“የዘመናችን ከዋክብት ገፅ” – ከመስፍን ታፈሰ ጋር…

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሀገሪቱ ምርጥ አጥቂዎች ተርታ መመደብ የቻለው መስፍን ታፈሰ የዛሬው ‘የዘመናችን ከዋክብት’ ገፅ እንግዳ ነው።

መስፍን ታፈሰ ትውልድ እና ዕድገቱ ሀዋሳ በተለምዶ ቄራ 02 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ብዙዎችን ባፈራው የቄራ ሜዳ በአሰልጣኝ ታምራት ተስፋዬ አማካኝነት ከ15 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ገብቶ ኳስን መጫወት የጀመረ ሲሆን በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ እና በቀድሞዋ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በኃይሏ ዘለቀ ፕሮጀክቶችም አልፏል። በመቀጠል በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ዛማ የእግር ኳስ አካዳሚ ውስጥ በመግባት ረጅም የስልጠና ጊዜን ካሳለፈ በኃላ 2009 ላይ በአሰልጣኝ ብርሀኑ ወርቁ የሀዋሳ ከተማ የ17 ዓመት በታች ቡድንን ተቀላቅሎ የሁለት ዓመታት ቆይታን አድርጓል፡፡ በቆይታው 24 ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለተኛው ዓመት ላይም ኮከብ ተጫዋች እና ግብ አግቢ መሆን ችሏል። ይህን ተከትሎ ወጣቱ አጥቂ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶት ምንም እንኳን ከፓስፖርት ጋር በተያያዘ ቢሰረዝም ኢትዮጵያ ሳማሊያን ከኃላ ተነስታ 4-3 ስትረታ ሦስት ግቦችን ከመረብ አሳርፎ ነበር።

መስፍን ከውድድሩ መልስ በ20 ዓመት በታች ቡድኑ ውስጥ እየተጫወተ ካሳለፈ በኃላ መጋቢት ወር ላይ ወደ ዋናው ቡድን አድጎ በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለሀዋሳ አምስት ግቦችን ከመረብም አሳርፏል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ከ17 እና 20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግን ከማንሳቱ ባለፈ ለኢትዮጵያ ከ17 እና 20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሀገሩን መለያ የለበሰው አጥቂው በነበረው ተከታታይ ስኬት በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ አምና ሚያዝያ ወር ላይ ተጠርቶ በስድስት የነጥብ ጨዋታ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን አንድ ግብ አስቆጥሯል፡፡ በአባቱ አቶ ታፈሰ አማካይነት በልጅነቱ ከሜዳ ሜዳ በተለያዩ አሰልጣኞች ስር በመሰልጠን ዛሬ ላይ በሊጉ እየደመቀ የመጣው መስፍን ታፈሰ አዝናኝ ጥያቄዎች በሚቀርብበት የዘመናችን ከዋክብት ገፅ የዛሬው ዕንግዳችን ነው፡፡

ሊጉ በኮሮና ምክንያት ከተቋረጠ በኃላ ጊዜውን እንዴት እያሳለፍከው ነው ?

“ይህን ጊዜ የማሳልፈው ቤት ውስጥ ነው፡፡ ጠዋት ጠዋት ልምምድ እሰራለሁ። ከዛ በኃላ እተኛለሁ ፊልምም አያለሁ፡፡”

ከኮሮናም በኃላ አሁን ደግሞ ክረምቱ ገባ ፤ ጊዜው መርዘሙ እንደ ስፖርተኛ አልከበደህም ?

“እንደ ተጫዋች በጣም ይከብዳል። ግን ያው ሁሌም ስራችን እስከሆነ ድረስ መቀመጥ የለብንም ፤ መስራት አለብን። ነገ ሊያጋጥመን የሚችለውን ስለምናውቅ ሁሌም መስራት አለብን። ከሰራን ጊዜውም አይታወቀንም፡፡”

ኳስ ተጫዋች ባትሆን ኖሮ አሁን ምን ላይ እናገኝህ ነበር ?

“ተጫዋች ባልሆን ነጋዴ ነበር የምሆነው። ያው ከሰፈሬ የተነሳ የተወለድኩት ገበያ ሰፈር ስለሆነ ወደ ንግዱ ዓለም መግባቴ አይቀርም ነበር፡፡”

በአንድ ቡድን አብሬው ብጫወት ደስ ይለኛል የምትለው ተጨዋች ?

“አዲስ ግደይን እመርጠዋለሁ። ምክንያቱም እሱን እያየሁ ነው ያደግኩት። የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ያስደስቱኛል። ለውወጣት ተጫዋች ያለውም ቦታ ደስ ይላል፡፡”

በፕሪምየር ሊጉ አላሳልፍ ብሎ የፈተነህ ተጫዋች አለ ?

“ጨዋታ ላይ በዕርግጥ የፈተኝ ተጫዋች የለም ፤ ማንም እስከ አሁን አልከበኝም፡፡ ”

ከቤተሰብ ጋር ያለህ ግንኙነት እንዴት ነው ?

“የምኖረው ከቤተሰብ ጋር ነው። እህቶች አሉኝ ፤ ከእነሱ ጋር እየተጫወትኩ ፣ እየተቀላለድን ነው የማሳልፈው። አብዛኛዎቹን ጊዜያት ከቤተሰቤ ጋር አሳልፋለሁ። ከዛ በተረፈ ከጓደኞቼ ጋርም አሳልፋለሁ፡፡ ”

በእግር ኳስ የተጫዋችነት ዘመንህ ያዘንክበት ቀን ?

“ያዘንኩበት ወቅት አለ ፤ ብዙ ናቸው ግን አንደኛው ብሩንዲ ለብሔራዊ ቡድን ተጫውቼ ተቀንሼ ስመጣ በጣም ነው ያዘንኩት ፤ እያለቀስኩም ነበር። ሌሎቹ እየሰሩ እኔ ተቀንሰሀል ተብዬ ስወጣ እንባዬ መጣ። ያው ዕድሜዬም ገና ነበር። በዛን ሰዓት ከእኔ የተሻሉም ነበሩ። ግን ያን ዕለት ተቀንሼ ስመጣ በጣም ነው የተሰማኝ፡፡”

በተቃራኒው ደስተኛ የሆንክበትስ ?

“ደስተኛ የሆንኩት ያው 2011 ባደኩበት ዓመት መቐለ ላይ ግብ ሳስቆጥር። እናም ደግሞ ከ17 እና 20 ዓመት በታች ከሀዋሳ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳሁበት እና የኮካኮላ ውድድርም ላይ ዋንጫ ያነሳሁባቸው ጊዜዎች በጣም የተደሰትኩባቸው ናቸው፡፡”

አመጋገብህ እንዴት ነው ? ምን ዓይነት ምግብ ታዘወትራለህ ?

“እኔ ምግብ አላማርጥም። ግን ….(እየሳቀ)…ያው አቮካዶ በአይብ ብዙን ጊዜ በአቅራቢያችን ስላለ እሱን እበላለሁ ፤ ብዙ ጊዜ እሱን አዘወትራለሁ፡፡

ስለ መስፍን ሰዎች ማወቅ አለባቸው ብለህ ምታስበው የተለየ ባህሪ ?

“ብዙም የለም ፤ ቶሎ እናደዳለሁ እንጂ። እሱ ነው የኔ ባህሪ የክፋት ሳይሆን መሸነፍ ስለማልወድ ውጤት ሲበላሽ ቶሎ ነው የምነናደደው፡፡”

ቅፅል ስም አለህ ?

“አዎ አለኝ “ጩንኬ” ይሉኛል። ይሄን ስም እናቴ ናት ያወጣችልኝ። ጓደኞቼ ደግሞ “ዜጋው” ነው የሚሉኝ። ያው ያወጡልኝ ያለኝን ሰውነት አይተው ነው ዜጋው ያሉኝ፤ ከወጣት ቡድን ያደግኩም አልመስልም፡፡ ”

ከእግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ ሚስጥረኛ ጓደኛ አለህ ?

“ብዙ ሰው ይመክረኛል፤ ግን ያው ለመግለፅ ይቸግረኛል። ጥራ ካልከኝ ግን ፀጋዓብ ዮሐንስ፡፡ ”

ከእግር ኳስ ውጪ ምን ያዝናናሀል ?

“ያው መዋኘት ነዋ። አንደኛ ስፖርት ነው፤ እየዋኘው እየተዝናናሁ ሳሳልፍ ደስ ይለኛል፡፡”

ለመስፍን አርዓያ የሆነው ተጨዋች ማነው ?

“ለእኔ አርዓያዬ አዳነ ግርማ ነው። የሱን ነገር እየሰማሁ ነው ያደግኩት፡፡”

እዚህ ለመድረሴ ላመሰግናቸው እወዳለሁ ምትለላቸው ይኖራሉ ?

“በጣም ብዙ ናቸው። መጀመሪያ ፈጣሪን ነው የማመሰገንው። ቤተሰቤ በተለይም አባቴን፣ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት፣ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ፣ አሰልጣኝ መልካም (ባሪዬ) እና ታምራትን፣ የሰፈር ጓደኞቼ እና እኔን ላሰሩኝ አሰልጣኞች በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