የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የተደበቀ ተስጥኦ

የወቅቱ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከእግርኳስ ተጫዋችነት፣ ከአሰልጣኝነት ብቃታቸው ባሻገር የተለየ ሌላ ተስጥኦ እንዳላቸው ያውቃሉ?

እግርኳስን ተወልደው ባደጉበት አዳማ ከተማ ትግል ፍሬ ጀምረዋል። በክለብ ደረጃ ወንጂ ፣ ሙገር ፣ ኪራይቤት፣ አየር መንገድ እና ጉምሩክ ተጫውቶ አሳልፈው በ1995 እግርኳስን ካቆሙ በኃላ ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ በመቀላቀል በሠፈር ውስጥ የጀመረው የአሰልጣኝነት ጉዟቸው በፖሊስ ቡድን ቀጥሎ በአዳማ ከተማ በም/አሰልጣኝነት እና በዋና አሰልጣኝነት አገልግለዋል። በኃላም በኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ እና በሰበታ ከተማ ስኬታማ ቆይታ በማድረግ በቅርቡ የኢትዮጵያ ዋና ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ከሚያውቀው የተጫዋችነት እና የአሰልጣኝነቱ ህይወት በተጨማሪ ጥሩ ድምፃዊ፣ የክራር መሣርያ ተጫዋች እና የስዕል ጥበብ ባለሙያ እንደሆኑ ያውቃሉ ? በዚህ ዙርያ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ቆይታ አድርገናል።

” ክራር መጫወት የጀመርኩት አዳማ (ናዝሬት) እያለሁ ነው። አንድ ከበደ የሚባል ልጅ ነበር። ከርቸሌ እያለ ክራር መጫወት ያገኘው እውቀት ነው። እርሱ ሲጫወት ልጅ ሆኜ እርሱን በመመልከት በስሜት ያለ አስተማሪ የለመድኩት መሣርያ ነው። በኃላም በተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉ ክራር ይዤ በልምምድ ውጭ ጊዜ ሳገኝ፣ ለጫዋታ ወደ ተለያዩ ክልሎች ጉዞ ስናደርግ መኪና ላይ ክራር እጫወታለው። በድምፄም አንጎራጉር ነበር። (ሳቅ) ከተወሰነ ጊዜ በኃላ በስልጠናው ላይ ትኩረቴን ሳደርግ አልፎ አልፎ ቤቴ እጫወታለው። ባይገርምህ አንዲት ፈረንጅ አስተምራኝ የስዕል ጥበብ ላይ ያለኝ ታለንት የሚገርም ነው። ቤት ብትመጣ በተወጠረ ሸራ ላይ የተሳሉ የተለያዩ ስዕሎች አታጣም። ይህን መልመዴ (ማወቄ) በእግርኳስ ውስጥ የሚፈጠሩ ጫናዎችን ለመርሳት ጠቀሜታ አለው። ትኩረት ሰጥተን አለማየታችን እንጂ እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ተስዕጦ አለው። እኔ በአካባቢዬ ያለውን ነገር ተመልክቼ ነው ስዕል መሳል፣ ክራር መጫወት የቻልኩት። ማንም ሰው በልጅነቱ አካባቢው እንደሰጠው ነው የሚሆነው። ጋራዥ ከዋለ መካኒክ እንደሚሆነው፤ እኔም በዚህ መልኩ ተስቤ ነው ወደዚህ ሙያ የገባሁት። እግርኳስ ተጫዋች ወይም አሰልጣኝ ባልሆን ወደ ዚህ ሙያ የመግባት ዕድሉ ይኖረኝ ነበር።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!