ታክቲክ ፡ ጥብቅ መከላከል እና ስኬታማ መልሶ ማጥቃት ድቻን ለድል አብቅቶታል 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት እሁድ እለት በተደረገ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ባለሜዳው መከላከያን 2-1 በመርታት ደረጃውን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል ችሏል፡፡ የሶከር ኢትዮጵያው የታክቲክ ሪፖርተር ሚልኪያስ አበራ ጨዋታውን ተከትሎ ታክቲካዊ ትዝብቱን እንዲህ አቅርቦታል፡፡   

የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች አሟሙቀው ወደ መልበሻ ክፍል ከገቡ በኋላ ወደ ሜዳ ሲመለሱ በመሮጫ መሙ ላይ በመሰባሰብ እና ተቀራሪ ወንበር ላይ ከነበሩት የቡድን አጋሮቻቸው ጋር በመቀላቀል ባህላዊውን ሞቅ ያለ ዘፈን ከሚስብ ጭፈራ ጋር ለጥቂት ደቂቃዎች አድርገዋል፡፡ ሁኔታው ቡድኑ ጨዋታውን ከመጀመሩ በፊት ተጫዋቾች ዘና ያለ መንፈስ እንዲኖራቸው የሚያግዝ ስነልቦናዊ ጠቀሜታ ነበረው፡፡

እንግዳው ቡድን በጨዋታው አመዛኝ ደቂዎች ለ4-1-4-1 የተጠጋ 4-5-1 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ የተጫዋቾች የአደራደር ቅርፅ ሲተገብር መከላከያ ደግሞ ከ4-4-2 የተለያዩ ቅርፆች አንዱ በሆነው (4-4-2 variants) 4-1-3-2 ተጠቅሟል፡፡

im 1

የድቻ ቀጥተኛ እና መልሶ ማጥቃት

በዘመናዊም ሆነ በቀደመው ጊዜ እግርኳስ የአጨዋወት ስልቶች ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው ዘይቤዎች መካከል የመልሶ ማጥቃት ዘዴ አንዱ ነው፡፡ ብዙዎች የመልሶ ማጥቃት ስት ከአዎንታዊ ጎኑ በላቀ አሉታዊ ገጽታው ያመዝናል ቢሉም ከባላጋራዎቻቸው የእግርኳስ ደረጃ አንፃር ‹‹ትናንሽ›› የሚባሉ ቡድኖች በብዛት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ ትልልቅ የእግርኳስ ደረጃ ያላቸው ቡድኖችም ዘመነኛ የታክቲከ ግብአቶችን በማከል ተግባራዊ ሲያደርጉት በተደጋጋሚ ይታያል፡፡

የአጨዋወት ዘይቤው በጥልቅ እና ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ይመሰረታል፡፡ ወደ ኋላ ባፈገፈገ አቋቋም (deep positioning) ፣ የተጋጣሚን ጫና በመቋቋም (pressure absorbing) ፣ በተጫዋቾች መካከል የሚኖሩ የፊት ለፊት እና የጎንዮሽ ክፍተቶችን በማጥበብ (vertical compactness) ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ኳስን ከባላጋራ ቡድን ከቀሙ በኋላ ደግሞ ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ፈጣን ሽግግር (Defense-Attack transition) ከተጋጣሚ ተከላካዮች ጀርባ የሚገኘውን ሰፊ ክፍተት መጠቀምንም ይጨምራል፡፡ ልክ እንደ ሌሎቹ የእግርኳስ አጨዋወት ስርአቶች (systems) ሁሉ ይህም ጠንካራ የአካል ብቃት ፣ ፍጥነት ፣ የታክቲክ አቀራረብ ግንዛቤ ፣ እይታ ፣ የቅብብሎሽ ስኬት (ምጣኔ) እና የኢላማ ስኬታማነት ይሻል፡፡ የተጫዋቾች የአደረጃጀት እና የቦታ ውህደትም (organization) አስፈላጊ ነው፡፡

ይህ አጨዋወት በሃገራችን እግርኳስ አልፎ አልፎ ቢታይም ቡድኖች በዋነኝነት ሲጠቀሙበት የሚታየው ግን እጅግ ጥቂት ነው፡፡ አተገባበሩም ቢሆን የተጠና እና እንደ ጨዋታ እቅድ (strategy) የሚታይ ተደርጎ የሚወሰድበት አዝማምያ እምብዛም ነው፡፡

በመሳይ ተፈሪ የሚመራው ወላይታ ድቻ በጨዋታው ለመተግበር ሲሞክር የነበረው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ 3 ነጥቦ እንዲያገኝ አግዞታል፡፡ ብዙም ያልተደራጀው መከላከያም ቢሆን ይህን የድቻ የመልሶ ማጥቃት ለመቋቋም ሲቸገር ታይቷል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ ላ አላዛር ፋሲካ ሽመልስ ወደኋላ የመለሳትን ኳስ በፍትነት ከግብ ጠባቂው ይድነቃቸው በፊት ወደ ኳሷ ደርሶ ከአየር ላ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሯታል፡፡ አላዛር በጨዋታው በማጥቃት ሒደት ከነበረው ቁልፍ ሚና ባሻገር በመከላከል ላይም አስተዋፅኦው የላቀ ነበር፡፡ ተጫዋቹ ከኳስ ውጪ የሚያደርገው እንቅስቃሴ (off the ball movement) የመከላከያ ተከላካዮች የመከላከል አደረጃጀት (defensive organization) ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሲያሳርፍ ነበር፡፡

