“ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካልተመረጥኩ ለየትኛው ሃገር ተመርጬ ልጫወት?” በረከት ሳሙኤል

በአዲሱ የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ጨምሮ በቀደሙት ጊዜያትም ከብሔራዊ ቡድን ምርጫ እየተዘለለ መቆየቱን የገለፀው በረከት ሳሙኤል ከዚህ በኋላ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን እንዳገለለ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል።

አዲሱ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከኒጀር ጋር ላለባቸው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ይረዳቸው ዘንድ 41 ተጫዋቾችን መርጠው ዝግጅታቸው በካፍ የልህቀት ማኅከል መከወን ጀምረዋል። ታዲያ በአሠልጣኙ ምርጫ ያልተካተተው የድሬዳዋ ከተማው የመሐል ተከላካይ በረከት ሳሙኤል ከምርጫው ጋር የተያያዘውን ሃሳብ ለሶከር ኢትዮጵያ ከገለፀ በኋላ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሉን አስታውቋል።

“በዚህኛው የብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ እካተታለሁ ብዬ ጠብቄ ነበር። ግን አልሆነም። ሲጀምርም ምርጫው አላሳመነኝም። እኔን ጨምሮ በርካታ በቡድኑ ውስጥ መካተት የነበረባቸው ተጫዋቾች ነበሩ። ግን አሠልጣኙ ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተጫወቱትን ተጫዋቾች ብቻ ነበር ትኩረት ሰጥተው የመረጡት። ይህ ደግሞ አግባብ አይደለም። ሃገራችንን ማገልገል እየፈለግን ዕድሉን ያላገኘን ተጫዋቾች መታየት ነበረብን። ቢያንስ በቡድኑ ተካተን አሳማኝ ካልሆንን መቀነስ እንችል ነበር። ግን ይህ ሳይሆን ቀርቷል።

“እርግጥ እኔ በዚህኛው ስብስብ ብቻ ሳይሆን ከዚህም በፊትም መጠራት በነበረብኝ ጊዜ በብሔራዊ ቡድኑ አልተካተትኩም። ከ2007 ጀምሮ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስጫወት ነበር። በድሬዳዋ ቤት እንኳን ተቀያሪ ሆኜ አላውቅም። ሁሌ ቋሚ እንደሆንኩ ነው። በወጥነት እና በቋሚነት እየተጫወትኩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካልተመረጥኩ ለየትኛው ሃገር ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ልጫወት? ስለዚህ ከዚህ በኋላ ራሴን ከብሔራዊ ቡድን አግልያለሁ።”

ራሱን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያገለለው ይህ የቀድሞ የሱሉልታ እና የሙገር ሲሚንቶ ተጫዋች የነበረው በረከት ከዚህ በኋላ ጥሩ ቢደርሰው ሃሳቡን ሊቀይር ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ አንስተንለት ተከታዩን ሃሳብ ሰጥቶናል።

“በጭራሽ አልመለስም። እስካሁን ሳልመረጥ እንዴት ወደፊት እመረጣለሁ። ምንም ቢመጣ ሃሳቤን አልቀይርም። ወጣቶች እድል ይሰጣቸው እና ሃገራቸውን ያገልግሉ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!