መንግሥቱ ወርቁ ሲታወሱ (፯) | መንግሥቱ ወርቁ ወይስ መንግሥቱ ነዋይ ?

በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምን ጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። የታላቁን የእግርኳስ ሰው ዕድገት ፣ የእግር ኳስ አጀማመር ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ትውስታዎች እና የብሔራዊ ቡድን አስተዋፅኦን እያነሳንም ሰንብተናል። ዛሬ ደግሞ ታላቁ ስምንት ቁጥር ከሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድል በኋላ ካሳደጉት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጋር የነበረውን አጭር ቆይታ መሰረት አድርገን ይህችን ትውሳት አቅረብንላችኋል።

ማስታወሻ ፡ በገነነ ሊብሮ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ከመንግሥቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እና የልሣነ-ጊዮርጊስ ጋዜጣ የታላቁን ሰው ህልፈት ተከትሎ በተከታታይ ያወጣቸው ፅሀፎች ዋነኛ ግብዓት እንደሆኑ እንገልፃለን።

1953 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሳ ዓመት ነው። የንጉሱን ከሀገር ውጪ መሆን ተከትሎ በወንድማማቾቹ መንግሥቱ ነዋይ እና ግርማሜ ነዋይ አጋፋሪነት አይነኬ በነበሩት ንጉስ ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተደረገበት ዓመት ነበር። ‘ታድያ ይሄ ከእግር ኳስ ጋር ምን አገናኘው ?’ ካላችሁ ለሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለአንድ ዓመት መራዘም መንስኤ በመሆኑ ነው። ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በግብፅ አስተናጋጅነት 1951 ላይ ስለነበር የተከናወነው ከሁለት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ውድድር ማሰናዳት ነበረባት። ሆኖም ያልተሳካውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ውድድሩ በ1954 እንዲካሄድ ሆነ። ባሳለፍነው ሳምንት ባስነበብናችሁም ፅሁፍ መሰረት ኢትዮጵያ ውድድሩን አሸንፋ ዋንጫውን አንስታለች።

በመዲናዋ ህዝብ ቁጥር ጥቂት በነበረበት እና ለእግርኳስ ያለውም ፍቅር ማቆጥቆጥ በጀመረበት በዚያ ወቅት ንጉሱ ለስፖርቱ ቅርብ ሆነው ዕድገቱን ለማፋጠን ይሞክሩ ነበር። በስማቸው የተሰየመውን እና እስከዛሬም አገልግሎቱ የቀጠለውን ስታድየም ከማስገንባት ባለፈ ንጉሱ ብሔራዊ ቡድኑ የወዳጅነት ጨዋታ ሲያደርግም ሆነ በክለቦች የዋንጫ ጨዋታዎች ላይም በስታድየም የመገኘት ልማድ ነበራቸው። ከታላቁ የስፖርት ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር በቅርበት በመስራትም ከስታድየሙ ግንባታ ውጪ ለብሔራዊ ቡድኑን የተለያዩ እገዛዎችን ያደርጉ ነበር። ለወዳጅነት ጨዋታዎች ቡድኑ ወደ ውጪ እንዲሄድ ፍቃድ ከመስጠት አልፎ ቡድኑ ከሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፊት በቤተመንግስት ተቀምጦ ልምምድ እንዲያደርግ ጭምር ሀሳብ አቅርበው ነበር።

በመጨረሻም በዚህ መንገድ የሚንከባከቡት ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫን አንስቶ ፌሽታ ሆነ። ታድያ በልጅነቱ ከቋራ ያስመጡት እና ‘አሻግራቸው’ በሚለው ቤተሰቦቹ ባወጡለት ስም የሚያውቁት የፊት አውራሪ ወርቁ ስንቄ ልጅ የያኔው መንግሥቱ ወርቁ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ሆኖ ሀገሩን ለስኬት አብቅቷል። በእርግጥ መንግሥቱ በኳስ ፍቅር ተነድፎ ንጉሱ ሊጎበኙት ወደሚመርበት አዳሪ ትምህርት ቤት በተደጋጋሚ ሲመጡ አግኝተውት አያውቁም። ምክንያቱም የእረፍት ቀናቱን ኳስ በመጫወት ሲያሳልፍ ጠዋት ወጥቶ ማታ ይገባ ስለነበር ነው። ከዚያም በጊዮርጊስ እና በብሔራዊ በድን ውስጥ በፈጣን ዕድገት እዚያ ደረጃ ሲደርስ በሚወደው ስፖርት ውስጥ ሆኖ ሄዶም ሳይጠቃቸው ቀርቷል። በመሆኑም በአካል ካገኙት ብዙ ጊዜ ሆኖ ነበር።

ኢትዮጵያ እና ግብፅ ባደረጉት የፍፃሜው ጨዋታ ዕለት ንጉሱ በተገኙበት ደጋፊው መንግሥቱ በግብፅ ተከላካዮች ተይዞም በጨዋታው ላይ ልዩነት ለመፍጠር ለጓደኞቹ ኳስ ለማድረስ ሲሞክር እና አልሳካ ሲለው በማየት ‘አይ መንጌ ሠርተህ ነበር እኮ ምን ያደርጋል ተቀባይ አጣህ እንጂ’ በማለት ሲያሞካሸው ሰምተዋል። ወቅቱ የመንግሥቱ ነዋይ እና የወንድሙ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ወሬ ያልበረደበት በመሆኑም ንጉሱ ‘ሠርተህ ነበር ተቀባይ አጣህ’ የሚለው አባባል ሳይከነክናቸው አልቀረም። ለቀድሞው ጀነራል መንግሥቱ ነዋይ እንጂ ሜዳ ላይ ላለው መንግሥቱ ወርቁ የተሰነዘረ ማሞካሻ አድርገው አልወሰዱትም። ብሔራዊ ቡድኑ ከድሉ በኋላ የራት ግብዣ በተደረገለት ወቅትም መንግሥቱን አጠርተው በቁጣ “አሰድበን ! አስወቅሰን ! ሕዝቡንም አነሳሳ” ብለውታል። ቆይተውም ” ታድያ ምን ያስደብቅሀል ዋንጫውን መጥተህ አትቀበልም ነበር ? ” አሉት። እርሱም ያን ያላደረገው የቡድኑ አምበል ስላልሆነ እንደሆነ አስረድቷቸው ከመለያየታቸው በፊት ከቋራ አምጥተው ያሳደጉት እና ከገጠር ህይወት በሳቸው ችሮታ አምልጦ የሀገሪቷ የእግር ኳስ ጀግና እስከመሆን የዘለቀው ያሳደጉት ልጃቸው ስም በትረ ሥልጣናቸውን ለመቀማት ከሞከረው ጀኔራል ስም ጋር የመመሳሰሉ ጉዳይ ደስ እንዳላሰኛቸው በሚገልፅ መልኩ ” በል ይሄን ስምህን አልወደድንልህም” ብለው አሰናብተውታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!