“የተሰጠኝን ትልቅ ኃላፊነት ለመወጣት እሠራለው” የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል

ለ2013 የውድድር ዘመን በቅርቡ ቅድመ ዝግጅቱን የሚጀምረው አዳማ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ እንደሾመ ታውቋል።

በ2012 በክረምቱ ወራት ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር የተለያየው አዳማ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ እንደማይሾምና በምክትል አሰልጣኞቹ እየተመራ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት እንደሚጀምር መዘገባችን ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክለቡ ቦርድ አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ፊቱን አዙሮ አሰልጣኝ ዻውሎስ ጌታቸው እና አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን የመጨረሻ እጩ ሆነው እንደቀረቡ በተለያዩ መንገዶች ሲሰሙ ቆይተዋል። ሆኖም አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የክለቡ የበላይ አመራሮች ባደረጉት ስብሰባ በማቋረጥ ያለፉትን ሰባት ዓመታት አዳማ ከተማን በምክትል አሰልጣኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት አስቻለው ኃይለሚካኤልን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙ ሲገለፅ በምክትል አሰልጣኝነት ደጉ ዱባሞን ማድረጉን ለማረጋገጥ ችለናል።

አሰልጣኝ አስቻለው ከዚህ ቀደም በተጫዋችነት ዘመናቸው አዳማ ከተማ በ1992 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲያድግ ከነበሩ ቁልፍ ተጫዋቾች አንዱ ከመሆናቸው ባሻገር በ2006 ምክትል አሰልጣኝ በመሆን አዳማ ከተማን ከወረደበት ዳግመኛ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ቡድን አካል ነበሩ። ያለፉትን ሰባት ዓመታት በምክትል አሰልጣኝነት ቆይታ ካደረጉ በኃላ ዘንድሮ ዋና አሰልጣኝ በመሆን የሚያገለግሉ ይሆናል። አሰልጣኙ የአዳማ አዲስ አሰልጣኝ በመሆን መሾማቸውን ተከትሎ ስለ ቀጣይ እቅዳቸው እና ተያያዥ ጉዳዮች ተከታይ ሀሳባቸውን በአጭሩ እንዲህ በማለት ተናግረዋል።

” በመጀመርያ የክለቡን አመራሮችን አመሰግናለሁ። አዳማን ከተጫዋችነት ጀምሮ እስከ ምክትል አሰልጣኝነት ረጅም ዓመት አገልግያለው። ይህ ለኔ የተሰጠኝን ኃላፊነት ትልቅ ነው። የተሰጠኝንም ኃላፊነት ለመወጣት ጠንክሬ እሰራለው። ክለቡ ባስቀመጠልን አቅም መሠረት ያስፈርምናቸው፣ ውል ያላቸው እና ውላቸውን ያራዘሙ የቡድኑ ነባር ተጫዋቾችን እና ከታዳጊ ቡድን የምናሳድጋቸውን ልጆች አቀናጅተን አዳማ በሚታወቅበት አጨዋወት ጥሩ ተፎካካሪ የሆነ ቡድን ይዘን እንቀርባለን። በቅርብ ቀናት ውስጥም ቅድመ ዝግጅታችንን የምንጀምር ይሆናል።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!