የዳኞች ገፅ | ልባሙ ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በትላልቅ መድረኮች በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት ጭምር በጥሩ የዳኝነት አቅማቸው ጎልተው መውጣት ከቻሉ ዳኞች የሚመደበው ቴዎድሮስ ምትኩ የዛሬው የዳኞች ገፅ ዕንግዳችን ነው።

አዲስ አበባ ጃን ሜዳ አካባቢ የተወለደው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ እግርኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎቱን ከፕሮጀክት እስከ ተስፋ ቡድን ድረስ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ሆኖም የኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ሰብሮ ለመግባት አስቸጋሪ በመሆኑ እግርኳስን አቁሞ በሌላ የሙያ ዘርፍ ወደ ዳኝነቱ በማምራት ከመምሪያ ሁለት አንስቶ በአሁኑ ወቅት በኢንተርናሽናል ዳኝነት ሀገሩን በከፍተኛ ኃላፊነት እያገለገለ ይገኛል።

በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማን ፈለግ በመከተል በተለያዩ የአፍሪካ ውድድሮች በብቃት ዳኝቶ እየተመለሰ ይገኛል። የ2011 የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊጉ ምስጉን ዳኛ በመሆን የተሸለመው ቴዎድሮስ በዚህ አያያዙ ጠንክሮ ከሰራ ወደፊት ኢትዮጵያን በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ላይ የመወከሉ ጉዳይ ዕሩቁ አንደማይሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል። በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን ልባም እና ደፋር እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ዳኛ ከዚህ ቀደም የመነበረውን የዳኝነት ጉዞ እና የወደፊቱ ዕቅዱን አስመልክቶ ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል።

ወደ እግርኳሱ ከባቢ እንዴት ብቅ አልክ ?

በዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ውድድር ላይ በኢትዮጵያ ከ13 ዓመት በታች የታዳጊ ቡድን ውስጥ ነበርኩኝ። ከሁለት ዓመት በኃላ መብራት ኃይል ከ15 ዓመት በታች ቡድን ለመግባት ሙከራ አደረኩኝ ሆኖም ሳይሳካ በመቅረቱ እንደገና ከአንድ ዓመት በኃላ በድጋሚ ከ17 ዓመት በታች የታዳጊ ቡድን ኒያላ ለመግባት ለሁለት ወር የሙከራ ጊዜ አሳልፌ ፣ በደንብ ተዘጋጅቼ ሁሉን ነገር ጨርሼ መፈረም ብቻ ነበር የቀረኝ። ሆኖም የኔ ስም ተሰርዞ የሌላ ሰው ስም በማስታወቂያ ላይ ወጥቶ አየሁኝ። ለምን እንደሆነ በወቅቱ የነበረውን አሰልጣኝ ስጠይቀው “የኮሚቴ ውሳኔ ነው” አለኝ። በጣም እለኸኛ እና ግልፍተኛ ስለነበርኩኝ ‘የምን ኮሚቴ ነው? አንተ እና ምክትሉ አይደላችሁ ለሁለት ወር ያሰለጠናችሁኝ ከእናተ ውጪ ማን ነበር ?’ አሉኩት። ያው የደሀ ልጆች ስለነበርን ገንዘብ የመስጠት አቅም አልነበረንም። በእጃቸው የሄዱት በእኛ ቦታ ሲገቡ እኛ ወጣን በቃ እግርኳስን አልጫወትም ብዬ ወሰንኩ።

ተጫዋች በነበርክበት ጊዜ በምን ቦታ ነበር የምትጫወተው ? በመቀጠል አልጫወትም ብለህ ቀጣይ ውሳኔህ ምን ሆነ ?

