“ከክለባችን ጋር የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስም መነሳቱ ለእኛም አልገባንም” አቶ ዓለማየሁ ምንዳ – የሰበታ ከተማ ሥራ አስኪያጅ

የአሰልጣኝ ቅጥር ማስታወቂያ ያወጣው ሰበታ ከተማ ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር ግንኘነት እንዳልፈጠረ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ገለሰጸዋል።

ሰበታ ከተማ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ለዘንድሮው የ2013 የውድድር ዓመት ቢዘጋጅም አሰልጣኙ የአንድ ዓመት ውል እየቀራቸው የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው በመሾማቸው ከክለቡ ለመለያየት ተገደዋል። ክለቡ ከአሰልጣኙ መልቀቅ በኃላ የተለያዩ አማራጮችን ለመመልከት የሞከረ ሲሆን ለአብነትም አብርሀም መብራቱን ለመቅጠር ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። በትናንትናው ዕለትም ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የአሰልጣኝ ቅጥር ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ክለቡ ማስታወቂያውን ከማውጣቱ ቀደም ባሉት ቀናት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና፣ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ እና አሸናፊ በቀለን ሊቀጥር ተቃርቧል የሚሉ መረጃዎች ሲነሱ የቆዩ ሲሆን በተለይ አዳማ ከተማን ለቀው ወደ ሀድያ ሆሳዕና ያመሩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ “ክለቡን ለመያዝ ተቃርበዋል፤ ማስታወቂያው እንዲሁ ለማውጣት ያህል የወጣ ነው፡፡” በሚል ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል። እኛም በዚህ ጉዳይ ላይ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ምንዳን አናግረን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

“ማንም የሚለውን እኛ አንሰማም፤ የራሳችንን ሥራ እየሰራን ነው፡፡ እኛ ከአሸናፊ በቀለ ጋር የተያያዘ ምንም መረጃ ለማንም አልሰጠንም። አሰልጣኙም ከእኛ ጋር ግንኙነት አላደረገም። የክለቡ እና አመራሮችን ስም ለማጉደፍ ካልሆነ በስተቀር ከክለባችን ጋር የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስም መነሳቱ ለእኛም አልገባንም።

“ማስታወቂያ አውጥተናል። በወጣው ማስታወቂያ መሠረት ማንኛውም አሰልጣኝ መጥቶ ሲመዘገብ እናወዳድራለን እንጂ ከዛ ውጪ ምንም የሚሠራ ሥራ የለም። የክለቡ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በማስታወቂያ አወዳድሩ ብሎ ያስቀመጠልን አቅጣጫ አለ፤ እሱንም እያደረግን ነው፡፡ ማንም ስለፈለገ የሚሆን ነገር የለም። ማስታወቂያው ሲያልቅ ሁሉንም በይፋ ማየቱ ይሻላል። በውጤት የተሻለውን አሰልጣኝ እንቀጥራለን፡፡ ማንኛውም መስፈርቱን አሟላለሁ የሚል አሰልጣኝም መወዳደር ይችላል፡፡”

ክለቡ ትናንት ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 3 ድረስ አሰልጣኞችን ለመቅጠር ይፋዊ ማስታወቂያን ያወጣ ቢሆንም ትናንት እና ዛሬ ሲቪውን ያስገባ አሰልጣኝ እንደሌለ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!