የሴቶች ገፅ | ቆይታ ከነፃነት መና ጋር …

በሀዋሳ ከተማ ያለፉትን አምስት ዓመታት በመጫወት ያሳለፈችው ፈጣን፣ ታጋይ እና ጠንካራዋ ነፃነት መና የዛሬው የሴቶች ገፅ እንግዳ ነች፡፡

ብዙም የሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ከአካባቢዋ መውጣት ባይችሉም ከወንዶች ጋር በሠፈር ውስጥ ተጫውታ ማደጓ ለዛሬው ስኬታማ የተጫዋችነት ዘመኗ እንደረዳት ብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡ በወላይታ ሶዶ ተወልዳ ያደገችው አጥቂዋ ቁመቷ አጭር ቢሆንም ደፋር እና ፈጣን እንዲሁም የማያቋራጥ ትጋት በውስጧ ስለነበር ህልሟን ከትውልድ ከተማዋ ጀምራ እስከ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድረስ ማድረስ ችላለች፡፡ቤተሰቦቿ በልጅነቷ እግር ኳስን ለመጫወት ፍላጎቷን ቢመለከቱም በትምህርቷ ብቻ መግፋትን እንጂ የሷን ምርጫ ፈፅሞ አልተቀበሉትም። በዚህም የተነሳ እግር ኳስን አጠብቃ በጀመረችበት ወቅት በቤተሰቧ አስገዳጅነት ለሦስት ዓመታት ያህል ለመራቅ ተገዳ በድጋሚ ውስጧ የነበረውን ጥልቅ የመጫወት ፍቅር ለማሳካት በድጋሚ መመለስ ችላለች፡፡

ትምህርቷን በአንድ በኩል፤ በትርፍ ሰዓቷ እግር ኳስን ማስኬድን የመረጠችው የያኔዋ ታዳጊ በፍጥነት እየበሰለች ስትመጣ ለሶዶ ከተማ፣ ለወረዳ እያለች ወላይታ ዞንን ወክላ በመጫወት ወዳሰበችበት እቅዷ መንደርደሯን ቀጠለች። 2006 ለወላይታ ዞን ስትጫወት በነበረበት ጊዜ በወቅቱ ተመስርቶ ጥቂት የፕሪምየር ሊግ ቆይታን አድርጎ ወደፈረሰው ወላይታ ድቻ አምርታ በክለቡ ጥሩ ዓመታትን ጊዜ ማሳለፍ በመቻሏ ሀዋሳ ከተማን 2008 ላይ ተቀላቅላ በመጫወት በግሏም ሆነ ከክለቧ ጋር ያለፉትን አምስት ዓመታት ደምቃ ታይታለች።

በክለቡ ውስጥ ሁለት የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ያነሳችው አጥቂዋ በ2009 ሀዋሳ ከተማ ደደቢቶን ረቶ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ሲያነሳ የግቧ ባለቤት እሷው ነበረች፡፡ በቅርብ ጊዜም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሷት የነበረችው ነፃነት መና የዛሬው የአዝናኝ ጥያቄ የሴቶች ገፅ እንግዳ ነች፡፡

በሴቶች ፕሪምየር ሊግ አጭር አጥቂዎች ብዙም አልተመለከትኩም። ስለ ቁመትሽ አስበሽ ታውቂያለሽ …?

አጭር ስለሆንኩ ነው መሰለኝ በጣም ፈጣን ነኝ። ብዙ ጊዜ በእግሬ ነው ጎል የማስቆጥረው። በግንባሬ አግብቼ አላውቅም። ግን አንድ ወሳኝ ጨዋታ 2009 ደደቢትን ያሸነፍንበት ጨዋታ በግንባር አስቆጥሬ ነው ዋንጫ ያነሳነው። ያልተጠበቀ ጎል ነበር፤ አላሰብኩትም። ግን እስከ አሁን በጨዋታ ዘመኔ በግንባር ያገባሁት ያቺን ነው። አጭር በመሆኔ ግን አልተቸገርኩም። ምክንያቱም ከቁመቴ ጋር እንዲሄድ ብዙ ጊዜ በእግሬ ነው የምጫወተው፡፡

የእግር ኳስ አርዓያሽ ማናት ?

