የሰማንያዎቹ… | ይልማ ከበደ (ጃሬ)

አንድ ግብ ጠባቂ ሊያሟላ የሚገባውን ነገር ሁሉ የያዘ ነው። ረጀም ዓመታት በአምበልነት በወጥ አቋም ሀገሩን እና ክለቡን በማገልገል መዝለቅ ችሏል። በአሁኑ ወቅት በአሳዛኝ ሁኔታ የሚገኘው የሰማንያዎቹ ድንቅ ግብ ጠባቂ ይልማ ከበደ (ጃሬ) ማነው ?

ባደገበት ከተማ ሀዋሳ ታቦር ትምህርት ቤት ሁሌም ከተማሪዎች ሁሉ አርፍዶ በመምጣት በሩ ሲዘጋባት ከጥበቃዎች እይታ ተሰውሮ አጥር ዘሎ የሚገባ አንድ ተማሪ ነበር። ጥበቃዎቹ እርሱ አጥር ዘሎ በገባ ቁጥር አባሮ በመያዝ ሊቀጡት ቢያስቡም የሚሳካላቸው አልሆነም። በጣም ከመማረራቸው የተነሳ ይህ ልጅ አይያዝም ጀርጃራ ነገር ነው ብለው ‘ጃሬ’ እያሉ ይጠሩት ጀመር። ታዲያ ይህ አርፍዶ በመምጣት የትምህርት ቤቱን አጥር እየዘለለ የሚገባው ታዳጊ አርፍዶ የመምጣቱ ምክንያት ኳስ መጫወት በጣም ከመውደዱ የተነሳ የትምህርት መግቢያ ሰዓት እያለፈው ነበር። ይልማ ከበደ ትውልዱ ይርጋለም ከተማ ቢሆንም ያደገው በሀዋሳ ነው። እንደአጋጣሚ ሆኖ ኃይቅ ለሚባል ቡድን እየተጫወተ ሳለ ግብ ጠባቂው ይጎዳል። አሰልጣኙ ማንን እንደሚያስገባ እያሰበ ሳለ ‘እኔ እችላለው’ ብሎ በመግባት በተጀመረበት አጋጣሚ ዘልቆ ኢትዮጵያ በግብ ጠባቂዎች ታሪኳ ካገኘቻቸው ድንቅ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ለመሆን ችሏል።

በ1972 በመጀመርያ ክለቡ ደቡብ ፖሊስ መጫወት ጀመረ። ለሰባት ዓመታት በወታደራዊው ክለብ መጫወቱ ምን አልባትም ደፋር ፣ ቆፍጣና ፣ ጎሉን በንቃት የሚጠብቅ ወታደር እንዲሆን ያስቻለው ይመስላል። ከደቡብ ፖሊስ በመቀጠል በ1979 አዲስ አበባ በመምጣት ለሌላኛው የወታደር ክለብ ኦሜድላ ተጫውቷል። እስከ መንግስት ለውጥ መዳረሻ 1981 ድረስ ለሦስት ዓመታት ከተጫወት በኃላ ኢትያጵያ መድንን ተቀላቅሏል። በመድን ቤት እጅግ የተሳኩ አስራ አምስት ዓመታትን አምበል በመሆን ጉዳት ወይም የተለየ ነገር ካላጋጠመው በስተቀር በብዙ ጨዋታዎች በወጥ አቋም በግብ ጠባቂነት ከማገልገሉ በተጨማሪ በረዳት አሰልጣለኝነትም ሰርቷል። ከኢትዮጵያ መድን ጋር ሦስት የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ያሳካው ጃሬ በተለይ በአፍሪካ የክለቦች ኮፌዴሬሽን ካፕ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ድረስ በተጓዘው የመድን ስብስብ ውስጥ ከነበሩ እና ድንቅ እንቅስቃሴ ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር።

ወደ መጨረሻው አካባቢ አብሮት የተጫወተው እንድርያስ ብርሀኑ ስለ ጃሬ እንዲህ ይላል። “ጃሬ ከእኔ ጋር በተጫወተበት ወቅት በጣም ደፋር ፣ በጣም ተጫዋች የሚያነሳሳ ፣ ጉልበት የሚሰጥ ፣ ከኋላ ሆኖ እየተቆጣ በፍቅር በማስተባበር ቡድን የሚመራ ፣ ከአሰልጣኝ በላይ ጨዋታ የማንበብ ዕይታው ከፍተኛ የሆነ ትልቅ አቅም የነበረው ግብጠባቂ ነው።”

