​ሶከር ሜዲካል | የአዕምሮ መዛል በእግር ኳስ [ክፍል 2]

ከዚህ በፊት በነበረው የሶከር ሜዲካል ፅሁፋችን በእግር ኳስ ተጫዋቾች የአዕምሮ መዛል መንስኤዎች መካከል የሆነውን መዋቅራዊ ተፅዕኖ ተመልክተናል። በዚህኛው ፅሁፍ ደግሞ ከስነ ልባና ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጫናዎችን እንመለከታለን። አትሌቲክ በተሰኘው የእግር ኳስ ድረ ገፅ የሰፈረውን ” we need to talk about mental burnout in football.” እንደ ግብዐት ተጠቅመናል። 

ሥነ ልቦናዊ ጫናዎች በሚኖሩበት ጊዜ ተጫዋቾች በፍጥነት ከጉዳት የማገገም ብቃታቸው የሚቀንስ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ነገሮችን በተቀላጠፈ መልኩ የማድረግ ችሎታቸው እከል የሚገጥመው ይሆናል። የስፖርት ሳይኮሎጂስት የሆነው ዳን አብራሃምስ እንደሚናገረው ከሆነም ተጫዋቾች ጭንቀት ወይንም ውጥረት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ያላቸውን እምቅ ኃይል አውጥተው መጫወት አይችሉም። 

ከላይ በጠቀስነው ፅሁፍ ሥር ሌላ እንደምሳሌ የቀረበ ጉዳይ ቢኖር በዘመናዊ እግር ኳስ ተስተውሎ እንደሚታየው አሰልጣኞች ሊባረሩ ጫፍ በሚደርሱበት ወቅት የአንድ ወይም ሁለት ጨዋታዎች ፋታ ይሰጠዋል። በእነዚህ በቀሩ ግጥሚያ ወቅት ተጫዋቾች ለአሰልጣኙ ለመጫወት ቢሞክሩ እንኳን ያለባቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና አቅማቸውን አውጥተው ማሳየት እንዲችሉ አይፈቅድላቸውም። በግልፅ መረዳት እንደምንችለው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከሥነልቦናዊ ዝግጅት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ተጓዳኝነት አለው። 

ባለንበት የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ደጋፊዎችም ሆነ ጋዜጠኞች በተጋነነ በሚባል መልኩ ተጫዋቾችን የመተቸት እና የማብጠልጠል ልምድ በስፋት እየታየ ይገኛል። ይህን የከፋ የሚያደረገው ደግሞ አብዛኛዎቹ ተቃውሞዎች ውጤትን ብቻ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸው ነው። እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ተቺዎች ተጫዋቾች የሚያልፉበትን ሥነ ልቦናዊ ጫና እና ከአቋማቸው መውረድ ጋር የተያያዙ አዕምሯዊ ምክንያቶችን ለመረዳት ፈቃደኛ አይደሉም። ይህም ብዙ ታዋቂ ተጫዋቾች በቅርብ ዓመታት ስለእነዚህ ጉዳዮች እንዲያወሩ ምክንያት ሆኗል። 

እ.ኤ.አ በ2010 በከፍተኛ ድባቴ (Depression) ተጠቅቶ የነበረውና በዛው ዓመት ህይወቱን ያጠፋው ሮበርት ኤንከ ለብዙዎች ትልቅ ሀዘንን ፣ ፀፀትን እና ትምህርትን ጥሎ አልፏል። ምንም እንኳን ዝነኛ ቢሆኑም እና ከፍ ያለ ገንዘብ ቢያገኙም እግር ኳስ ተጫዋቾች እንደማንኛችንም ሰው ናቸው። በሁለት እና በሦስት ቀናት እየተጫወቱ ለምን 100% ብቃት አያሳዩም ብሎ ማብጥልጠል እና አልፎም ፀያፍ የሆኑ ቃላትን መጠቀም አግባብነት የለውም። በቅርቡም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤት ባጣባቸው ጨዋታዎች ወቅት ደጋፊ ነን ከሚሉ ሰዎች ይሰነዘሩ የነበሩ ኃይለ ቃሎች እጅጉን አሳፋሪ እና አስነዋሪ ነበሩ። 

ያለ አዕምሮ ጤና ሙሉ ጤና የለም!

© ሶከር ኢትዮጵያ