ሶከር መጻሕፍት | መሠረታዊው ሐሳብ (ምዕራፍ ሁለት – ክፍል ሁለት)

THE PHILOSOPHY OF FOOTBALL፡ UNDER THE SHADOWS OF MARCELO BIELSA” ለአራት ዓመታት ያህል ከፍተኛ ጥናትና ምርምር የተደረገበት ሥራ ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙረያ ቡና ፉት እየተባለ ከተደረጉ ምሁራዊ ውይይቶች አንስቶ ማርሴሎ ቢዬልሳን የተመለከቱ በርካታ ቃለ-መጠይቆችን መሥራት ጠይቋል፡፡ የእግርኳስ ሐሳባውያኑን ፍለጋ የተደረጉ የውጭ ጉዞዎችና አያሌ መጻሕፍትን መዳሰስም የዚህ መጽሐፍ ግብዓቶች ሆነዋል፡፡ ጸሃፊው በዚህኛው ምዕራፍ አርጀንቲናዊው የእግርኳስ ታክቲክ ባለሟል ከሌሎች በተለየ ኅልዮታዊ ልህቀት ያገኙበትን ምስጢራት ለማብራራት ይጥራል፡፡

” እግርኳስ በተጫዋቾች የአንድ-ለ-አንድ ፍልሚያ ይካሄዳል፡፡” የሚል ተለምዷዊ አረዳድ ነበር፡፡ ይህ ሐሳብ በሮቤርቶ ማርቲኔዝ እና በሌሎችም አሰልጣኞች ፍልስፍና ውስጥ ሲንጸባረቅ ተስተውሏል፡፡ አይርተን ሳርጉሲንግ ” እግርኳስ በሜዳ ላይ የሚገኙ የአንድ ቡድን ሁለት ተጫዋቾች በተጋጣሚ ቡድን አንድ ተጫዋች ላይ በሚያሳድሩት ጫና የሚካሄድና በተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ የሚወሰን ጨዋታ ነው፡፡” ሲል ያቀረበው መነሻም የቀደመውን ሐሳብ የሚያጠናክርለት ድምዳሜ ነው፡፡
አይርተን አንድ የአግድሞሽ ዝርግ መስመር አስምሮ ሦስት ተጫዋቾችን ደረደረበት፡፡ ሌላ አቋራጭ መስመር ስሎም በጫፎቹ ላይ ሁለት ተጫዋቾች አስቀመጠ፡፡ ከዚያም ማስረዳቱን ቀጠለ፡፡ ” ሁለት ተጫዋቾች ከተጋጣሚዎቻቸው ሶስት ተጫዋቾች ጋር የሚከውኑትን ተመልከት!” ሁኔታው ተመሳሳይ መሆኑን አስተውል፡፡ አሁንም ቢሆን ዞረን ዞረን የምደርሰው ሁለት ተጫዋቾች በአንድ የባላጋራ ቡድን ተጫዋች ላይ የሚያሳርፉት ጫና ላይ ነው፡፡”
አይርተን ሐሳቡን በዝርዝር መተንተኑን ቀጠለ፡፡ በአንድ መስመር ከተደረደሩት ሶስት ተጫዋቾች አንደኛው ብቻ በጨዋታው የቅርብ እንቅስቃሴ ተካፋይ መሆኑን ይገልጻል፡፡ የተጫዋች <A> ዓላማ ለተጫዋች <B> ኳሱን በማቀበል በሜዳው ቁመት ወደ ተጋጣሚ ክልል ሰብሮ መግባት እንደሆነ ያሳያል፡፡ ከታች በቀረበው ምስል የኳስ አቀባዩ እና ተቀባዩ ሐሳብ በሜዳው ቁመት በሚደረገው ቅብብል ላይ የተቃኘ መሆኑን አሳይተውናል፡፡