ይልማ ከበደ በ1984 ለመጀመርያ ጊዜ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ከተደረገለት ጀምሮ ለአምስት ዓመታት በሴካፋ እንዲሁም በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ሀገሩን አገልግሏል።

በዘመኑ ከተነሱ ጥሩ ግብጠባቂዎች አንዱ የነበረው እና በብሔራዊ ቡድን ከጃሬ ጋር አብረው መጫወት ከቻሉት መካከል አንዱ የነበረው በለጠ ወዳጆ ስለ ጃሬ ሲናገር “ጃሬ በጣም የሚገርም አቅም የነበረው። አንድ ግብ ጠባቂ ሊያሟላ የሚገባቸውን ነገሮች ሁሉ አሟልቶ የያዘ ግብጠባቂ ነው። በጣም አቅም ያለው ረዥም ዓመት በወጥ አቋም ማገልገል የቻለ ነው። የአንድ ግብ ጠባቂ መለኪያው ቡድን ይዞ መውጣት ነው። ጃሬ ደግሞ ይህን ማድረግ የቻለ በጣም የተሳካለት የማደንቀው ግብጠባቂ ነው።” ይላል።

ለ24 ዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ከፍተኛ ግልጋሎት በመስጠት በ1996 ጓንቱን ከሰቀለ በኃላ ወድያውን ወደ ግብጠባቂዎች አሰልጣኝ በማምራት በቡራዩ ከተማ በኃላም በእግርኳስ ተንታኝነት በሸገር ኤፍ ኤም፣ በብስራት ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ያለውን ልምድ ለትውልዱ ሲያጋራ ቆይቷል። ከ2008 ጀምሮ ለአንድ ዓመት የወልዲያ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ባለበት ወቅት ባጋጠመው የስትሮክ ህመም ያለፉትን ሦስት ዓመት ብዙ ታሪክ የሰሩ እጁና እግሩ የማይንቀሳቀሱለት ሆነው በከዘራ ለመሄድ ተገዶ በአሳዛኝ ሁኔታ ይገኛል። በሰማንያዎቹ ውስጥ ከተነሱ ምርጥ ግብጠባቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ይልማ ከበደ የዛሬው እንግዳችን ሆኖ የግብጠባቂነት ዘመን ህይወቱን ከዛም በኃላ ስላለው ሁኔታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

“በአስራ ሠባት ዓመታት የኢትዮጵያ መድን ቆይታዬ በጣም አሪፍ ነበር። ቆይታዬን የተሳካ ያደረገልኝ አንደኛ ጥሩ በወጣት የተገነባ ቡድን መኖሩ ሁለተኛ የራሱ የተጫዋቾች ማረፊያ ያለው በመሆኑ እና የልምምድ ሜዳው፣ ክለቡ የነበረው ጥሩ የተጫዋቾች አያያዝ በአጠቃላይ ለተጫዋቾች የተሟላ ክለብ መሆኑ እኛ ትልቅ ነገር እንድናስብ ጥሩ ደረጃ እንድንደርስ ትልቁን አስተዋፆኦ አድርጓል። ከመድን ጋር ሦስት የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አንስቻለው። ሁሌም ወደ ኋላ ጊዜውን ሳስታውሰው የምደሰትበት ግን የአፍሪካ ክለቦች ኮፌዴሬሽን ካፕ እስከ የግማሽ ፍፃሜ የደረስንበት ጉዞ ለኔ ትልቁ ስኬቴ ነው።

“ሁሌም የማስታውሰው የማረሳው ገጠመኝ በ1985 መድን ላለመውረድ የሚጫወትበት ወቅት ነበር። የመጨረሻው ጨዋታ ከኪራይ ቤት ጋር ነበር። አንድ ለዜሮ እየተመራን እስከ እረፍት መውጣት ችለናል። ሁላችን ተጨንቀናል በአፍሪካ መድረክ ረዥም ርቀት በተጓዝንበት ዓመት ልንወርድ ነው የሚል በቡድኑ ውስጥ ፍርሀት ነበር። ሆኖም በአለቀ ሰዓት ሁለት ጎል አስቆጥረን ከመውረድ የተረፍንበት ጊዜ መቼም የማረሳው ገጠመኝ ነው። አስበው መድን ቢወርድ የሚኖረው ስሜት መጥፎ ነበር።

