የሴቶች ገፅ | ቆይታ ከመዲና ዐወል ጋር…

በዛሬው የሴቶች ገፅ መስናዷችን ከመከላከያዋ አጥቂ መዲና ዐወል ጋር በአጫጭር ጥያቄዎች ያደረግነውን ቆይታ እናስነብባችኋለን።

የካዛንችዝ ልጅ ናት ፤ እስካሁንም ከቤተሰቦቿ ጋር ባደገችበት ሠፈር እየኖረች ትገኛለች። በአካባቢዋ በኳስ ተጫዋችነት ዓረአያ ይሆናት ሰው ባይኖርም የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለች የወስዳት የእግርኳስ ፍቅር እስከ ክለብ እና ብሔራዊ ቡድን አድርሷታል። በሰፈሯ ከወንዶች ጋር በመጫወት ጀምራ በትንሳኤ ብርሀን እና ምስራቅ ጎህ የተማሪነት ጊዜዋ ከኳስ ጋር ይበልጥ ተወዳጅታ በወረዳ እና ክፍለከተማ ውድድሮች ራሷን በማሳየት የዛሬ ህይወቷን መንገድ ጀምራለች። በኮፓ ኮካ ኮላ ተሳትፎዋ ከአፏ በማይጠፋው አሰልጣኝ ዮናስ ወርቁ በእሷ አጠራር ‘ዮዬ’ እይታ ውስጥ ከገባች በኋላ አሰልጣኙ ቤተሰቦቿን ለማሳመን ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ታግዛ የቅድስተ ማሪያምን ቡድን በመቀላቀል ወደ ክለብ እግርኳስ ብቅ ብላለች።

በተክለሰውነቷ አነስ ያለች ብትሆንም ባለክህሎት ከሚባሉ ተጨዋቾች መካከል ትጠቀሳለች። እይታን ከሚስበው ተፈጥሯዊው የቴክኒክ ብቃቷ ባሻገር በግብ ፊት ጥሩ ጨራሽ በመሆን በወጥነት ብቃቷን ስታስመለክተን ቆይታለች። እጅግ ጎልታ ከወጣችበት የቅድስተ ማርያም ጊዜዋ በኋላ 2010 ላይ አሁን የምትገኝበት መከላከያን ተቀላቅላ በግብ አስቆጣሪነቷ ቀጥላለች። ከዚህ በተጨማሪ በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ እና ብርሀኑ ግዛው ጥሪ ከደረሳት ከ2006 ጀምሮ ሀገሯን የማገልገል ዕድልንም አግኝታለች። ጭንቀታቸው በሜዳ ላይ ለሚያሳዩት እንቅስቃሴ እንጂ ለቃለ- መጠይቅ እምብዛም ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል የምትጠቀሰው መከላከያዋ አጥቂ መዲና ዐወል የዛሬዋ የሴቶች አምድ ዕንግዳችን ናት።

ኮቪድ-19 ወደ ሀገራችን ከገባ እና ውድድሮች ከተቋረጡ በኋላ የነበረው ጊዜ እንዴት ነበር ?
ከምለው በላይ በጣም ከባድ ጊዜ ነበር። ከዚህ ቀደም ከባድ ጉዳት ገጥሞኝ ወይም በሌላ ምክንያት ከእግርኳሱ ይህን ያህል ለረጅም ጊዜ የራቅኩበት ወቅት አልነበረም። ስሜቱን ስለማለውቀውም ሊሆን ይችላል ጊዜው በጣም ነው የረዘመብኝ።

ታድያ ይህን ጊዜ በምን አሳለፍሽው ?

ብዙውን ጊዜ ከቤተሰቦቼ ጋር ነው ያስለፍኩት ፤ እምብዛም ከቤት አልወጣም ነበር። በይበልጥ ቤት ውስጥ ልምምዶችን በማድረግ ፣ ጨዋታዎችን በመመልከት እና በማንበብ ነው ያሳለፍኩት።

አንዳንዴ ኳስ ተጫዋቾች መጫወቱን እንጂ መመልከቱን አይወዱትም ፤ እዚህ ውስጥ አትካተቺም ማለት ነው ?

አዎ ለእኛ ኳስ ከማየት የተሻለ ነገር ይገኛል ብዬ አምናለሁ። እናም የውጪም የሀገር ውስጥም ጨዋታዎችን እመለከታለሁ።

ታዲያ እንዲህ የረዘመብሽ የኮቪድ ጊዜ ምን አዲስ ልምድ ይዞ መጣ ?

