ቢኒያም አየለ የት ይገኛል ?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዕይታ የራቁ ተጫዋቾች በምናቀርብበት የ “የት ይገኛሉ?” ዓምዳችን ከቢኒያም አየለ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ለድሬዳዋ ከተማ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ሐረር ቢራ ፣ መብራት ኃይል እና ወልዋሎ የተጫወተው ይህ አጥቂ በእግር ኳስ ሕይወቱ የመጀመርያ ዓመታት የተሳካ ግዜያት አሳልፎ የግል ሽልማቶችንም አሳክቷል። በተለይም ድሬዳዋ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ በግሉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን አዳማ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግም በተመሳሳይ ከአንድ ተጫዋች ጋር በጋራ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ጨርሷል። ከአዳማ ቆይታው በኋላ በ2010 በወልዋሎ አጭር ጊዜ አሳልፎ አምና በከፍተኛ ሊጉ ድሬዳዋ ፖሊስ ቆይታ ማድረግም ችሎ ነበር።

ከሁለት ዓመታት ወዲህ ከእግርኳስ ቤተሰብ ትኩረት ከጠፋው ቢንያም አየለ ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

በዚህ ወቅት ጊዜውን የሚያሳልፍበት ሁኔታ

አሁን እንደሚታወቀው ወቅቱ የኮሮና ስለሆነ ብዙ እንቅስቃሴ አላደርግም። ከቤት ውጭ የማሳልፈው ግዜ በጣም ጥቂት ነው የስፖርት እንቅስቃሴ ለማድረግ ከመውጣት ውጭ ብዙም ከቤት አልርቅም።

ከዋናው ሊግ እግር ኳስ የራቀበት ምክንያት

ያው ምክንያቱ ብዙ ነው። አንዳንድ አለመግባባቶች ነበሩ ፤ ከዛ ውጭ ደግሞ በአንድ ወቅት መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር። ከዛ በኃላ ነው በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ያልተጫወትኩት። ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም ጉዳት እና ቅድም የጠቀስኩት መጠነኛ አለመግባባቶች ናቸው ምክንያቶቹ።

ስለ ፕሪምየር ሊጉ የመጨረሻ ዓመታት

የመጨረሻዎቹ ዓመታት ላይ የተወሰኑ መንገራገጮች ነበሩ። ወደ ወልዋሎ ሄጄ የተሳካ ግዜ አላሳለፍኩም። ያሰብኩት እና የገጠመኝ የተለያየ ነው። በዛ በዛ ምክንያት እንዳሰብኩት የተሳካ ግዜ ማሳለፍ አልቻልኩም። በወቅቱ አሰልጣኙ ጥሩ ነበር። ግን ደግሞ ብዙ የማይመቹ ሁኔታዎች ነበሩ።

ስለ ወቅታዊ ሁኔታው

ሊጉ በኮሮና ከመቋረጡ በፊት በብሄራዊ ሊግ ክለብ አማራ ውሃ ሥራ (አውስኮድ) እየተጫወትኩ ነበር። በክለቡም ጥሩ ቆይታ ነበረኝ።

ወርቃማ የሚለው የእግርኳስ ሕይወቱ ወቅት

ወርቃማ የምለው በ2000 ድሬዳዋ ከተማ ወደ ሊጉ ሲያድግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኜ ያጠናቀቅኩበት እና በ2007 አዳማ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ አስገብተን በመጀመርያው የሊጉ ዓመት ሦስተኛ የወጣንባቸው ጊዜያቶች ናቸው። በሁለቱም ወቅት በግል ጥሩ ነበርኩ።

በመጨረሻ..

መጨረሻ ላይ ፈጣሪ ሁኔታዎች ሰላም አድርጎልን ሁላችንም ወደምንወደው እግርኳስ እንድንመለስ እመኛለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