“በግብጠባቂ በቆየሁበት ዓመታት በጣም የሚያስቸግሩኝ ሁለት አጥቂዎች ነበሩ። በጣም የሚያስፈሩ ልትቆጣጠራቸው የማትችላቸው። የበረኛን አቋቋም፣ አንቅስቃሴ የሚከተታሉ ኃይለኛ አጥቂዎች የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሙሉጌታ ከበደ እና የመብራት ኃይሉ ኤልያስ ጁሀር ናቸው። በጣም በደካማህ ጎንህን፣ መዘናጋትህን አይተው የሚጠቀሙ አጥቂዎች ናቸው። እንዲሁም አሰግድ ተስፋዬ ጥሩ አጥቂ ነው። እነዚህ አጥቂዎች ዛሬ በማዳቀል ብንፈልጋቸው እንኳን የማናገኛቸው ምርጥ አጥቂዎች ናቸው።

” አሁን ላይ ሆኜ የምቆጨው መድን በ1996 ወደ ብሔራዊ ሊግ የወረደበት ጊዜ ነው። ምነው አብሬው ወርጄ ወደ ላይ ይዤው በወጣው ኖሮ ብዬ ሁሌም እቆጫለው። በወቅቱ እኔ ጓንቴን በመስቀሌ መጫወት አቁሜ ሆነ እንጂ ብጫወት ኖሮ በእርግጠኝነት እመልሰው ነበር።

“ጃሬ የሚባለውን ቅፅል ስም ያወጡልኝ ሀዋሳ የነበሩ የታቦር ትምህርት ቤት ጥበቃ አቶ ዮሴፍ የተባሉ ሰው ናቸው። ትምህርት ቤቱና የእኛ ቤት አጠገብ ለአጠገብ ናቸው። ሁሌም አስር ሜትር ለማይሞላ ርቀት አረፍድ ነበር። እና አጥር ዘልዬ እገባለው። ሊዙኝ ቢፈልጉ ሮጬ አመልጣቸዋለው። በዚህ የተነሳ ይህ ጀርጀራ የሆነ ልጅ አይያዝም በማለት ጀርጀራ የሚለው አጥሮ ጃሬ በመባል መጠራት ጀመርኩ ይህው እስካሁን ከአባቴ ስም በላይ ጃሬ የሚለው መጠርያ ስሜ ሆኖ ቀርቷል።

“ግብጠባቂነትን ከማቆሜ በፊት ተጫዋች እና አሰልጠኝ በመሆን ድርብ ኃላፊነት ተሰጥቶኝ በ1994 ከጥላሁን መንገሻ ጋር አብሬ ሰርቻለው። በዚህም ጊዜ ነው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን የሆነው። አቁሜ ጓንቴን እንዳወለኩ ወድያውኑ የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስጄ ከ1998እና 99 ለሁለት ዓመት የቡራዬ ከተማ የግብጠባቂ አሰልጣኝ የሆንኩት። ምንም እንኳን ለዘጠኝ ዓመት የግብጠባቂ አሰልጣኝ ሳልሆን ቀርቼ የተለያዮ ስልጠናዎችን እየወሰድኩ ቆይቼ በ2008 የወደልድያ የግብጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን ለአንድ ዓመት እየሰራው ለቀጣይ የውድድር ዓመት ቅድመ ዝግጅት እያደረግን የስትሮክ ህመም አጋጥሞኝ ለመቀመጥ ተገደድኩ።

“አሁን ያለሁበት ሁኔታ ሁለቱም ግራ እጄ እና እግሬ አይንቀሳቀስም፤ በከዘራ ነው እንደምንም ብዬ በአካባቢዬ ከቤት ወደ ውጭ እየተንቀሳቀስኩ ያለሁት። ህክምና ወጪዬን ኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ክለቡ ለህክምና ወጪዬ እየሸፈነልኝ የፊዚዮትራፒ ህክምና እየተከታተልኩ መቆየት ችዬ ነበር። መድን እስካሁን ድርሻውን ተወጥቶ አሳክሞኛል። ሆኖም አሁን ገንዘቡ አልቆ ፊዚዮትራፒ ማድረግ አልቻልኩም። ህመሙም ወደ ቀድሞ ባህሪው እንዳይመለስ እሰጋለው። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአቅም ውስንነት እንዳለብኝ ተረድቶ ድጋፍ እንዲደርግልኝ ለፌዴሬሽኑ ፀሐፊ ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ደብዳቤ ካስገባው ከአስራ አምስት ቀን ሆኖኛል፤ እስካሁን ግን ምላሽ አላገኘሁም። በዚህ አጋጣሚም ሶከር ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ ተከታይ አንፃር የስፖርት ቤተሰቡ ያለሁበትን ችግር ተረድተው የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉልኝ ጥሪ እንድታስተላልፉልኝ ጥሪዬን አቀርባለው።

“የመድን እግርኳስ አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም ያሳስበኛል። ይህ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ብዙ አስታዋፅኦ የድረገ ብዙ ትውልዶችን የፈጠረ ተወዳጅ ክለብ ለምን እንዲህ ሆነ እያልኩ አስባለው። ምን አለ ከህመሜ ቶሎ ድኜ ባለኝ እውቀት እና ልምድ መድንን ረድቼ ወደ ቀድሞ ስሙ መመለስ እና ወደ ላይ የሚወጣበት መንገድ ነው እያሰብኩ ያለውት። የመድን ነገር በጣም በጣም ነው የሚያሳስበኝ።

“አሁን ያለው ግብጠባቂ ችግር ምን መሰለህ ብዙ ክለቦች ለጊዚያዊ ውጤት ብለው ከውጭ ሀገር ነው ግብጠባቂ የሚያመጡት። ስለዚህ ከህፃናት ጀምሮ አሳድጎ ለትልቅ ደረጃ የሚያደርስ ክለብ የለም። የሀገሩን በማልያ ወደ የሚመጣ ግበረጠባቂ መፍጠር አልተቻለም። ከውጭ በሚልየን ብር ግብጠባቂ አውጥተህ ከምታመጣ እዚህ ለፕሮጀክት ላይ ቢያውሉት ጥሩ ነው። ዛሬ እንዲህ በየግብጠባቂ ችግር ውስጥ አንገባም። እንዲሁም በየክለቡ ያሉ የግብጠባቂዎች አሰልጣኞች በደንብ አይሰሩም። ግብጠባቂዎቹ ዓላማ እንዲኖራቸው ለብሔራዊ ቡድን መጫወት እንዳለባቸው አያደርጓቸውም። በእኛ ዘመን የነበሩ አሰልጣኞች ከፍተኛ ደረጃ እንድንደርስ አድርገውን ነው ይቀርፁን የነበረው። እንዳውም እናተን ካገኘው ከ2013 ጀምሮ ኢትየለጵያ ውስጥ በየትኛውም ሊጋችን ምንም ዓይነት የውጭ ግብጠባቂ የማይኖርበት እንዲሆን እታገላለው።

“የእግርኳስ ተንታኝነት የጀመርኩት 2000 ላይ ነው ከመሰለ መንግሥቱ ጋር በሸገር ኤፍኤም የጀመርከት። ከትልልቅ አሰልጣኞች ጋር አብሬ መስራቴ ከእነርሱ የወሰድኩት ብዙ ልምድ አለ። በተጨማሪ ከማየው እና ሁሉንም ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ገብቼ እንድከታተል የስታድየም ነፃ መግቢያ ስለነበረኝ ሁሉንም ጨዋታ ስለምከታተል የእያንዳንዱን ጨዋታ ታክቲክ እና ቴክኒክ ለይቼ ስለማቅ በዚህ ሁኔታ እያዳበርኩት መጥቼ ተንታኘ ሆኛለው። ህመሜ እስካጋጠመኝ ድረስ ሥሰራ ቆይቼ በህመሜ ምክንያት አቋርጫለው። በቀጣይ ህመሜ ሲስተካከል ወደ ቀድሞ ተንታኝነቴ እመለሳለው ብዬ አስባለሁ።

“በመጨረሻ ዕድሉን ከሰጠኸኝ ማመስገን የምፈልገው የተለያዩ አካላቶች አሉ። ህመሙ ባጋጠመኝ ወቅት ጎኔ ለቆሙት በተለይ ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ስፖርት ክለብ በጋራ በመሆን ትልቅ የህክምናዬን ወጪ የሸፈኑት እዚህ ላለሁበት ደረጃ ያደረሱኝ። በግል የማሰለጥናቸው ቡድኖች መካከል በጁቬንትስ ስፖርት ክለብ በተለይ የኔ ሪልኢስቴት ባለቤት አቶ እንዳለ ይርጋ። የተክለሃይማኖት አካባቢ ማኀበረሰብ በተለይ አቶ ውድነህ ማሞ እና ምስጋና ቅርብልኝ። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች፣ በኢትዮጰያ የቼልሲ ደጋፊዠዎች በአጠቃላይ የስፖርት ቤተሰቡን አመስግንልኝ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!