ያኔ እኔ ሰፈር ውስጥ ስጫወት አሁን የእግር ኳስ ዳኛ ነች ፈዲላ ትባላለች፤ ሌሎችም አሉ። ወላይታን ብዙ ጊዜ ወክለው ተጫውተዋል። እነርሱን ለማየት በልጅነቴ ወደ ሜዳ እሄድ ነበር፡፡ሰፈር ውስጥ ስጫወት አርዓያዬ ፈዲላ ናት። ክለብ ከገባሁ በኃላ ደግሞ ሽታዬ ሲሳይን በጣም በጣም ነው የማደንቃት። እንሷም መሆንን ነበር የምፈልገው፡፡

ውድድሮች በኮቪድ 19 ተቋርጠው ረጅሙን ወራት ካለ እግርኳስ ነው በርካቶች ያሳለፉት። እነኚህ ጊዜያትን ነፃነት ስታሳልፍ የነበረው እንዴት ነበር ?

ኮሮና ከገባ በኃላ በቀጥታ ወደ ቤተሰብ ጋር ነው የመጣሁት። እኛ ጋር ደግሞ ኮሮና ከገባ በኃላ ብዙም ሰው ጥንቃቄ እያደረገ ስላልነበረ የተወሰነ ቀን ሜዳ አልወጣሁም። በሳምንት ሦስት ጊዜ ቤት ውስጥ ነበር የምንቀሳቀሰው። ከዛ በኃላ ግን ጥንቃቄ በተሞላ መልኩ ወደ ሜዳ እየወጣን ከወንዶች ጋር እሰራለሁ። ቤት ውስጥ ደግሞ በሳምንት ሁለቴ እንቀሳቀሳለሁ፡፡ ከልምምድ ባለፈ ደግሞ ፊልም በማየት ነው የማሳልፈው፡፡

በግልሽ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍሽበት ዓመት መቼ ነው ?

በግሌ ጥሩ ጊዜ የነበረኝ 2012 ኮሮና ሳይገባ በፊት ነበር። ወረርሺኙ ባይገባ ኖሮ ለሀገሬም ለቡድኔም አንድ ነገር መስራት የምችልበት ጊዜዬ ነበር። ምክንያቱም ጥሩ ነበርኩ። ፡፡

እግርኳስ ተጫዋች ባትሆኚ በዚህ ሰዓት ምን ሙያ ላይ እናገኘሽ ነበር ?

እግርኳስ ባልጫወት ቤተሰቦቼ ሁሉም ነጋዴዎች ስለሆኑ ነጋዴ እሆን ነበር። አሁንም ድረስ በትምህርቴም መካከለኛ ከሚባሉት ነኝ። በትምህርት እንድቀጥል ጫና ቢያደርጉብኝም ግን ካደኩበት አንፃር ወደ ንግዱ አዘንብል ነበር።

አብሬያት ብጣመር እና ብጫወት እመርጣለሁ ብለሽ ምትጠቅሻት ተጫዋች አለች ?

አዎ! አብሪያት መጫወትን የምፈልገው ከሽታዬ ሲሳይ ጋር ነው፡፡ በቃ ሜዳ ላይ የምታደርጋቸው ነገሮች፣ ፍጥነቷ፣ ኳስ አመታቷ፣ ጎል የምታስቆጥርበትን መንገድ ስለማደንቅላት ከእርሷ ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል፡፡ አንድ ቦታ ሳይሆን ብዙ ቦታንም ሸፍና ስለምትጫወት በጣም በጣም አደንቃታለሁ፡፡

በተቃራኒው ስትገጥሚያት የምትከብድሽ ተጫዋች ትኖር ይሆን ?

በተቃራኒው ስገጥማት የከበደችኝ የንግድ ባንኳ የመሐል ተከላካይ ገነሜ ነች። ከሷ ውጪ ሌላ የለም፡፡

በሀገራችን ከሚገኙ ያንቺ ምርጥ ተጫዋች ማነች ?

ሎዛ አበራ! ጎበዝ ነች። በጣም ነው የማደንቃት። ኳስን በየትኛውም አቅጣጫ እንዴት እንደምትመታ እንዴት እንደምታገባ ከርቀት የምታደርገው አመታትን ስለማደንቅላት እንዲሁም ቦታ አያያዟን ስለምወድላት በእነዚህ ምክንያቶች ለእኔ ጥሩ ተጫዋች ብዬ የማስባት እሷ ነች፡፡

ከአሰልጣኞች ?

ከአሰልጣኝ ለእኔ ምርጡ አሁን ከሀዋሳ ጋር የተለያየው ዮሴፍ ገብረወልድን ነው፡፡ እርሱን በጣም ነው የማደንቀው፡፡

በእግርኳሱ የተደሰትሽበት ጊዜ መቼ ነው ?

በጣም የተደሰትኩበት አጋጣሚ 2008 ወደ ሀዋሳ የሄድኩበት ዓመት ነበር። ብዙም ስኬታማ አልነበርኩም። እኔም አዲስ፤ አብዛኛዎቹ ደግሞ ሲኒየር ተጫዋቾች ስለነበሩ ከባድ ነበር። ወላይታ ድቻ እያለው ሙሉ ጨዋታ ነበር የምጫወተው። ሀዋሳ ስመጣ ግን በመቀመጥም በመጫወትም ስላሳለፍኩ የተደሰትኩበትም የተከፋሁበትም ወቅት ያኔ ነበር፡፡

እግርኳስ ተጫዋች መቼስ ገጠመኝ አይጠፋውም። እስቲ አንዱን ገጠመኝ ንገሪን ?

ገጠመኝ ብዬ የማስበው 2009 አዳማ ላይ ደደቢትን አሸነፈን ዋንጫ የበላንበትን ነው። ጨዋታ የዛን አመት ውል ጨርሼ ስለነበር ወደ ሌላ ቦታ የመሄድ ፍላጎት ነበረኝ። ያን ጨዋታ ተቀይሬ ነበር የገባሁት። ገብቼ ጨዋታውን ቀይራለሁ የሚል ውስጤ ያምናል። ግን ደደቢቶች ጥሩ እየተጫወቱ ስለነበር ከዛ እኔ ገብቼ በእኔ ጎል እናሸንፋለን የሚል ብዬ አላሰብኩም። ገብቼ ያንን ጎል ካገባሁ በኃላ በቃ በጣም ነበር የተደሰትኩት። ስለዚህ የማልረሳት ጎል ስለሆነች ያን ገጠመኝ መቼም አልረሳሁም፡፡

በእግርኳሱ ውስጥ ካሉ ግለሰቦች የቅርብ የሀሳብሽ ተጋሪ ማናት ?

አሁን አብራኝ እየተጫወተች ያለችው ተከላካይዋ ትዝታ ኃይለሚካኤል ቅርቤ ነች። አሉ ብዙ ናቸው የቅርብ ጓደኞቼ ግን በብዛት በክፉም በደጉም የምንገናኘው ከትዝታ ጋር ነው፡፡

ስለ ግላዊ ባህሪሽ አጫውቺኝ ምን የተለየ ባህሪ አለሽ ?

ምንም የተለየ ባህሪ የለኝም። ወጣ ያለ ባህሪም የለኝም። ከስራዬ ውጪ ቤት ነኝ መዞርም መውጣትም ብዙ አይመቸኝም። ከልምምድም ከምግብ ቤት መልስ ቤት ነኝ። ብዙ ጊዜ ፊልም ነው የማየው። ከዛ ውጪ መፅሐፎችን አነባለሁ። የተለየው ግን ወጥቶ መዞር አይመቸኝም። መዝናናትም አይመቸኝም። ማህበራዊ ኑሮ ካለ ከጓደኞቼ ጋር እሄዳለሁ። ከዛ ውጪ ሌላ ባህሪዎች የሉኝም ፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!