የሰማንያዎቹ… | ብዙ ያልተነገረለት የልበ ሙሉው ግብጠባቂ ቅጣው ሙሉ ሕይወት

ታታሪ እና ጠንካራ እንደሆነ የሚነገርለት፣ በተለይ ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው የሚመሰከርለት የሰማንያዎቹ ድንቅ ግብጠባቂ፣ አሰልጣኝ በመሆን ታሪክ የሰራው ቅጣው ሙሉ የዛሬው የሰማንያዎቹ ገፅ እንግዳችን ነው።

በቀደመው ዘመን በኢትዮጵያ የውትድርና ሙያ ውስጥ የሀገርን ልዓላዊነት በከፍተኛ ጀብዱ በማስጠበቅ እና ጠላትን ድባቅ በመምታት የአየር ኃይል ሚና ከፍተኛ እንደነበረ በታሪክ አጋጣሚ ሲነገር ይደመጣል። በተለያዩ ዘመናት ሀገርን ከጠላት በመጠበቅ አኩሪ ታሪክ የፈፀሙ ጀግና ጀግና አብራሪዎችን መፍጠርም ችሏል። ዛሬ ልናወራችሁ የወደድነው ስለ ውትድርናው ዓለም አስደናቂ ገድል ሳይሆን የአየር ኃይል ግቢ ካፈራቸው የሰማንያዎቹ ድንቅ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ስለሆነው ልበ ሙሉ ግብጠባቂ የእግርኳስ ታሪክ ነው።

ቢሾፍቱ (ደብረዘይት) በሚገኘው የአየር ኃይል የጦር ካምፕ ግቢ ፊት ለፊት የተወለደው ይህ ታዳጊ ከልጀነቱ ጀምሮ ለወትሮም ከትምህርት ቤት መልስ እና በእረፍት ቀኑ ወደ አየር ኃይል ግቢ እየሮጠ በመሄድ አዋቂዎቹ ተጫውተው እንደጨረሱ ጠብቆ ከዕድሜ እኩያ ጓደኞቹ ጋር የቅርጫት ኳስ ስፖርት አዘውትሮ ይጫወት ነበር። ሁሌም ቅርጫት ኳስ በመጫወት የሚታወቀው ይህ ታዳጊ በአንድ አጋጣሚ ወደ እግርኳሱ በመግባት በቅርጫት ኳስ አሜካኝነት ያካበተውን በእጁ የመጫወት ክህሎት ወደ እግርኳሱ በመቀየር ጥሩ ግብጠባቂ ይወጣው ጀመር። ይህን ያዩ የአየር ኃይል እግርኳስ ክፍል አመራሮች ሊያቋቁሙት ባሰቡት የ “ቢ” ቡድን ውስጥ ተመልምሎ ሙከራ እንዲያደርግ እድል ያመቻቹለታል። የወቅቱ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ የነበሩት ማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታም የዚህን ልጅ ንቃት እና ቅልጥፍናን ተመልክተው በተስፋ ቡድን ውስጥ እንዲቀላቀል አድርገው ብዙም ሳይቆይ ወደ ዋናው ቡድን አሳድገው አጫውተውታል።

በሰማንያዎቹ ከሚጠቀሱ ድንቅ ግብጠባቂዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ቅጣው ሙሉ በዚህ መልኩ ገና በአስራ ስድስት ዓመቱ በ1976 ወደ ግብጠባቂነት ሕይወቱን በአየር ኃይል ጀምሯል። ለብዙ ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ ያሳልፍ የነበረው ቅጣው ቡድኑ አየር ኃይል በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጨዋታ ነበራቸው። አጋጣሚ ሆኖ የአየር ኃይል ቋሚ ግብጠባቂ የነበረው ፋንታሁን በጨዋታው ላይ ጉዳት አጋጥሞት ተቀይሮ ሲወጣ ጋሽ ሐጎስ ተነስቶ እንዲገባ ያዙታል። በጨዋታው የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂዎች የፈጠሩትን የማጥቃት ጫና በአስገራሚ የማዳን ብቃቱ ተቆጣጥሮ በአየር ኃይል አንድ ለዜሮ አሸነፊነት ጨዋታው እንዲጠናቅ ትልቁን ሚና ተወጥቷል። በነገራችን ላይ የያኔው አየር ኃይል በተደጋጋሚ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የማይበገር እና ጠንካራ ቡድን እንደነበረ ብዙዎች ወደ ኃላ የሚያስታውሱት ሀቅ ነው። በዚህ ጨዋታ የተሰጠውን እድል ተጠቅሞ በጥሩ ሁኔታ መጫወት የቻለው ቅጣው ሙሉ የእጅ ጓንቱን እስካወለቀበት 1990 ድረስ አመዛኙን ጨዋታ ማለት በሚያስችል ሁኔታ በወጥ አቋም በቋሚ ግብጠባቂነት ተጫውቷል።

አስገራሚ የግብጠባቂ ክህሎት እንዳሉት የሚነገርለት ቅጣው ኢትዮጵያ ባዘጋጀችውና “ዳኙ ገላግሌ በተባለበት የ1980 ሴካፋ ዋንጫ ድል ወቅት የተካበ ዘውዴ ተጠባባቂ በመሆን ከስኬቱ ጀርባ የራሱን ታሪክ አስቀምጦ ከጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም እጅ ሽልማት ተረክቧል። በኃላ ላይ የመንግስት ለውጥ መጥቶ አየር ኃይል ቡድን ሲበተን አንድ ዓመት ከማንኛውም ክለብ ጨዋታ ርቆ በግሉ እየሰራ ሳለ በ1985 አሰልጣኝ ወንድማገኝ ከበደ የሚያሰለጥኑትን መብራት ኃይልን መቀላቀል ችሏል። መብራት ኃይል በገባበት ዓመት ከረጅም ዓመት በኃላ ቡድኑ የኢትዮጵያ ቻምፒዮን እንዲሆን የነበረው ሚና በብዙዎች የሚዘነጉት አይደለም።

በወጣት ብሔራዊ ቡድን በክለብ እንዲሁም በአሰልጣኝነት ረጅም ዓመት አብሮት የሠራው ብርሀኑ ባዩ ስለ ቅጣው ሙሉ ሲናገር ” ከ1979 ወጣት ብሔራዊ ቡድን ጀምሮ ቅጣውን አውቀዋለው። ከልምምድ ጀምሮ በጣም ጠንካራ፣ የመሥራት ፍላጎቱ ከፍተኛ የሆነ፣ ለማወቅ ጥረት የሚያደርግ ሰው ነው። ቅጣው ግብጠባቂ ብቻ ሳይሆን አማካይ ተጫዋች ጭምር ነው። በተለይ ጨዋታዎችን ፈጥኖ በማስጀመር የተለየ አቅም የነበረው። በመልሶ ማጥቃት ላይ ተኝቶ ኳስ ይዞ በተኛበት ፍጥነት ወደ ግራና ቀኝ የሚወረውርበት መንገድ የሚገርም ነው። ቅጣው አሰልጣኝ ሆኖ ከመጣ በኃላ በጣም ታታሪ፣ ለማወቅ የሚጥር ደከመኝ የማይል፣ ሁልግዜ ለውጤት የሚተጋ በወጣቶች የሚያምን የሚያሰራ ብቻ ሳይሆን ሰርቶ የሚያሰራ ነው። በተለይ ወጣቶችን ካገኘ በደንብ ትኩረት ሰጥቶ የሚያሰራ ጠንካራ ሰው ነው ” በማለት ይገልፀዋል።

በመብራት ኃይል እንዲሁም በተለያዩ ዘመናት በብሔራዊ ቡድን ሀገሩን ያገለገለው ቅጣው ሙሉ እስከ 1989 መጨረሻ ድረስ በግብጠባቂነት ከተጫወተ በኃላ ራሱን ከግብ ጠባቂነት አግልሏል። ተተኪ ትውልድን ማፍራ ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳም የአሰልጣኝ ስልጠናዎችን በመውሰድ በተጫዋችነትም በመንግሥት ሠራተኝነትም በሚያገለግልበት መብራት ኃይል ክለብ በ1992 የተስፋ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን የአሰልጣኝነት ህይወቱን ጀምሯል። ከታፈሰ ተስፋዬ እስከ መስዑድ መሐመድ ድረስ ሌሎችም ትውልዶችን አሳድጎ፣ አሰልጥኖ ያበቃ የሥራ ሰው እንደሆ ብዙዎች ይስማሙበታል።