እንቅልፍ ! (ሣቅ) በፊት ለልምምድም ለመድረስ በለሊት ነበር የምነሳው። በኮቪድ ጊዜ ግን እንቅልፍ በጣም መተኛት ጀምሪያለሁ።

ዛሬ ‘ኮሮና ጠፋ!’ ቢባል ምን ታደርጊያለሽ ?

ይህ ለኳስ ተጫዋች ምንም ጥያቄ የለውም። ቀጥታ የምድሄደው ወደ ሜዳ ነው ፤ ከተጫወትኩ ስለቆየሁም ኳስ ነው የምጫወተው። በእሱ ነው ደስተኛ የምሆነው።

ኳስ ተጫዋች ባትሆኚ ምን ትሆኚ ነበር ?

እግርኳስ ተጫዋችነት በተፈጥሮ የተሰጠኝ እንጂ ሰርቼ ያመጣሁት ነገር አይደለም። እና ኳስ ባልጫወት ብዬ አንድም ቀን አስቤው አላውቅም።

ኳስን መጫወት ካቆምሽ በኋላስ ?

ዕድሜዬ ገና ነው ፣ ብዙ የመጫወትበትም ጊዜ አለኝ እና እሱን እስካሁን ብዙም አላአላሰብኩበትም።

ጥሩ ጊዜ ያሳለፍሽበት ዓመት ?

2008 ላይ በ20 ዓመት ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያሳለፍኩት ጊዜ የማይረሳኝ ነው። ቡድኑ ጠንካራ እና ለዓለም ከ20 ዓመት ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ የተቃረበ ነበር።

ራስሽን እንደተጫዋች ስትመለከቺ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችሽ ምንድን ናቸው ?

እንደተጫዋች ምሉዕ ነኝ ብዬ አላስብም። ብዙ የሚቀሩኝ ነገሮች አሉ። በይበልጥ ደግሞ ብዙ መልካም ነገሮችም አሉኝ።

ከአጀማመርሽም አንፃር ‘ያሰብኩበት ቦታ ላይ ደርሻለው’ ብለሽ ታስቢያለሽ ?

በጣም ከባድ ነው። በእርግጥ ትናንት ከነበርኩበት ነገር አንፃር የተሻለ ደረጃ ላይ ነኝ ብዬ አስባለው። በተለይ አባቴ ብዬ የምጠራው አሰልጣኝ ዮናስ ወርቁ የለፋብኝን ያህል ደርሻለው ማለት አልችልም። እሱ መዲና ዐወልን ሊያገኛት ያሚፈልገው ቦታ ላይ አይደለሁም። ከትናንት ማንነቴ ተሽያለው መድረስ የነበረብኝ ቦታ ላይ ግን አይደለሁም ብል የይቀለኛል።

ሜዳ ላይ አብረሻት በጥምረት መጫወት የምትፈልጊያት ተጫዋች ?

አብዛኞቹ ተጫዋቾች ጋር በብሔራዊ ቡድንም አብሬ የመጫወት ዕድሉ ስለነበረኝ ፤ አብሪያት ብጫወት ብዬ የምጓጓላት ተጫዋች አትኖርም።

በተቃራኒ ስትገጥሚያት የምትከብድሽ ተጫዋች ?

ማንም የለም!

የምታደንቂያቸው ተጫዋቾች ?

አሁን ላይ በጉዳት ብዙ ባናያትም የዙለይካ ጁሀድ አድናቂ ነኝ። ሽታዬ ሲሳይ ፣ ረሂማ ዘርጋው ፣ ብርቱካን ገብረክርስቶስ እና አሁን ላይ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያዊያን አቅም እንዳለን ላሳየችው ሎዛ አበራም ትልቅ ክብር አለኝ።

ከአሰልጣኞችስ ?

ምንም ጥያቄ የለውም። ከአባትም በላይ የሆነው እና ለእኔ ብዙ ነገር የሆነልኝ አሰልጣኝ ዮናስ ወርቁ ነው። እሱ ለእኔ በጣም ይለይብኛል። እኔ ዮዬ ብዬ የምጠራው እና እንደአባቴ ሄኖ እዚህ ያደረሰኝ ዮናስ ወርቁን እጅግ አድርጌ ማመስገን እፈልጋለሁ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!