ድቻዎች ሲያጠቁ ወደ 4-1-3-1-1 በሚቀየር ቅርፅ በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል (Attacking third) ላይ እስከ 5 የሚሆኑ ተጫዋቾን በማግኘት ተጋጣሚያቸውን ተጭነው (press አድርገው) ይጫወታሉ፡፡ ይህም የመከላከያዎቹን በኃይሉ ግርማ እና ሚካኤል ደስታን የፈትለፊት እንቅስቃሴ እንዲቀንሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህም ሙሉአለም እና መሃመድ ናስር ከሌላው ቡድን እንዲነጠሉ (Isolated እንዲሆኑ) ተገደዋል፡፡

የወላይታ ድቻ የመስመሮች ሽግግር ን ለማሳካት የሚችሉ ፈጣን የመስመር አማካዮች ባለቤት ነው፡፡ በተሌ እንዳለ መለዮ የድቻን ቀኝ መስመር ሽግግር (flank transition) ሲመራ የነበረበት ብቃት የሚያስመሰግነው ነው፡፡ በትጋት የተጋጣሚ ተጫዋቾችን ተከታትለው ኳስን የሚቀሙት የመስመር ተከላካዮችም (በተለይም ፈቱዲን) ቡድናቸው ላገኘው ድል ተጠቃሽ ሚና ነበራቸው፡፡ ፈቱዲን እና አናጋው የፊት ለፊት ሩጫ ሲያደርጉ ሁለቱ የመሃል ተከላካዮች የመከላከያን የማጥቃት መስመር የተከተለ የጎን እንቅስቃሴ (lateral ball oriented movement) በመከተል በመሃል ተከላካዮች እና መስመር ተከላካዮች መካከል የነበረውን ክፍተት (channels) እንዲያጠቡ አግዟቸዋል፡፡

im 2

በሽግግር ላይ ያለ የመከላከያ ድክመት

ሌላኛው ደካማ የመከለከያ ቡድን ችግር ሽግግር ነው፡፡ ቡድኑ አሁንም በመስመሮች ሉትን ችግሮች ማስወገድ የሚችልበት ታክቲካዊ ስርአት የዘረጋ አይመስልም፡፡ በመስመር አማካይነት እየተሰለፉ ያሉት ተጫዋቾች ተፈጥሮአዊ የቦታው አማካዮች አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ አሳይተዋል፡፡ በማጥቃትም ይሁን በመከላከል ሒደት ሳሙኤል እና ፍሬው የሚገኙት በበኃይሉ እና ሚካኤል ፊት በትይዩ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የመከላከያን መስመሮች ማጥቃት ቀላል እየሆነ ያለው፡፡ ሽመልስ እና ነጂብ በተደጋጋሚ በተጋጣሚዎቻቸው ብልጫ ዪወሰድባቸው ከፊት ለፊታቸው የከላከል ስራውን የሚያግዛቸው አጣማሪ ባለማግኘታቸው ነው፡፡

እጅግ ወደ መሃል ያጠበበው የአማካ ክፍል ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን ካለመስጠቱም በላይ በጫዋታ የሽግግር ሒደቶች ላ ያለው የአደረጃጀት ውህደትም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ የሳሙኤል ፣ የፍሬው እና የሚካኤል እንቅስቃሴ የጨዋታውን ፍሰት እና ሒደት የጠበቀ አለመሆኑ ቡድኑን ቅርጽ ሲያሳጣው በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ አማካዮቸ በእግርኳሱ አለም እጅግ ጠቃሚ ታክቲካዊ ስርአት (systems) በሆነው ሽግግር (tarnsition) ላይ ያላቸው የአካል ብቃትም ይሁን የቦታ አጠባበቅ (positioning) ከኳሱ እንቅስቃሴያዊ አቅጣጫ እና ከጨዋታው ሁኔታ ጋር የተቀናጀ አይደለም፡፡ ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረገው የጨዋታ ሒደት ለውጥ ጨዋታን ለማስጀመር ወደ ኋላ የሚያፈገፍጉት አማካዮች በፍጥነት ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል የሚደርሱበት እንቅስቃሴ ብዙም አመርቂ አልነበረም፡፡ ወደ ፊት የሚላከው ኳስ ለአጥቂዎች ሳይደርስ በተጋጣሚ ተጫዋቾች ይቆረጣል፡፡ ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረገው የሒደት ለውጥም ቢሆን አማካዮቹ ከተከላካዮች ርቀው በመስመሮች መካከል (between the lines) ያለው ክፍተት ሰፍቶ ይታያል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ደግሞ የተጫዋቾች የአካል ብቃት ተመስጋን አልሆነም፡፡

የጨዋታ ሽግግሮች ከተጫዋቾች የመከላከል አደረጃጀት ቅርጽን የመስራት ውህደት ፣ ቀድሞ የጨዋታውን ፍሰት እና ሒደት የመገንዘብ አእምሯዊ ብቃት (game reading) ፍጥነት እና ከፍተኛ አካል ብቃትን ይጠይቃል፡፡ ለቀጥተኛ ማጥቃትም ሆነ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ ላመዘነ አጨዋወት ሽግግሮች መሰረታዊ ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *