሊያቆየው አልወደደም፤ ከዕረፍት መልስ ቀይሮ አስወጣው፡፡ ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ አሰልጣኙ ኢንተር ከካግሊያሪ ጋር ከሜዳው ውጪ ለሚያካሂደው ጨዋታ ከቡድኑ አባላት ጋር ጂዪላኖን ይዞ ወደ ሳርዲኒያ አቀና፡፡ ሄሬራ አጥቂውን የመጠቀም ምንም አይነት ዕቅድ አልነበረውም፡፡ ይሁን እንጂ ጨዋታው በሚከወንበት ዕለት ገና በማለዳው ከባድ ውርጭና ሃይለኛ ንፋስ ባለበት ባህር ዳርቻ ላይ ቶኮላ ከቡድን አባላቱ ጋር ጠንካራ ልምምድ እንዲሰራ አደረገ፡፡ ከዚያም ቶኮላ ጨዋታውን ከተመልካቾች ጋር ተቀምጦ ተከታተለ፤ ጨዋታው ሲጠናቀቅ ወደ መልበሻ ክፍል አመራ፡፡ ተጫዋቾቹ ጋር ከደረሰ ጥቂት ሰዓታት በኋላ ተዝለፍልፎ ወደቀ-ዳግም አልተነሳም፤ በዚያው እስከወዲያኛው አሸለበ፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