ሶከር ታክቲክ | ተጭኖ መጫወት እና መልሶ-ማጥቃት

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡

አንድ ቡድን የሚተገብረው ተጭኖ የመጫወት ሥልት (Pressing) ይዘቱ እና አይነቱ ከመልሶ-ማጥቃት (Counter-Attacking) ሒደት ጋር ቀጥተኛ መስተጋብር አለው፡፡ እያንዳንዱ ቡድን ሜዳ ላይ በተግባር ሊያውል የሚያቅደው ተጭኖ የመጫወት ሥርዓት ለቀጣይ የማጥቃት አጨዋወት መንገዱን ያቀልለታል፤ ፈጣን አጋጣሚዎችን ለመጠቀምም ያዘጋጀዋል፡፡ ኳስን ከተጋጣሚ ነጥቆ በራስ ቁጥጥር ሥር የሚደረግበት የሜዳ ክፍል እስከ ተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል ድረስ ያለውን ርቀት እንዲሁም የባላጋራ ተጫዋቾች የመከላከል አደረጃጀታቸውን መልሰው እስኪይዙ ድረስ የሚፈጠር የክፍት ቦታ መጠንን ይወስናል፡፡ በአንድ ቡድን ጠንካራ ጎን እና በባላንጣው ደካማ ጎን ላይ በመመሥረት ልንጠቀማቸው የምንችላቸው የተለያዩ ተጭኖ የመጫወት ዘዴዎች መልሶ-ማጥቃትን እንድንተገብር ያግዙናል፡፡

ወደ ተጋጣሚ ክልል እጅጉን ተጠግቶ የሚከወነው ተጭኖ መጫወት (High-Press)

ይህኛው ተጭኖ የመጫወት ዘይቤ የተጋጣሚ ግብ ክልል ለመድረስ የሚያስችለውን አጭር ርቀት ያስገኝልናል፡፡ ይሁን እንጂ  ከተጋጣሚ ቡድን የመጨረሻው የመከላከል የአግድሞሽ መስመር ጀርባ የሚፈጥረው ክፍተት በጣም የጠበበ ይሆናል፡፡

በእርግጥ ተቃራኒ ቡድንን ወደ ራሱ ክልል በመግፋት በሜዳው የላይኛው ክፍል ተጭኖ መጫወት የዚህኛው “ፕሬሲንግ” ሲስተም መሰረታዊው ሒደት ነው፡፡ ከላይ በመግቢያው እንደተጠቀሰው ተቃራኒ ቡድን ጎል ክልል ጋር ለመድረስ ያጠረው ርቀት የሚገኘውም በዚሁ ስልት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ በዚህ ስልት ከመጨረሻው ተከላካይ ጀርባ ሊገኝ ወይም ሊፈጠር የሚችለው ክፍት ቦታ ሰፊ አይሆንም፡፡

ከታች በቀረበው ምስል እንደሚታየው ሊቨርፑል በሜዳው የላይኛው ከፍል ከተጋጣሚው ኳስ ከነጠቀ በኋላ ጎል ሊያስቆጥር ይችላል፡፡የማንችስተር ሲቲ ተጫዋቾች የሚያደርጉትን የቅብብል ሒደት የሊቨርፑሉ ተጫዋች ባጨናገፈበት በሲቲዎች ጎልና በኳሱ መካከል የተገኙት ተከላካዮች ሁለት ብቻ እንደሆኑ ከቀጣይ እንቅስቃሴው መረዳት ይቻላል፡፡

ከላይ በምስሉ እንደተመለከተው ሊቨርፑሎች የተጋጣሚያቸው ክልል ድረስ በመሄድ የተጋጣሚያቸውን የኳስ ቅብብለሎች ያቋርጣሉ። ስለዚህም በጨዋታ ወቅት በኳስ ቁጥጥር ከፍተኛ ብልጫ የሚኖራቸው ቡድኖች በአብዛኛው ይህን የ”ፕሬሲንግ” ዘዴ ይጠቀማሉ፡፡ በእንደእነዚህ አይነቱ ቡድኖች ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በአብዛኛው በጠባብ ቦታ ላይ የመቀናጀት ብቃት ያላቸው ከመሆናቸው ባሻገር ስኬታማ እንቅስቃሴ ለማድረግም ከተጋጣሚዎቻቸው ተከላካዮች ጀርባ ሰፊ ቦታ ላይሹ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፦ እንደ ማንችስተር ሲቲና ሊቨርፑል ያሉ ቡድኖች አዘወትረው በሜዳው የላይኛው ክፍል “ፕረስ” ያደርጋሉ፡፡ በተጨማሪ ደግሞ በተቻለ ፍጥነት በመልሶ-ማጥቃትም ይጫወታሉ፡፡

