“ወደ ፋሲል ያመራሁበት ምክንያቴ ዋንጫ ለማንሳት ነው” የዐፄዎቹ አዲስ ፈራሚ በረከት ደስታ

ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣት ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል፡፡ በየጊዜው ፈጣን እና ሳቢ የእንቅስቃሴ ለውጦችን ከአዳማ ከተማ ከ20 ዓመት በታች ቡድን በ2009 ካደገ በኃላ በፕሪምየር ሊጉ እየደመቀ የመጣው የመስመር አጥቂው በረከት ደስታ በአዳማ ከተማ በዋናው ቡድን አራት ዓመታትን በማሳለፍ ለልጅነት ክለቡ በሚገባ ግሎጋሎትን መስጠት ችሏል፡፡ በክረምቱ ከአዳማ ከተማ ጋር ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሀዲያ ሆሳዕናን ለመቀላቀል ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረ ቢሆንም በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት በመገኘት ፋሲል ከነማን በይፋ ተቀላቅሏል፡፡

ለሁለት ዓመታት በክለቡ ለመቆየት ያመራው የመስመር አጥቂው ተከታዩን ሀሳብ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

“አዳማ በቆየሁባቸው አራት ዓመታት የተሻለ እና ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለሁ። በታዳጊነቴ ስለገባሁም ደስ የሚሉ ቆይታዎችን አድርጊያለሁ። ሦስት ዓመት ቋሚ ሆኜ ተጫውቻለሁ። በአዳማ በነበረኝ ቆይታ ሁሉንም ማመስገን እፈልጋለሁ።

“ፋሲልን በመቀላቀሌ ደስ ብሎኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ እና ጥሩ ከሚባሉት አንዱ ወደሆነው ቡድን በማምራቴ በውስጤ እጅግ ደስታን ፈጥሮልኛል። ፋሲልን በመቀላቀሌ ጥሩ ውሳኔን የወሰንኩ ያህል ይሰማኛል።

“ሀድያ ሆሳዕና በእርግጥ ፈርሜ ነበር። ሆሳዕና እንደ የትኛውም ቡድን ጥሩ ቢሆንም ባለው ስብስም ሆነ ውጤት ፋሲል የተሻለ ነው። የተሻሉ ደጋፊዎች ያሉበት እና ጥሩ ጥሩ ነገሮች የሚገኙበት ክለብ ነው ብዬ ነው የገባሁት።

“ፋሲል የገባሁበት ምክንያቴ ዋንጫ ለማንሳት ነው፡፡ እሱንም እናሳካለን ብዬ ተስፋ ስለማደርግ ነው። ራሴንም ለመፈተንም ጭምር ነው ልገባ የቻልኩት። ካለሁበት ክለብ ወደተሻለ ክለብ ገብቼ ራሴን ለመፈተሽ ፋሲልን ተቀላቅያለሁ። ሁለት የተሳኩ ዓመታት አሳልፋለሁ ብዬ አስባለሁ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!