በ2004 ከሠላሳ አንድ ዓመታት በኃለ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ባለፈው ወርቃማ ትውልድ ውስጥ የግብጠባቂዎች አሰልጣኝ በመሆን የራሱን ታሪካዊ አሻራ በማሰረፉ ይታወቃል። ይልቁንም ካርቱም ላይ በነበረው የአምስት ለሦስት ሽንፈት ወቅት የመጀመርያው ጎል ሱዳኖች ባስቆጠሩ ወቅት በጣም ከመበሳጨቱ የተነሳ ራሱን እስከ መሳት ደርሶ ወደ ሆስፒታል ማምራቱ ይታወቃል።

ቅጣው በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነቱ ጊዜ
በተለይ በ2004 ካሰለጠናቸው ግብጠባቂዎች መካከል ሲሳይ ባንጫ አንዱ ነው። ይህ የዋልያዎቹ ግብጠባቂ ሲሳይ ስለ ቅጣው ሙሉ ይሄን ይናገራል። “በጣም መልካም ጥሩ፣ የዋህ ሰው ነው። ሰው እንዲለወጥ፣ እንዲያድግ የሚፈልግ ጥሩ ስብዕና ያለው ነው። ግብጠባቂዎች ጥሩ ሆነው እንዲወጡ ይለፋ ይደግም የነበረ፣ ስንሳሳት ደግሞ እንደገና አርመን መልካም ስራ እንድንሰራ እንደ አባት የሚያበረታታ፣ የሚመክር ለእኔ ቅጣው በጣም ታታሪ ትልቅ ሰው ነው። ከሜዳ ውጭ በጣም ዝምተኛ ብዙ የማያወራ ሰውን ሰላም የሚል ሰላምተኛ፣ አንዳንድ ነገሮችን እንደ አባት አይቶ እንዳለየ ሆኖ የሚያልፍ። በጣም የባከብረው የምወደው ብዙ ነገር የለወጠኝ ሰው ነው።”

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሀገሩን ለሦስት ዓመታት በሚገባ ካገለገለ በኃላ ወደ እናት ክለቡ በመመለስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እስከወረደበት 2010 ድረስ በግብጠባቂ አሰልጣኝነት አገልግሏል። በተለያዩ አፍሪካ ሀገራች የግብጠባቂ አሰልጣኝነት ኮርስ የወሰደው ቅጣው ሙሉ ያለፈው ሁለት ዓመት ከአሰልጣኝነቱ በመራቅ በመንግስት ሥራው ተሰማርቶ ይገኛል።

እጅግ የተረጋጋና ዝምተኛ፣ ሰው እንዲለውጥ የሚፈልግ እና በመልካም ባህሪ ተላብሶ ያለፉትን ሠላሳ ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ትልቅ አበርክቶ የነበረው የቀድሞ ግብጠባቂ እና የግብጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን የሰራው የሰማንያዎቹ ኮከብ ቅጣው ሙሉ ስለ እግርኳስ ሕይወቱ ይህን በመሰለ መልኩ አጋርቶናል። በመልካም ቆይታ!

” በመጀመርያ አስታውሳችሁ ለሀገሩ አንድ ነገር ሰርቷል ብላቹ አንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ በጣም አመሰግናለው። በእግርኳስ ባሳለፍኩበት ረጅም ዓመት ውስጥ በስኬት የተሞሉ ዓመታትን አሳልፌያለሁ።