ወደ ራስ የግብ ክልል በማፈግፈግ ተጭኖ የመጫወት ሒደት (Low Press)

ወደ ራስ የግብ ክልል በጣሙን ቀርቦ ተቃራኒ ቡድንን “ፕሬስ” ማድረግ ከተጋጣሚ የግብ ክልል ፊት ለፊት ሰፊ ቦታ እና ረጅም ርቀት ይፈጥራል፡፡ በሌላ በኩል ከተቃራኒ ቡድን የመጨረሻ የመከላከያ መስመር ጀርባ በመልሶ ማጥቃት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ሰፋ ያለ ክፍተት  ይሰጣል፡፡

ወደ ተጋጣሚ ክልል እጅጉን ተጠግቶ ከሚከወነው ተጭኖ የመጫወት ሥልት (High-Press) በተጻራሪ ቡድኖች በዚህኛው የ”ፕሬሲንግ” መዋቅር ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በጣሙን ቀርበው ይጫወታሉ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ለመድረስ ረጅም ርቀት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ በአዎንታዊነት ከተጋጣሚ ቡድን የመከላከያ መስመር ጀርባ ሰፊ ክፍተት ያስገኛል፡፡ ይህም ፈጣን አጥቂዎች ለያዙ ቡድኖች አመቺ ይሆንላቸዋል፡፡ ብዙውንጊዜ ወደኋላ እጅጉን አፈግፍጎ መከላከል ዝግ ያለ እንቅስቃሴ በመሆኑ የሚከወነውም በሜዳው የተወሰኑ ዞኖች ብቻ ይሆናል፡፡ “ፕሬስ” ሲያደርጉ በዝቅተኛ አዘጋግ ወደኋላ ይሆናሉ፡፡ በእርግጥ እንደ አትሌቲኮ ማድሪድ መሰሎቹ ቡድኖች በዚህ መንገድ ቢከላከሉም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተጋጣሚዎቻቸውን ” ፕረስ” ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡

ከላይ በምስሉ እንደተመለከተው አትሌቲኮ ማድሪዶች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በጣሙን ቀርበው በመከላከል ከተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች ጀርባ የሚያገኙትን ክፍት ቦታዎች በመልሶ-ማጥቃት ሒደት ይጠቀሙባቸዋል፡፡

ይህን የአጨዋወት ሥልት በውጤታማ መንገድ ለመተግበር እና በመልሶ-ማጥቃት ተጠቃሚ ለመሆን በሜዳው የላይኛው ክፍል የማጥቃት ሒደቱን በከፍተኛ ፍጥነትና ስልነት የሚያግዙ በቂ ተጫዋቾች ያስፈልጋሉ፡፡

መሐለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጭኖ መጫወት (Mid Press)

መሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጭኖ መጫወት ከመጨረሻው ተከላካይ ጀርባ የተወሰነ ክፍት ቦታ እንዲተው ያደርጋል፡፡ እስከ ተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል ድረሰ ያለው ርቀትም ብዙ አይሆንም፡፡

ወደ ተጋጣሚ ክልል እጅጉን ተጠግቶ ሚከወነው ተጭኖ የመጫወት (High-Press) ዘይቤ አኳያ መሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጭኖ መጫወት (Mid Press) ከከተጋጣሚ ቡድን ኋላ መስመር ጀርባ ብዙ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ በሌላ በኩል ይህን የ”ፕሬሲንግ” ዘዴ የሚጠቀም ቡድን ከራሱ የመከላከያ መስመር ጀርባ እንዲተው የሚገደደው  ክፍት ቦታ አነስተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የ”Mis Press” ተግባሪው ቡድን ተከላካዮች ከተቃራኒ ቡድን አጥቂዎች የተሻለ ፍጥነት ከሌላቸው ይህንን ዘዴ መጠቀም አደገኛ ይሆናል፡፡

ከላይ በምስሉ የሊቨርፑል ተጫዋቾች መሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጭኖ በመጫወት ከማንችስተር ሲቲ ተጫዋቾች ኳስ ሲቀሙ ይታያል፡፡ ሊቨርፑል በፕሪሚየር ሊግ ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ  “Mid Press”ን በቁልፍ የታክቲክ ግብነት ተጠቅሟል፡፡ የየርገን ክሎፑ ቡድን ይህን ተጭኖ የመጫወት ዘዴ በመከተሉ በራሱ የሜዳ ክፍል ብቻ እንዲወሰን አልተገደደም፡፡ ይልቁንም  ፈጣኖቹን ሰሥት የሊቨርፑል አጥቂዎች- ሞሐመድ ሳላህ፣ ሰይዱ ማኔ እና ሮቤርቶ ፌርሚኒሆን  በማንችስተር ሲቲ ግማሽ ሜዳ ያለውን ክፍት ቦታ መጠቀም እንዲችሉ አድርጓቸዋል፡፡