“እየሳቀ”… ግብጠባቂ ነበርኩ። ከ13 ዓመት በታች ፕሮጀክት ስጫወት አጥቂ ሆኜ ነበር። በኃላ ግን ወደ ግብጠባቂነት መምጣት ችያለው። ኒያለ እንዲህ ያለ በደል ሲሰራብኝ አልጫወትም ብዬ ቁጭ ባልኩበት ሰዓት አንድ ሰው ለሜታ ቢራ የሠራተኛ ቡድን ለወራት እንድጫወት አድርጎኝ ለተወሰ ጊዜ ተጫውቼ ነበር። ሆኖም ስሜቴ ስለተጎዳ ለመቀጠል ሳልፈልግ ቀርቼ እግርኳስን መጫወት አቆምኩኝ። ከዚህ በኃላ ግን ግራ ገባኝ። ‘ምንድነው የማደርገው ?’ ከእግርኳስ (ከስፖርት) ውጪ ህይወቴን የምመራ መስሎ ስላልታየኝ እግርኳስ ካልተጫወትኩ ዳኛ ልሁን አልኩኝ። እንደ ወንድሜ የማየው ሱልጣን መሐመድ የሚባል ዳኛ ነበር። በኢንተርናሽናል ዳኛ ደረጃ የደረሰ በጣም ምርጥ ረዳት ዳኛ ነው። እርሱ አነሳሳኝ እና ወደ ዳኝነቱ ልገባ ችያለው።

የመጀመርያውን የዳኝነት ኮርስ መቼ ወሰድክ ? የመጀመርያውን ጨዋታህንስ ታስታውሰዋለህ?

በ1997 የመጀመሪያውን መምርያ ሁለት ኮርስ በጃን ሜዳ ወሰድኩኝ ። በወቅቱ የሚገርምህ በቀን አራት ጨዋታ በአስር ብር አበል እያጫወትን ውለን እንወጣ ነበር። የመጀመርያ ጨዋታዬ የጤና ቡድን እየተጫወትኩ አጋጣሚ ሆኖ ዋናው ዳኛው ከተማ (ኮሜዲ) ይባላል አሁን ኮሚሽነር ሆኗል። እንደአጋጣሚ ረዳቶቹ ይቀሩበታል። በዚህ ሰዓት እኔ እና አሸናፊ የሚባል የንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን መሪ ነው። ረዳት ሆነን እንድናጫውት ተደረገ። ለመጀመርያ ጊዜ የሴቶች ጨዋታን ለጤና ቡድን ለመጫወት ለብሼው በመጣሁት መልያና ቁምጣ አጫውቻለው።

እንዲህ ብለህ የጀመርከውን የዳኝነት ሙያን ወደ መምርያ አንድ እንዴት አሻገርከው ?

ያው የዳኝነት ኮርስ የምትወስድባቸው የኮርሶች ሂደቶች አሉ። መምርያ አንድን ከሦስት ዓመት በኃላ 2000 ላይ ወሰድኩኝ። በዚሁ ዓመት ላይ በአዲስ አበባ ደረጃ የመጀመርያውን የምስጉን ዳኝነትን ሽልማት አገኘሁኝ። ከዚህ በመቀጠል በ2003 ፌደራል ዳኛ ሆንኩኝ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከፍተኛ ፈተናዎችን አልፌ ዳኛ የመሆን ሀሳቤን ለማሳካት ጠንክሬ እሰራ ነበር።

በስድስት ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ጨዋታዎችን በማጫወት የፌደራል ዳኝነትን ማዕረግ አግኝተሀል። በእነዚያ ስድስት ዓመታት ውስጥ ያገኘኸውን ልምድ አጫውተኝ።