“እኔ ሲቪል ብሆንም ጥሩ ግብጠባቂ እና አሰልጣኝ ሆኜ በሥነ ስርዓት እንዳድግ በአየር ኃይል ያገኘሁት የወታደር ሥነ ስርዓት በጣም ጠቅሞኛል። በኛ ጊዜ አየር ኃይል በጣም የተከበሩ የሚፈሩ የጦር መኮንኖች ያሉበት ግቢ በመሆኑ ብዙ ጥሩ ነገር ተምረን የወጣንበት ነው። ኖሮን እንድናድግ ሆኗል። ከምንም በላይ ግን ነፍሱን ይማረው እና ማስተር ሀጎስ ደስታ ለእኔ ትልቅ አስተዋፆኦ አድርጓል። አየር ኃይል እንድጫወት ያደረገኝ ገና በአስራ ስድስት አመቴ እርሱ ነው። እንደሚታወቀው ማስተር ሀጎስ በታዳጊ የሚያምን ትልቅ አሰልጣኝ መሆኑ ይታወቃል። በኃላም ወደ አሰልጣኝነቱ እንድገባ በማድረግ የተስፋ ቡድኑን እንድረከብ ያደረገኝ ሰው ነው። ብቻ ምን ልበልህ አሁን እዚህ ደረጃ ለመድረሴ የርሱ ድርሻ ከፍተኛ ነው። መወለድ ቋንቋ ነው አባቴ እርሱ ነው። ሁሌም የማስበው መቼም የማረሳው ሰው ነው።

“አየር ኃይል ብዙ ጊዜ ተጠባባቂ በረኛ ነበርኩ። በአንድ አጋጣሚ ፋንታሁን መንግሥቱ ሲጎዳ ጋሽ ሐጎስ እኔን አስበው በጊዮርጊስ ከባድ ጨዋታ እንድገባ እድሉ ተሰጠኝ። ምንም ሳልፈራ አስተማሪ ሲያስተምርህ የሚሰጥህን ፈተና በደንብ መስራት እንዳለብህ ሁሉ እኔም ሜዳ ላይ ጥሩ ነገር አሳይቼ ጨዋታውን አሸነፍን። ከዛ በኃላ በእኔ ያላቸው እምነት ጨምሮ ለብዙ ዓመት በቋሚነት ተጫውቻለው። በእኛ ጊዜ ደግሞ አንዴ የመጫወት እድል ካገኘህ በድጋሚ ቦታህን ላለማጣት ስትል ወጥረህ ትሰራለህ። ለምን ቦታው ከተያዘ የሚለቅልህ የለም። በአንድ አጋጣሚ ምን ሆነ መሰለ መብራት ኃይል እያለው ጓደኞቼ በቃ አንተ ለዚህ ልጅ ልቀቅለት በተጠባባቂ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ቀረ እኮ! ሲሉልኝ ተጎድቼ ወጣው በእኔ ቦታ የገባው ብዙወርቅ ቀላል አንደኛ አይሆንም። በቃ ጋሽ ሀጎስ እንዴት ነው እኔ አልገባም ስለው አንተም እርሱም አንደኛ ሆናቸዋል አሁን ደግሞ እርሱ ይሞክር አለኝ። ይህ አሁን ላሉት ግብጠባቂዎች አስተማሪ ነው። ብዙ ጊዜ በሊጋችን አሁን አሁን የውጭ ግብጠባቂ እየበዛ በመምጣቱ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ተገደው ይሆናል። ሆኖም በየትኛው አጋጣሚ የመጫወት እድሉን እስኪያገኙ ተስፋ ባለ መቁረጥ ልምምዳቸውን መስራት አለባቸው። እድሉንም ሲያገኙ በአግባቡ መጠቀም ራሳቸውን ለተሻለ ነገር ማውጣት አለባቸው። ብዬ እመክራለው። አንዳንድ ጊዜ ምንም ሳንሰራባቸው በራሳቸው ጥረት እዚህ የደረሱትን ግብጠባቂዎች መውቀስ አያሳስፈልግም። እኛ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሰራንባቸው ሥራ ስለሌለ።