ወዲያውኑ ወደኋላ ተመልሼ ማሰብ ተጠበቀብኝ፡፡ ስድስት-ለ-ሁለት ተሁኖ በሚደረገው አነስተኛ ልምምድ መሳይ ጨዋታ ላይ “የሶስተኛው መስመር ቅብብል”  ስለሚሰኘው የመከላከል መርህ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ” እሺ ቆይ – ምናልባት የአንድ ቡድን አማካይ ክፍል ከመስመር የተሻለ ቅርጽ ቢይዝስ? ማለቴ አማካይ ክፍሉ ዝርግ ባይሆንስ? ምክንያቱም የትኛውም የአማካይ ክፍል በአንድ ቅብብል ብቻ የበላይነት ሲወሰድበት በቀላሉ ለመቀበል ይቸግረዋል፡፡” ብዬ ለሃሳቡ ጥያቄም መልስም አቀረብኩ፡፡ እንዲያም ሆኖ ለአይርተን ኅልዮታዊ የታክቲክ አቋም የምሰጠው ምላሽ የእርሱን ድምዳሜ የሚቃረን አመክንዮ ሆኖ ተሰማኝ፡፡
እኔም ልክ እንደ እርሱ “ስድስት ተጫዋቾች-ከ-ሁለት ተጋጣሚዎች” ጋር በሚያደርጉት አነስተኛ ጨዋታ የመቀባበያ አቅጣጫዎችን የሚያመለክቱ መስመሮችን ሳልሁ፡፡ እነዚህን አማራጭ የመቀባበያ አቅጣጫዎች በተለያዩ የሥልጠና መንገዶች መጠቀም ስለሚቻሉባቸው ዘዴዎችም ዝርዝር ሃሳቦችን ገለጽሁለት፡፡

ከላይ በሚታየው ምስል ሰማያዊዎቹ መስመሮች  በሁለቱ ተከላካይ ተጫዋቾች አማካኝነት ቅብብሎቹ ሊቋረጡ የሚችሉባቸውን ሐሳባዊ ቦታዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ምስሉ እነዚህ ሁለት ተከላካዮች የተጋጣሚ ቡድን ስድስቱን ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ፍሬ አልባ እንዲሆን ሊያደርጉ የሚችሉባቸውን ንድፈ-ሐሳባዊ ዝርዝርም ይሰጣል፡፡

በእንዲህ አይነቱ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ ፍልሚያ (ስድስት-ለ-ሁለት በሆነ የተጫዋቾች ሁኔታ) ተከላካዮች ተራርቀው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአንድ ዝርግ መስመር ከመገኘት ይልቅም በሁለት የተለያዩ መስመሮች ላይ መገኘት የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡ ተከላካዮቹ ከቻሉ የጨዋታ ፍሰቱን ለማቋረጥ ሁለተኛ የመቀባበያ መስመሮችን መዝጋት አለባቸው፡፡ ምሉዕ ከሆነ ጽንሰ-ሐሳብ አንጻር ተከላካዮች የተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች “ሶስተኛ የመቀባበያ መስመር” እንዲጠቀሙ የሚገደዱበት ቦታ ላይ ተገኝተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ሶስተኛ የመቀባበያ አቅጣጫን የማግኘት ሁኔታ ኳስ ለያዘውና በማጥቃት ሒደት ላይ ላለው ቡድን አመቺ መንገድ ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይሁን እንጂ ተከላካዮቹ ተጫዋቾች በተለያዩ መስመሮች እና አቅጣጫዎች በመገኘታቸው ቅብብሎችን የማቋረጥ ዕድላቸው ይሰፋላቸዋል፡፡  በመጀመሪያው የመቀባበያ መስመር ላይ ቅብብሉ በሚካሄድበት ቅጽበት መገኘት ግን ተከላካዮችን ከሁሉ በላይ የሚበጀው ሥልት ነው፡፡

የላይኛው ታክቲካዊ ኅልዮትና የቀረቡት ሁኔታዎች በአግባቡ ከተተገበሩ የተከላካዮቹ ቁጥር ሁለት ብቻ ቢሆንም ከስድስቱ የባላጋራ ቡድን ተጫዋቾች ላይ ኳስ የመንጠቅ አቅም ማጎልበት ይቻላል፡፡ ይህ ኅልዮት በመከላከል ሒደት ላይ ለሚገኝ ቡድን እና ተከላካዮች በመሃል ሜዳ ሶስት ተጫዋቾችን በዝርግ መስመር ማሰለፍ ምንም እንደማያስፈልግ ያሳያል፡፡ ከዚህ አንጻር ጽንሰ-ሐሳባዊ ድምዳሜው የአይርተን ሳርጉሲንግን እምነትን፡ ፉርሽ ያደርጋል፡፡

በክርክራችን አይርተን የሚበገር አልሆነም፡፡ እርሱ የደረሰበትን ኃሳባዊ ድምዳሜ የሙጥኝ አለ፡፡ ስለዚህ ” የእግርኳስ ዋናው ዓላማ ኳሱን ሳይሆን ተጋጣሚን ማንቀሳቀስ ወይም መግፋት ነው፡፡” ተብሎ ስለተገለጸው መነሻ ሐሳብ ማሰላሰል ያዝሁ፡፡