ብዙ ልምዶችን አግኝቼበታለው። ምን መሰለህ በእኔ ዕምነት አንድ ዳኛ ዳኛ ከመሆኑ በፊት ኳስ መጫወት አለበት እላለው። ምክንያቱም በዳኝነት ያሉትን ሁሉን ነገር ለማወቅ እግርኳስ ተጫውተህ ካለፍክ ማንም ተጫዋች አንተን አያታልልህም። ታቀዋለክ ምን ጋር ምን እንደተፈጠረ። በዚህ መልኩ ተጠቅሜያለው። ሁለተኛ ዳኛ ለመሆን ስትፈልግ የሚያጫውቱ ዳኞችን ቁጭ ብለህ መመልከት አለብህ። እኔ የጃን ሜዳ ልጅ በመሆኔ በቀን ብዙ ጨዋታዎችን የማየት ዕድሉን አግኝቻለው። አካባቢያችን ላይ በዳኝነት ያለፉ ብዙ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ትልልቅ ዳኞች ሜዳ ውስጥ ምን እንደሚሰሩ ማየት ችያለው። ተጫዋች በነበርኩበት ጊዜ ደግሞ በባህሪዬ ለዳኞች አስቸጋሪ ነበርኩ። ይህም የሰጠኝ ጠቀሜታ አለ። እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ በቀን ውስጥ ጠዋት ሁለት ከሰዓት ሁለት ጨዋታ አጫውት ነበር። ይሄ ሁሉ ተደምሮ ለኔ ዳኝነትን በደንብ እንዳውቅ ትልቅ ልምድ ሆኖኛል ማለት እችላለው።

አሁን ትልቅ ዳኛ ለመሆን እየተንደረደርክ ነው። ደረጃ በደረጃ እያለፍክ ፌደራል ዳኛ ሆነሀል። ፌደራል ዳኛ ሆነህ የመጀመርያ ጨዋታህ የት እና ማን ከማን ጋር ነበር ?

አሰላ ከተማ ላይ ነው። የወልዴ ንዳው ረዳት ዳኛ ሆኜ የብሔራዊ ሊግ ጨዋታ መቱ ከኦሮሚያ ፖሊስ ነው ያጫወትኩት። ከዚህ በኃላ ነው ከጨዋታ ጨዋታ ራሴን እያሻሻልኩ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ማደግ የቻልኩት። በፕሪሚየር ሊጉ ደግሞ ኢትዮጵያ መድንን ከአርባምንጭ ከነማ በማጫወት ነው የጀመርኩት።

ከረዳት ዳኝነት ወደ ዋና ዳኛ እንዴት መጣህ ?

መጀመሪያ ዳኛ ሆኜ በአዲስ አበባ ዳኞች ኮሚቴ ውስጥ የቀድሞ ዳኛ የአሁኑ የጨዋታ ኮሚሽነር ይሸበሩ ዕድገቴን ያውቅ ስለነበር ወደ ላይ ስመጣ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አርቢትር ኮሚቴ ውስጥ ነበር። በአንድ ወቅት ጎንደር ላይ የአሰፋ ደቦጭ አራተኛ ዳኛ ሆኜ ከአንድ የጨዋታ ታዛቢ ጋር አልተግባባሁም ነበር። በዚህ ምክንያት የዳኞች ኮሚቴ ጠርተው ያናግሩኛል። ቢሮ ስገባ ጋሽ ይሸበሩ ‘ይሄን በጣም አውቀዋለው ጀግና ዳኛ ነው። እንዳውም ምረጥ ዋና ይሻልሀል ረዳት ?’ ብለው ጠየቁኝ ‘እኔ እናንተ በመረጣችሁት ይሁንልኝ ፣ በዚህ ቦታ ላይ ሁን ካላችሁኝ ባላችሁበት ቦታ ስጡኝ እኔ የመስራት አቅም አለኝ።’ አልኳቸው። ከዛ በኃላ ባልሳሳት በ2004 ዋና ዳኛ ሆኜ በቋሚነት ገባሁ።

በፌዴራል ዳኝነትህ ፈተነኝ የምትለው ጨዋታ የቱ ነበር ?