“ተኝቼ በመልሶ ማጥቃት ኳስን በፍጥነት የማስጀመር ድፍረቱ እና ልምዱን ያገኘሁት ቅርጫት ኳስ እጫወት ስለነበረ ያ በጣም ግብጠባቂ እንድሆን እና ሳልሳሳት በትክክል ለምፈልገው ሰው ተኝቼ ኳሱን እንድሰጥ ረድቶኛል። ሌላው ተከላካይ እኔ ጋር ምን ይሰራል። ተከላካይ ከሆንክ መጫወት አለብህ እኔ ኳሱን ሲይዝ ቆሞ መመልከት የለበትም። ኃላፊነት ወስጄ ጨዋታው በፍጥነት እንዲጀመር አደርጋለው። አንዳንዴ አንተ ተኝተህ ኳስ ስታቀብል ጎልህን ለቀህ ማን ኳሱን ሊይዝልህ ነው ሲሉኝ መረቡ ይዘዋል እላቸዋለው…… እየሳቀ ። ይህም ብቻ አይደለም ብዙ ጊዜ ተወርውሬ ኳስ አልይዝም። በቅርጫት ኳሱ ያገኘሁት ልምድ ስላለ ነው። ቅርጫት ኳስ ታይሚንግ ነው አይደል በቃ ግብጠባቂ ስትሆንም እንዳይገባብህ ትከላከላለህ፣ ብሎክ ታደርጋለህ ይት ቦታ ሰጥተህ መሮጥ እንዳለብህ ታውቃለህ ስለዚህ ይህን አድርግ ነበር።

“ረጅም ዓመት በቆየሁበት ዓመታት ለኔ እንደ ስኬት የምወስደው ዋናው ከ31 ዓመት በኃላ የአፍሪካ ዋንጫ፣ የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ያለፍንበት ጊዜ ከአዋቂ እስከ ህፃን የተደሰተበት ታሪካዊ ቡድን ውስጥ ግብጠባቂዎችን በማዘጋጀት የሰራሁት ስራ ለኔ ትልቁ ስኬት ነው። ከዚህ ውጭ በ1980 የሴካፋ ዋንጫ በሀገራችን አዘጋጅተን ያስቀረንበት ጊዜ ተጠባባቂ ግብጠባቂ በመሆን ያገለገልኩበት እንዲሁም በ1985 ከኤልፓ ጋር የኢትዮጵያ ሻምፒዮን መሆኔ ብዙ ትውልድ በማፍራቴ። ይህ ለኔ ስኬት ነው።

“ስለ ተጫወትክ ብቻ አሰልጣኝ መሆን አትችልም። መማር የበለጠ ማወቅ ያስፈልጋል። በተለይ በዚህ ዘመን እራስህን ጊዜው በሚጠይቀው ነገር ሁሉ እራስህን ማዘጋጀት አለብህ የምታስተምረው ትውልድን ነው። ተጫውተህ ማለፍ የሚሰጥህ ከፍተኛ ልምድ ቢኖርም መማር አስፈላጊ ነው። እኔ በዚህ ረገድ በተለያዮ ሀገሮች ተምሬአለው። ስለዚህ መማር ኮርሶችን መውሰድ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ነው ሁሌም ለማወቅ ጥረት የማደርገው።

“ብሔራዊ ቡድን ወደ ማሰልጠን የመጣሁት ኤፊ ሆሩና በ2003 ብሔራዊ ቡድን ሲረከብ እኔ ከብዙዎች መሀል ተመርጬ የግብጠባቂነት አሰልጣኝነት ጀምሬ አለው። በኃላም እርሱ ከሄደ በኃላ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጋር በመሆን እስከ 2006 ድረስ መስራት ችያለው። ይህም ብዙ ልምድ ያገኘሁበት በጣም አስደሳች ጊዜ ነበር። ከብሔራዊ ቡድን ስነሳ ወደ ኤልፓ በመምጣት እስከ 2010 ድረስ በመቆየት የግብጠባቂ አሰልጣኝነት አሳልፌለው። ከዛ በፊት ግን በተስፋ ቡድን በአሰልጣኝነት ቆይቻለው።

“ከ31 ዓመት በኃላ በ2004 የአፍሪካ ዋንጫ ያለፍንበት ቡድን ውስጥ ብዙ ትውስታዎች ቢኖሩኝም አዲስ አበባ ከነበረው የመልሱ ጨዋታ በፊት ሁንዱርማን ላይ በነበረው ጨዋታ ሰው ራሽ ሜዳ እና በከፍተኛ ሙቀት እንድንጫወት የተደረገበት ነበር። በደንብ ልጆቼን አሰርቼ አዘጋጅቼ ነበር። በዕለቱ በቋሚ ግብጠባቂነት ሲሳይ ባንጫ ነበር። ገና ጨዋታው እንደጀመረ ቀላል የሚባል ጎል ከእጁ አምልጦ ሲቆጠር በጣም ተበሳጭቼ ደክሜ ለፍቼ አሰርቼ እንዴት ይህ ጎል ይቆጠርበታል። የኔ ልፋት ምድነው እያልኩ ስጨናነቅ ራሴን ስቼ ወድቄ ዶክተ ተረፈ ይዞኝ ሆስፒታል አመራሁ። ጨዋታውን በቀጥታ ያስተላልፍ የነበረው መሰለ መንግስቱ ‘ራሱን ስቶ በመውደቁ ወደ ሆስፒታል አምርቷል’ በማለት ሲዘግብ ቤተሰቦቼ ደንግጠው የተጨነቁበት እና ጨዋታው ሳልከታተል ሆስፒታል የቆየሁበት አጋጣሚ አስታውሳለው።

“ሌላው የ1980 የሴካፋ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ መንግስቱ ኃይለማርያም ጨዋታውን ለመከታተል ስታዲየም ተገኝቶ ነበር። እንደምታቀው በአለቀ ሰዓት አቻ ሆነን በመለያ ምት አሸንፈን በሚገርም ሁኔታ ህዝቡ ደስታውን ሲገልፅ የመንግስቱ የክብር ዘብ ጠባቂዎች እርሱን መጠበቅ ትተው ከእኛ ጋር አብረው ደስታቸውን ሲገልፁ አንድ ተመልካች ጃኬቱን አውልቆ በደስታ በእሳት አያይዞ ሲጨፍር ጓድ መንግስቱ ኧረ ይሄ ሰውዬ ልብሱ ይቃጠል እርሱ ግን እንዳይቃጠል አድኑት ብሎ የተናገረውን ሰው መጥቶ የነገረኝን መቼም አረሳውም። ያው በወቅቱ አምስት ሺህ ብር እና አንድ ቴሌቪዢን መሸለማችንም ይታወቃል።

” ብዙ ጊዜ የምቆጨው እኛ ሀገር ብዙ ጊዜ ታስቦ ይቀራል ሁሉም ነገር አይሳካም። በውጭ ዓለም ተጫውተው ያለፉ በለሙያዎች በስልጠናው ተይዘው በሂደት ታዳጊዎችን እንዲያፈሩ ይደረጋል። እኛ ሀገር ግን ይህ የለም ፕሮጀክት ተብሎ ከዚህ ቀደም ተጀመረ ብዙም ሳይቀጥል ተቋረጠ። ይህ ደግሞ በሙያው ያለፈ ሰው ትውልድ እንዲያፈራ አድርጎታል። ይህ በመሆኑ አዝናለው። ሁሉም ተጫዋች በራሱ መንገድ ነው የሚመጣው በዚህ አጋጣሚ ይህን ትውልድ አደንቃለው። ለምን ብትለኝ በራሳቸው ጥረት ነው የመጡት እከሌ ከዚህ ፕሮጀክት መጣ የምትለው ነገር የለም። ምክንያቱም ፕሮጀክቱ ስሌለ ይህ ደግሞ ሁሌም ውስጤን በጣም ያሳዝነኛል። በዚህ አካጣሚ መንግስት እግርኳሱን የሚመሩ አካላት የታዳጊዎች ፕሮጀክት ስልጠና ወጥ የሆነ የስልጠና መንገድ ተዘጋጅቶ ቢጀመር ለሀገሪቱ እግርኳስ ጠቀሜታው የጎላ እላለው።