” በእርግጥም የርገን ክሎፕ የመልሶ-ማጥቃት አጨዋወት ጠቢብ ነው፡፡ ሊቨርፑሎች በሦስት ወይም አራት ንክኪዎች በመጨረሻው የማጥቃት ክልል ላይ ይደርሳሉ፡፡” ፔፕ ጓርዲዮላ

በዚህ ተጭኖ የመጫወት ስልት ሊቨርፑሎች ለተጋጣሚ ጎል ቀርበው የሲቲን ተጫዋቾች በቁጥር መብለጥ ችለዋል፡፡ ልክ ወደ ራስ የግብ ክልል በማፈግፈግ ተጭኖ መጫወት (Low Press) ሁሉ ይህም ዘዴ በተለይ ኳስ ከተጋጣሚ ከተነጠቀ በኋላ የማጥቃት ሒደቱን ለማቀላጠፍ የሚያስችሉ አማካዮች ይሻል፡፡

ተጋጣሚን መምራት

የተሳካ የ”ፕሬሲንግ” አጨዋወት ለመተግበር  ተቃራኒ ቡድንን ወደ አንደኛው የሜዳ ክፍል እንዲሄድ ማስገደድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የመጫወቻ ሜዳን የመሀል ክፍል (Centre)፣ መስመሮች/ክንፍ (Wings) እንዲሁም (Half-Space) ብለን በንከፋፍል እነዚህ የሜዳው ክልሎች ተጨነን ልንጫወት ከምንችልበት ርዝመት አንጻር የራሳቸው የሆነ አሉታዊና አዎንታዊ ጎን እንዳላቸው እንረዳለን፡፡ ከተጠቀሱት የሜዳ ክፍሎች ውስጥ ተጋጣሚን በመስመሮች ተጭኖ መጫወት የተሻለ ቅለት ይኖረዋል-ምክንያቱም ተጋጣሚ ቡድን የሚኖረው የመቀባበያ አማራጭ መስመሮች ስለሚያንሱ ኘው፡፡ የመሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጋጣሚን መጫን ደግሞ ከበድ ያለ ይሆናል-ለዚህም ተጋጣሚ ቡድን በርካታ የመቀባበያ አማራጭ መስመሮች ማግኘቱ እና ብዙ ክፍተቶችን በቀላሉ መድፈን አለመቻሉ በምክንያትነት ይቀርባል፡፡

አንድ ቡድን ከተጋጣሚ የጎል ክልል አንጻር ያለው ርቀትም እጅግ ወሳኝ የ”ፕሬሲንግ” አጨዋወት ግብዓት ነው፡፡ በመሃል ክፍል ተጭኖ መጫወትን የመረጠ ቡድን ለባላንጣው የጎል ክልል ይበልጡን እየተጠጋ መሄዱ እሙን ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጨዋታ እቅድን ለመቀየር፣  የተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ አደራደርን ላይ መጠነኛ ሽግሽግ ለማድረግ፣ የተጋጣሚን ጥቃት ለመከላከልም ሆነ ለሌሎች በጨዋታ ወቅት ለሚስተዋሉ የተለያዩ ሁነቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አመቺው “ፕሬሲንግ” ይኸው “Mid Press” ይሆናል፡፡
የመልሶ-ማጥቃት አጋጣሚ እና አደጋው

ብዙውን ጊዜ መልሶ-ማጥቃት የሚከወነው በሽግግር ሒደት (Transition Phase) ላይ ስንሆን ነው፡፡ ለሽግግር ጨዋታ ፈጣን አጸፋ፣ ተገቢ የውሳኔ አሰጣጥ፣ በጥልቀት ማሰብ እንዲሁም ከፍተኛ ፍጥነት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ተጫዋቾች ይህን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወስዱ ማበረታታት ጠቃሚ ነው፡፡

“አንዳንዶች ሌስተር ብዙ ኳስ እንደሚያባክን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በብርሃን ፍጥነት ስትጫወት ይህ መከሰቱ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡” የሌስተር አሰልጣኝ የነበሩት ክላውዲዮ ራኒየሪ የተናገሩት

በጨዋታ ወቅት በአንድ ቡድን ውስጥ በቁጥር የሚያመዝኑት ተጫዋቾች በተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል እና በኳሱ መካከል ሲሆኑ በመልሶ-ማጥቃት ጊዜ የሚፈጠረው አደጋ ይቀንሳል፡፡ በአንጻሩ ግብ የማስቆጠር እድል ደግሞ ይጨምራል፡፡ በዚህም ሳቢያ በመልሶ-ማጥቃት ሒደት ለተጫዋቾች “ሪስክ” እንዲወስዱ መፍቀድ ግድ ይላል፡፡


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