ወልዲያ (መልካ ቆሌ) ሜዳ ላይ ነው። ብዙ ጊዜ ዳኞች እዛ ሄደው ለማጫወት ይቸግራቸዋል። እኔ ደግሞ የትም ክልል ሄጄ ጨዋታ ሳልመርጥ አጫውቼ እመለሳለው። ወልድያ ላይ ያጋጠመኝ በመጀመርያው አጋማሽ ልጁ በእጁ ጎል ለማግባት ሞክሮ ቢጫ ካርድ ሰጥቼው ነበር። ወልዲያ ደግሞ በዚህ ጨዋታ በሜዳው አንድ ለዜሮ እየተመራ ነው። በሁለተኛው አጋማሽም ያ ልጅ ጥፋት ያጠፋል። ጠርቼው አንተ ልጅ ተጠንቅቀህ ተጫወት ቢጫ ካርድ አለብህ በማለት በምክር አለፍኩት። ሆኖም ተደጋጋሚ ጥፋት እያጠፋ መጨረሻ ላይ ኳስ ከመሬት ጋር ሲያነጥርብኝ በሁለት ቢጫ ከሜዳ አስወጣሁት። ከዚህ በኃላ ሜዳው ውስጥ የነበረው ድባብ ያስጠላ ነበር። ዳኝነቱ አቅቶኝ አልነበረም። ሆኖም የደጋፊዎቹ ሁኔታ በጣም ጥሩ አልነበረም። ለመጀመርያ ጊዜ ነው በተወረወረ ድንጋይ የተመታሁትም። ብዙውን ጊዜ እኛ ሀገር ጨዋታዎቹን ከባድ የሚያደርጉት ሜዳ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ሳይሆን የደጋፊው ድባብ ነው። አንዴ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር እያጫወትኩኝ ሁለት ተጫዋቾችን በኤሌክትሪክ በኩል አስቸግረውኝ በቀይ ካርድ አስወጣኋቸው። ሌሎች ሁለት ተጫዋቾች ደግሞ አስቸገሩኝ። በአንድ ቡድን አራት ተጫዋቾች ከወጡ የጨዋታው ውበት ላጠፋው ነው። ደጋፊው ደግሞ ኳስ ማየት አለበት በሚል እነዛ ሁለት ተጫዋቾች ‘የምትችሉ ከሆነ ጨዋታው ካለቀ በኃላ አናግሩኝ እንጂ እባካቹሁ አትበጥብጡኝ ፤ እናተን በማስወጣት ጨዋታዬን አላበላሽም’ ብዬ በስንት መከራ ያለውን ፈተና ተቋቁሜ ጨዋታውን ጨርሻለው።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ስለሆንክበት አጋጣሚ እናውራ።

በእኔ ዕምነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን ዘግይቻለው ነው የምለው። በእርግጥ ከእኔ በፊት የነበሩ ሰዎች ፈጥንሃል ይሉኛል። እኔ ደግሞ በነበረኝ የዳኝነት ብቃት ዘግይቻለው አላቸዋለው። የሚገርምህ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ሳልወስድ በየዓመቱ ታንዛኒያ እና ቦትስዋና ሁለት ጊዜ በመሄድ የፊፋ ኮርስ ወስጃለው። የ36 ሀገር ዳኞች መሀል የአካል ብቃት ፈተናውን የጨረስነው ሦስት ነበርን። በጥሩ ሁኔታ ኮርሱን ወስጄ ተሸልሜ ነው የመጣሁት። እንዲያውም በአንድ ወቅት የፊፋ ሰዎች ኤሜ ኮርስ ሊሰጡ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት  ‘እንዴት ይሄንን ልጅ የፊፋ ባጅ አልሰጣችሁትም ከአንዴም ሁለቴ የፊፋ ኮርስ ስንሰጠው ሀገሩ እንደገባ በመጀመርያ ቀን የፊፋ ባጅ ይሰጠዋል ብለን ጠብቀን ነበር’ ብለው ተናገሩ። ያው እንዳልሆን ብዙ ደባዎች ነበሩ። ፈጣሪ የፈቀደው ነው የሚሆነው በ2010 ላይ የፊፋ ባጅ ወስጃለው። የዳኝነት ልፋቱ ከመጀመሪያው መምርያ ጀምሮ እስከ ፌደራል ዳኝነቱ ድረስ ስትቆይ የሁሉም ዳኛ የወደፊት ራዕይ ኢንተርናሽል መሆን ነው። ዳኝነትን ስጀምር እዚህ ደረጃ እደርሳለው ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። በመጨረሻ ይህ ተሳክቶልኛል ፈጣሪ ይመስገን።



በጣም ደፋር ልባም ዳኛ ነህ። ይህን ሜዳ ውስጥ ምንም ነገር ሳትፈራ የማጫወት አቅምህን እንዴት አገኘኸው?

የመጀመርያውን የዳኝነት ኮርስ የሰጠኝ ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ ነበር። እርሱ ሁሌ የሚነግረን አባባል አለው። ‘ልብ ከሌላችሁ ባታጫውቱ ይሻላል! ‘ ይል ነበር። ዳኝነት በኛ ሀገር በተለይ ከፍተኛ ፈተና እና ውጣ ውረድ ስላለው መጀመርያ ልባም መሆን ያስፈልጋል ይሉ ነበር። ልባም ካልሆንክ ተስፋ ትቆርጣለህ መጨረሻ ላይ ያሰብክበት አትደርሰም። ከዚህ የተናሳ ዳኝነትን በሙሉ ልባምነት እንዳጫውት የእርሳቸው ምክር ጠቅሞኛል። ከዚህ ውጪ ተጫዋች ሆኜ ስላለፍኩ የደጋፊን ፣ የተጫዋችን ፣ አጠቃላይ የስፖርቱን ማኀበረሰብ ስሥነ-ልቦና ጠንቅቄ ስለማቅ በየጨዋታዎቹ ሳልፈራ የሚሰጠኝን ጨዋታ በብቃት አጫውቼ እወጣለው።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ከሆንክ በኃላ በተደጋጋሚ በአፍሪካ መድረክ ጨዋታዎችን እያጫወትክ ትገኛለህ። የመጀመርያ ጨዋታህና እስካሁን ያገኘህውን ዕድል እንዴት ታየዋለህ ?

የኦሊምፒክ ማጣርያ ከ23 ዓመት በታች ጨዋታ ሲሸልስ ላይ ሲሸልስ ከሱዳን ነው የመጀመርያ ጨዋታዬን ያጫወትኩት። በነገራችን ላይ በጣም ዕድለኛ ነኝ። ካፍም ሆነ ፊፋ አስቀድመው የሚያቁኝ በመሆኑ ብዙም አልቆየሁም ጨዋታ ለማጫወት። አንዳንድ ጊዜ ባጁን አግኝተው ጨዋታዎችን ለማጫወት ብዙ የሚጠብቁ አሉ። እኔ ግን ገና ከወዲሁ ብዙ ጨዋታዎን አጫውቻለው። ውድድሮች በኮሮና ቫይረስ እስከተቋረጡበት ጊዜ ድረስ አራት በዋና ዳኝነት ፣ አስራ አንድ በአራተኛ ዳኝነት በአጠቃላይ ከአስራ አምስት በላይ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ አድርጌአለው። ይህ በሁለት ዓመት ያገኘሁት ኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ ነው። በቀጣይ ጠንክሬ ከሰራሁ ብዙ ርቀት እሄዳለው ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

በቀጣይስ በአሁጉራዊ መድረክ ከአንተ ምን እንጠብቅ ?

በመጀመርያ ኢትዮጵያ በኔ ዘመን ዕድለኛ ነች። ከእኛ በፊት የኢትዮጵያን ስም ከፍ አድርገው ያስጠሩ በህይወት ያሉም በህይወት የሌሉም የቀድሞ ዳኞች አሉ። በዚህ ዘመን በካፍ እና በፊፋ እኛ ኢትዮጵያውያን ዳኞች ተፈላጊ ነን። ይህን ጅማሮዬን አጠናክሬ በዓምላክ እና ሊዲያ የደረሱበት ደረጃ በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ማጫወት ትልቅ ፍላጎት አለኝ። ይህንንም ለማሳካት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሬ እሰራለው።

በአፍሪካም ሆነ በፊፋ ኢትዮጵያውያን ዳኞች በጣም የተመሰገኑ ናቸው ፤ በጨዋታ ማጭበርበር ቅሌት አይጠረጠሩም። ለዚህ ብዙ ነገሮች ማንሳት ይቻላል። አንተ በዚህ ሀሳብ ምን ትላለህ ?

እውነት ነው በዚህ እኔ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል። ዳኛ ለመሆን ስታስብ ዋናው ከጨዋታ ማጭበርበር የፀዳህ መሆን አለብህ። በካፍ እና በፊፋ የተለያዩ ኮርሶችን ወስጃለው። በጣም የሚገርምህ በኮርሱ ላይ በመጀመርያ የሚለቀቅልህ ቪዲዮ አለ። እርሱም አፍሪካ ዳኞች ተብለው ስማቸው በሌብነት የሚጠሩ የተለያዮ ሀገር ዳኞችን ትመለከታለህ። እስቲ አስበው ቁጭ ብለህ ባንዲራህ እየተውለበለበ ሌባ ስትባል ምን ዓይነት ስሜት ነው የሚሰማህ ? በጣም ከባድ ነው። ከእኔ ጋር ኮርስ እየወሰዱ የኬንያ እና የጋና ዳኞች አጠገቤ ቁጭ ብለው የሀገራቸው ስም በሌብነት ሲጠራ ያለቅሳሉ። በዚህ በኩል እኔ ወደ ሀገሬ ስመጣ ባዓላክን እና ሊዲያን ‘በጣም አመሰግናለው’ እላቸዋለው። ‘ሀገሬን በሌብነት አላስጠራችሁም’ እላቸዋለው። ምን ልበልህ ከሥልጠናው በላይ ይህ ነገር በጣም ያስደስተኛል ፤ ኩራት ይሰማኛል።  ኢትዮጵያውያን ዳኞች በየትም ቦታ ስማቸው በመልካም የሚነሳ ቁጥር አንድ ዳኞች ናቸው። በዓምላክም ሊዲያም በጣም የተመሰገኑ ናቸው። እኔም በእነርሱ ደረጃ መሆን ነው የማስበው።

አንተ እስካሁን በዚህ ረገድ ያጋጠመህ ፈተና አለ ?

