“ወደ አፍሪካ ዋንጫ የምናደርገው ጉዞ የሚወሰነው ከኢትዮጵያ ጋር በምናደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ነው” – ዣን ሚሸል ካቫሊ

አዲሱ የኒጀር ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዣን ሚሸል ካቫሊ የቡድናቸው የአፍሪካ ዋንጫ ተስፋ በኢትዮጵያ የደርሶ መልስ ጨዋታ እንደሚወሰን ተናግረዋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት ለተዘዋወረው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር እና ኮትዲቯር ጋር የተደለደለችው ኒጀር ከሳምንታት በፊት አዲሱን የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዣን ሚሸል ካቫሊን በይፋ የቡድኗ ዋና አሠልጣኝ አድርጋ መሾሟ ይታወሳል። የ63 ዓመቱ ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ካቫሊም ቡድኑን ለ2022 የዓለም ዋንጫ እና የአፍሪካ ዋንጫ ለማብቃት ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

በምድብ 11 ተደልድለው ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሽንፈትን ያስተናገዱት ኒጀሮች ወደ ካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በህዳር ወር የመጀመሪያ ቀናት ከኢትዮጵያ ጋር ያለባቸውን የደርሶ መልስ ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተዋል። የቀድሞ የሊል እንዲሁም አልጄሪያ አሠልጣኝ የነበሩት ዣን ሚሸል ካቫሊም አዲሱ ስራቸውን ከቻድ እና ሴራሊዮን ጋር ባደረጉት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ጀምረው ጥሩ ውጤትን አስመዝግበዋል። አሠልጣኙ ከፊታቸው ያለባቸውን የኢትዮጵያ ጨዋታን ለማሸነፍ ጠንክረው እየሰሩ እንደሚገኙም ለፊፋ ድረ-ገፅ በሰጡት አስተያየት አስታውቀዋል።

“ቡድናችን ሁለት ወሳኝ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ተሸንፏል። ይህ ደግሞ ውድድሩ ላይ እንድንሳተፍ ያለንን እድል ያጠባል። ግን እኛ እድላችን ጠባብ ነው ብለት አንቀመጥም። ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች ጠንክረን እየሰራን ነው። ወደ አፍሪካ ዋንጫ የምናደርገው ጉዞ የሚወሰነው በቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች (ከኢትዮጵያ ጋር) ነው።

“ወደ ኒጀር ከመምጣቴ በፊት የተጫዋቾቹን ሁኔታ ስከታተል ነበር። አሁን ላይ ሁለት ተጫዋቾች ጉዳት አስተናግደውብናል። ግን አጠቃላይ ቡድኑ በጥሩ የማሸነፍ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። በሦስት ቀን ልዩነት ያደረግናቸውን ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች አሸንፈናል። ስለዚህ ቡድኔ ጠንካራ ደረጃ ላይ ይገኛል።

“አላማችን ኒጀር ለአፍሪካ ዋንጫ እንድትበቃ ብቻ አይደለም። ለ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይም ጠንካራ ፉክክርን የሚያደርግ ቡድን መገንባት እንጂ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!