“የውጭ ሀገር ግብጠባቂ መብዛት ያሳስበኛል። ይህም የሆነው መሠረታዊ የግብጠባቂ ሥልጠና ስለሌለን ነው። እኔ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ፣ ካሜሮን ፌዴሬሽኑ ልኮኝ ኮርስ ወስጃለው። እነርሱ ሲያስተምርኑ መሰረታዊ የግብጠባቂ ስልጣና የሚጀምረው ከአስራ አራት ዓመት ጀምሮ ነው ይላሉ። ይህ እኛ ሀገር አለ ወይ ስትል የለም። እዚህ ጋር ምንም ነገር በሌለበት ሁኔታ ላይ እከሌ ጥፋተኛ ነው ብሎ መውቀስ ከባድ ነው። ሁሉም ያለማንም እርዳታ በራሱ መንገድ የመጣ ነው። በዚህ ሁኔታ ላይ ደግሞ የውጭ ግብጠባቂ ስታመጣ የበለጠ ችግሩ እየባሰ ይሄዳል። ስለዚህ ቆም ብለን በማሰብ፣ መስራት አለብን። ሙያተኛው የመስራት እድል ሊሰጠው ይገባል። ግን ጠርቶ የሚያናግረን አካል ጠፍቷል። ይህ ርስት አይደለም ሰው አፍርተን ተክተን መሄድ አለብን።

“ኤልፓ መውረድ የሌለበት ቡድን ነው። ይህ ቡድን አንጋፋ ነው። ብዙ ትውሎዶች ያፈራ ታሪካዊ ቡድን ነው። እንደሰው በመውረዱ ታዝናለህ። ይህም የሆነው ካስታወስክ የመጀመርያ ጨዋታችን ከመከላከያ ጋር ነበር። አንድ አቻ ወጣን፣ በመቀጠል አርባምንጭ ሄድን 2–1 አሸንፍን መጣን። በሦስተኛው ከወልዋሎ ተጫወትን 3–1 ተሸነፍን። አርባምንጭ ስንሄድ የሚቀጥረው አሰልጣኝ መጥቷል። ምን ማለት ነው ትእግስት የሚባል ነገር የለም። መነጋገር እየተቻለ በችኮላ አሰልጣኝ ብርሀኑን አነሱት ይህ ስህተት ነበር። ቡድኑን እስከ መወወረድ አድርሶታል። ገና በሁለት ጨዋታ ሰው ታባርራለህ በጣም የሌለ የወረደ ነገር ነው። ቁጭ ብሎ ተመካክሮ ያሉ ችግሮችን መነጋገር እየተቻለ በግብታዊነት ይሄን ውሳኔ ወስኑ። ይህም ቡድኑ ለመውረድ በቅቷል። እኛ እዛ ቦታ ቋሚ እንደማንሆን እናውቃለን እግርኳስ ሂደት ነው መተካካት አለ። ማንም ሰው ይምጣ ይጠቀም በዚህ ቅሬታ የለኝም ሆኖም ያለ አግባብ የማይሆን ስራ ተሰርቶ በመጨረሻ ክለቡ ለመውረድ በቅቷል።

“የቤተሰብ ህይወቴ በጣም ጥሩ ነው። አራት ወንድ ልጆች አሉኝ ሁልም ጎርምሰው ትልልቅ ልጆች ሆነዋል። የሚገርምህ አንዳቸውም በእግርኳሱ አላለፉም ሁሉም በትምህርታቸው ገፍተው በመሄድ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

” ሁለቱን ዓመት ከሜዳ እርቄ በመብራት ኃይል የመንግስት ስራ ላይ ነኝ ወደ አሰልጣኝነቱ የመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። ብዙ ትውልድ አፍርቻለው የራሴንም ታሪክ አስቀምጫለው። በአሰልጣኝነት ትምህርቱም ጥሩ ዶክሜንቶች አሉኝ አሁን ያለ አሰልጣኝነት ብቀመጥም ማንኛውም ክለብ እንድሰራለት ከጠየቀኝ በነፃ ያለ ምንም ክፍያ ያለኝን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ ነኝ።

“በመጨረሻ ጥሩ ግብጠባቂዎች ወደ ፊት እንዲፈጠሩ ስራ መሰራት አለበት። ባልሰራንበት ሁኔታ እነርሱን መውቀስ ከባድ ነው። ስለዚህ አካዳሚዎች መከፈት አለባቸው ብዙ ታዳጊዎች እንዲፈሩ ፌዴሬሽኑ መስራት አለበት መልዕክቴ ነው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!