ምን አለ መሰለህ በዳኝነት ንፁሁ መሆን አለብህ። አይደለም ሀገር ውስጥ ውጪ ስትሄድ ንፁህ ካልሆንክ ዳኝነት ከባድ ነው። አንድ ነገር ልንገር የመጀመርያ ጨዋታ አራተኛ ዳኛ ሆኜ ከለሚ ንጉሴ ጋር ሩዋንዳ ነው የሄድነው። የኛ ጨዋታ ነገ ሊሆን ዛሬ አንድ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ነበር። ስታዲየም ሄደን ኳሱን ለማየት ቁጭ ብለን በካፍ በምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የሆነው ሰሊስቲን የሚባል ሰው ቁጭ ብሎ ከላይ እያየ ነው። እኔ በስም በዝና እንጂ በአካል ሰውዬውን አላውቀውም ነበር። አንድ ወጣት ተመልካች ከተቀመጥኩበት ቦታ ይመጣና ከአጠገቤ ቁጭ ብሎ ‘ከየት ነው የመጣኸው ?’ አለኝ። ‘ከኢትዮጵያ ለነገው ጨዋታ ለማጫወት ነው።’ አልኩት። ከዛ ቀጠለ እና ቀስ ብሎ ‘ገንዘብ (ዶላር) ብሰጥህስ ?’ አለኝ። ‘ለምድነው ገንዘብ የምትሰጠኝ ?’ ስለው ‘አይ ለነገ ጨዋታ’ አለኝ። ‘እንዴ አታውቅም እንዴ ኢትዮጵያዊያን ዳኞች እኮ ሳያልበን ገንዘብ አንወስድም።’ አልኩት። ይሄን ብዬ ለክንዴ ሙሴ የሆነውን ነግሬው ዞር ብዬ ስመለስ ልጁ ከአጠገቤ የለም። ለካ ይሄ ልጅ የካፍ ተወካይ ሰሊስቲን የሚባለው ሰው ነው እኔ ላይ የላከው ፤ እኔን ለመፈተን። አየህ እኔ የመጀመርያ ጨዋታዬ ነው እዚህ ጋር የሆነ ስተት ብሰራ በቃ አከተመ የኔ ዳኝነት ማለት ነው። ስለዚህ እኛ በዳኝነቱ ብቻ ሳይሆን በሌብነቱም የለንበትም። ባዓምላክ እና ሊዲያ እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ዳኝነትን አንድ እርምጃ ብቻ አይደለም ብዙ እርምጃ ነው ወደ ፊት ያሻገሩት። ለእነርሱ ትልቅ ክብር አለኝ ፤ የኢትዮጵያ ዳኝነት ከእነ ኃይለመላዕክ በኃላ ተቋርጦ ነበር። ያንን ድልድይ እንዳይሰበር አድርገው ያስቀጠሉት እነርሱ ናቸው። በተለይ እኔ ብዙ ጨዋታ እየወጣው ያለሁት ከባዓምላክ ጋር ነው። እንርሱ ያስከበሩትን ዳኝነት እኔ መጠበቅ አለብኝ። ከፈጣሪ ጋር ትልቅ ዳኛ ሆናለው ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

በሀገሪቱ ትልቁ ጨዋታ የሆነውን ሸገር ደርቢ እስካሁን አጫውተሀል ?

እስካሁን በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የሸገር ደርቢ ጨዋታን አላጫወትኩም። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በ2009 የፍፃሜ ጨዋታ ግን አጫውቻለው። ሆኖም የአዲስ አበባ ዳኛ በመሆኔ የሸገር ደርቢን በፕሪሚየር ሊጉ አልተሰጠኝም። ሆኖም ዘንድሮ ‘ለምድነው የሸገር ደርቢን የማላጫውተው ? እኔ እኮ ኢንተርናሽናል ዳኛ ነኝ ‘ ብዬ ጠይቄ ነበር። ከኮሮና ምክንያት የዘንድሮ ውድድር ተቋረጠ እንጂ ሁለተኛው ዙር ላይ ሊሰጠኝ ነበር። ያው ወደ ፊት ማጫወቴ አይቀርም።

ኢትዮጵያውያን ዳኞች ከሀገር ውጭ ትልቅ ክብር አግኝተው ይመለሱና በሀገር ውስጥ ግን የሚገባውን ክብር አያገኙም ይባላል በዚህ ላይ ያለህ አስታያየት ምንድነው?

ምን መሰለህ እኔ ይሄንን ምሳሌ የምነግርህ በባዓምላክ ነው። ከባዓምላክ ጋር ለመጀመርያ ጊዜ ለማጫወት የወጣሁት ሴኔጋል ነበር። እዛ ሄደን የሚሆነውን ነገር ስመለከት ባዓምላክ ኢትዮጵያዊ ዳኛ አልመሰል አለኝ። ሜዳ ላይ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ፣ የሚወስናቸው ውሳኔዎች፣ ከቦታ ቦታ የሚሸፍንበት ፣ አቅጣጫ የሚቀይርበት ፣ ቦታ አያያዙ በቃ ምን ልበልህ ፤ ሰው ነው ፍፁም አይደለም ግን ሁሉ ነገሩ የተሟላ ነው። ይገርምሀል እኔ ጨዋታውን መከታተል ትቼ እርሱ የሚያደርገውን ነገር ነበር የምመለከተው። ይሄን ሁሉ ሳይ ነው በዓምላክ ኢትዮጵያዊ ዳኛ አልመሰለኝም ያልኩህ። ውጭ ሀገር አስቁመውት አብረውት ፎቶ ሲነሱ ሳይ በቃ ነብይ በሀገሩ አይከበርም የሚልው አባባል ነው ትዝ የሚለኝ። እኛ ከኢትዮጵያ ውጪ የጨዋታ ህግን ነው የምንተገብረው ፤ ነፃ ሆነን ነው የምናጫውተው። እኛ ሀገር ስመጣ ሁሉም ዳኛ የዳኝነት ዕውቀት አለው ብዬ አልናገርም፣ ዕውቀታችን የተለያየ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን እዚህ ሀገር የዳኛን ውሳኔ የመቀበል ችግር አለ። የምትሰጠው ውሳኔ በብዙ መንገድ ይተረጎማል ነፃ ፤ ሆነህ ማጫወት አትችልም። ለዛም ይመስለኛል የሚገባውን ክብር ሳናገኝ የቀረነው።

የኢትዮጵያ ዳኝነት አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ትላለህ ?

ማስቀጠል ከተቻለ የኢትዮጵያ ዳኝነት አሁን ያለበት ደረጃ በጣም ጥሩ ነው። ከፌዴሬሽን የተሟላ ነገር ባይኖርም ዳኛው በራሱ ጥረት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። ግን አሁን በዚህ ሁኔታ ያለው ዳኝነት ማስቀጠል ያስፈልጋል። ብቅ ብለው የሚታዩትን ወጣት ዳኞችን መንከባከብ እንዳይጠፉ እየጠበካቸው በአቅማቸው እየሰሩ ልምድ እንዲያገኙ ከፍተኛ ሥራ መሰራት አለበት።

የቤተሰብ ህይወት..?

ሁለት ወንድ ልጆች አሉኝ አንደኛው ኢዛና ቴዎድሮስ ይባላል። ሁለተኛው አስር ወሩ ነው ክርስቲያን ቴዎድሮስ ይባላል። ባለቤቴ ዊንታና አበበ ትባላለች ፣ አሪፍ የትዳር ህይወት እየኖርን እንገኛለን።

በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልክት አለ?

ትንሽ አሁን ያለንበት ጊዜ ብዙ ቁጭ የሚያደርግ ነው ፤ አንድትንቀሳቀስ አያደርግም ። በተለይ ዳኞች ራሳቸውን መጠበቅ እና መስራት አለባቸው። በቡድን መስራት ባይቻል እንኳን በግላቸው የልምምድ መመሪያዎችን በመከተል በደንብ ልምምድ መስራት አለባቸው። እኛ እስካሁን ልምምድ አላቆምንም አየሰራን ነው። ልምምድ መስራት ጥቅሙ ደግሞ አንደኛ ጤናህንም ትጠብቃለህ ሁለተኛ የዳኝነት አቅምህ እንዳይጠፋ ማድረግ ትችላለህ። ሌላው የእንግሊዘኛ ቋንቋዎችን መማር ፣ የዳኝነት ህጎችን በደንብ እያነበቡ ፣ የጨዋታ ፊልሞችን በተደጋጋሚ በማየት እራሳቸውን እየጠበቁ ቢቆዩ እላለው። ሁላችንንም ፈጣሪ ከመጣብን ወረርሺኝ ጠብቆን ወደምንወደው እግርኳስ እንድንመለስ መልካም ምኞቴ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!