ኡመድ ኡኩሪ ለኢኤንፒፒአይ በቋሚነት ተሰልፏል

ዕሁድ ምሽት በተደረገ የግብፅ ፕሪየምር ሊግ ጨዋታ ኤኢንፒፒአይ ዋዲ ደግላን 3-2 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ጨዋታው የስድስተኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ ከረጅም ግዜ በኃላ ወደ ነዳጅ አምራቾቹ ቋሚ አሰላለፍ ተመልሶ በጨዋታው ላይ መጫወት ችሏል፡፡

ካይሮ በሚገኘው ጁን 30 ኤር ድፌንስ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኡመድ ለ61 ደቂቃዎች መጫወት ችሏል፡፡ ኡመድ በጨዋታው ላይ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን ለግብ የቀረበ ሙከራም ማድረግ ችሏል፡፡ የቀድሞ የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ኡመድ በ61ኛው ደቂቃ በኪኦለን ላማሃ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

የቀድሞ የፈርኦኖቹ ግብ ጠባቂ ኤሳም ኤል ሃድሪ ሶስት ግቦችን በማስተናገድ ጨዋታውን ሊያጠናቅቅ ተገዷል፡፡ የ43 ዓመቱ የአራት ግዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ሃድሪ በሳምንቱ መጨረሻ ዳግም ለግብፅ ብሄራዊ ቡድን ተጠርቷል፡፡ በጨዋታው ላይ የቀድሞ የቼልሲ ኮከብ ፍሎረንት ማሉዳም ለዋዲ ደግላ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡

ከፍተኛ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ለኢኤንፒፒአይ የድል ግቦቹን መሃሙድ ካሆድ (ሁለት) እና አህመድ አብደልዛሃር ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የዋዲ ደግላን ሁለት ግቦች ኤል ሳዒድ ሳሊም እና ራጋብ ነቢል አስቆጥረዋል፡፡ ሳሊም ያስቆጠራት ግብ ከረጅም ርቀት የተቆጠረች ድንቅ ግብ ነበረች፡፡

የአሰልጣኞች ሹም ሽር በበረከተበት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ የኤንፒፒአይ አሰልጣኝ ሃምዳ ሰድኪ የቀድሞ ክለባቸው ላይ ጣፋጭ ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡ ሰድኪ በዋዲ ደግላ ባሳዩት መጥፎ የውድድር ዘመን አጀማመር ከክለቡ ተሰናብተው በምትካቸው የቀድሞ የቲፒ ማዜምቤ አሰልጣኝ ፓትርስ ካርትሮን መሾማቸው ይታወሳል፡፡

የግብፅ ፕሪምየር ሊግን አል አሃሊ በ40 ነጥብ ሲመራ ዛማሌክ በ35 ይከተላል፡፡ የኡመዱ ኢኤንፒፒአይ በ28 ነጥብ 10ኛ ነው፡፡ የሽመልስ በቀለ ክለብ የሆነው ፔትሮጀት በ30 ነጥብ ስድስተኛ ነው፡፡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው እና የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ መከላከያን የሚያስተናግደው በምስር አል ማቃሳ እና ኢኤንፒፒኤ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 5 ብቻ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *