ኢትዮጵያ 1-3 ዛምቢያ | የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አስተያየት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሦስት ቀን ቆይታ በኋላ ከዛምቢያ አቻው ጋር ያደረገውን ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታ 3-1 በሆነ ውጤት ተሽንፏል። የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ከጨዋታው በኋላ ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።


አጠቃላይ ስለጨዋታው ምን አሰተያየት አለዎት ?

ዕቅዳችን የነበረው ሁሉንም ለጨዋታው ብቁ የሆኑ ተጫዋቾችን መጠቀም ነበር። ለሐሙሱ ጨዋታ መድረስ ያልቻሉ ተጫዋቾችንም ጭምር ተጠቅመናል። በመሆኑም ጨዋታውን ቡድናችን ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ተጠቅምንበታል።

ቡድኑ የተጋጣሚን ጫና መቋቀም ተስኖት ነበር ፤ በሁለት ተከላካይ አማካዮች የመጠቀም ዕቅድ ይኗራችኋል ? በተደጋጋሚ ስለሚታዩ ቀላል ስህተቶችስ ምን ይላሉ ?

የጨዋታው ዋና ዓላማ ውጤት ማግኘት ሳይሆን አቋማችንን መገምገሙ ላይ ነው። በመሆኑም በጨዋታው ብዙ ተምረንበታል እንጂ ተነሳሽነታችንን አይቀንሰውም።

የተጠቀምናቸው የጨዋታ ዘዴዎች ተመሳሳይ ነበሩ ፤ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ። ትልቁ ድክመታችን የነበረው ኳሱን ለማቀበል ወይም ለማንቀሳቀስ ሌሎች አማራጮች እያሉን በተመሳሳይ መንገድ መቀጠላችን ላይ ነው። ሌሎች የቅብብል አማራጮችን መፍጠር እየቻልን በቀላሉ ወዳዘጋጁልን ወጥመድ እንገባ ነበር።

ሁለት ተከላካይ አማካዮችን መጠቀም የተለየ ልዩነት አይፈጥርም። ዋናው ነገር ኳስን የምንቆጣጠርበት እና ቅብብሎችን የምንከውንበት መንገድ ነው። በዚህ ረገድ በጣም ደካማ ነበርን። ዛምቢያዎችም ይህን ደካማ ጎናችንን በደንብ ተጠቅመውበታል።

ስለመከላከል ስህተቶችስ ምን ይላሉ ?

የመከላከል ስራ እንደሙዚቃ ኦርኬስትራ በቡድን የሚከወን ነው። ኳስ ስንነጠቅ በቶሎ ወደ መከላከል ቅርፃችን መመለስ ይኖርብናል። ክፍተቶቹ የሚጠበቁ ናቸው። ክለብ ቢሆን በዚህ ፍጥነት መጫወታችን የማይጠበቅ ሊሆን ይችላል። በተናጠልም ሆነ በቡድን ችግሮች አሉብን።

የዛምቢያ ቡድን አቀራረብ የወዳጅነት ጨዋታ ዓይነት አልነበረም ፤ በእርሶ ቡድን ውስጥ ይህን ስሜት መመልከት ይፈልጋሉ ?

እንደማስበው ከሆነ ከጨዋታው በፊትም ሆነ በኋላ የተጫዋቾቻችን ተነሳሽነት ጥሩ ነበር። ተጫዋቾቼ ለጨዋታው ሙሉ ትኩረት እንደሰጠ አምናለሁ ፤ ሜዳ ላይ ግን ያ ነገር ሙሉ በሙሉ አልታየም። በዕረፍት ሰዓትም ጠይቂያቸው የተረዳሁት ይህንኑ ነው።

የወዳጅነት ጨዋታዎቹ የመጨረሻዎቹን ተጫዋቾች ለመለየት ምን ያህል ይረዳሉ ?

ጨዋታዎቹ እንደጠቀሙን አስባለሁ። ዋናው ዓላማችንም ወደ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ የምንወስዳቸውን ተጫዋቾች መለየቱ ላይ ነው። እያንዳንዱን ተጫዋች ሙሉ 90 ደቂቃ ማየት ብንችል ጥሩ ነበር። ሽመልስን ጨምሮ 27 ተጫዋቾችን በመያዝ ለቀጣዩ ጨዋታ ዝግጁ እንሆናለን። ጉዳት ወይም ኮቪድ ሊገጥመንም ይችላል። ሆኖም ወደ ኒጀር ከማቅናታችን በፊት የመጨረሻዎቹን 23 ተጫዋቾች እንለያለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!