ከላይ በቀረበው የ”ስድስት-ከ-ሁለት ተጫዋቾች” ጽንሰ ሐሳብ መልሶ ወደ “ሁለት-ከ-አንድ ተጫዋች” ወደሚለው የአይርተን መደምደሚያ የሚያደርስ ሌላ ትንታኔ ይኖር እንደሆን ብለን አሰብን፡፡ አይርተን ሁለቱ የኳስ ቅብብሉን ለማቋረጥ የሚታትሩ ተጫዋቾች በአንድ መስመር ላይ የሚገኙ አልያም የተራራቁ ከሆኑ ድምዳሜው ልከኛ ስለመሆኑ አንስቶ ሙግቱ መቋጫ እንዳይበጅለት አደረገ፡፡ ይሁን እንጂ እርሱ ከጠቀሳቸው ሁለቱ የሜዳ ላይ ምናባዊ ሁኔታዎች አንደኛውን ለማሳካት እንቅስቃሴውን ማጤን የግድ ይላል፡፡ በእንቅስቃሴ ሒደት ላይ ያለው ኳሱ ወይስ የተጋጣሚያችን ተጫዋቾች? ያኔ ቅብብል እንዲያቋርጡ የሚጠበቁት ተጫዋቾችን እንቅስቃሴ እና ዋላይ ቦታ አያያዝ መቆጣጠር ይቻላል፡፡

ከላይ በቀረበው ምስል ኳስ ለያዘው ተጫዋች የመቀባበያ አማራጭ ለመሥጠት ወደኋላ የተመለሰው ተጫዋች በግራ እግሩ አቅጣጫ “የመጀመሪያ የመቀባበያ መስመር” መስራት ችሏል፡፡ ይህ የመቀባበያ መስመር አንደኛውን ተከላካይ ወደ ኳስ ተቀባዩ ተጫዋች እንዲጠጋ ከመጋበዙም በላይ ቅብብሉን ለማቋረጥ እንዲንቀሳቀስ አነሳስቶታል፡፡ ተከላካዩ ይህን ሲያደርግ ከቀድሞ ቦታው ከመነሳቱ በተጨማሪ በጨዋታው ላይ በዚያች ቅጽበት የሚኖረውን ተጽዕኖ እንዳያሳርፍ ያደርገዋል፡፡

በርካታ ጊዜያትን ከወሰዱ ሐሰሳዎች በኋላ አዳዲስ ሐሳቦች ተገኙ፡፡ ” እግርኳስ በሜዳ ላይ የሚገኙ የአንድ ቡድን ሁለት ተጫዋቾች በተጋጣሚ ቡድን አንድ ተጫዋች ላይ በሚያሳድሩት ጫና የሚካሄድና በተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ የሚወሰን ጨዋታ ነው፡፡” ከሚለው
ቀላል መነሻም እግርኳስ የምቃኝባቸውን አተያዮች ቃረምኩ፡፡ ይህ እንግዲህ የሐሳብ መነሻ ሒደት ቢሆንም መድረሻው ሉዊ ቫን ሃል እና ማርሴሎ ቢዬልሳ የደረሱበት ድምዳሜ ላይ እንደሚቋጭ ግልጽ ነው፡፡ እንደ ተጫዋችም ሆነ አሰልጣኝ እግርኳስን በምንረዳበት መሰረታዊ መዋቅር ላይ ባሉት እያንዳንዳቸው ወሳኝ እርከኖች ሐሳብ ላረገዙ ቃላት ትኩረት መስጠት አለብን፡፡

” እንደ ጋሪ ሜደል ያለ አማካይ ስለ ተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ የሚያስበው ከኋላ መስርተው እንደሚጫወቱ ሌሎች የመሃል ተከላካዮች አይደለም፡፡ ቢዬልሳም ሜዴልን ከመደበኛ የአማካይነት ሚናው ይልቅ በጥልቀት ወደኋላ አፈግፍጎ የቅብብሎች ሒደትን እንዲመሰርት የሚያደርገው የሆነ የተለየ አቅም ቢያይበት ይመስለኛል፡፡”

– ክሪስ ዴቪስ፦ የቀድሞው የሊቨርፑል ወጣት ቡድን አሰልጣኝና የቪዲዮ ተንታኝ በቅርቡ ደግሞ የሴልቲክ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ያገለገለ

” ማርሴሎ ቢዬልሳ አጥቂዎች ጨዋታን ካፈገፈገ ቦታ እንዲጀምሩ የማድረግ ዝንባሌ ያሳያሉ፡፡ ምክንያቱም የማጥቃት አዕምሮ ያላቸው ተጫዋቾች የማጥቃት አጨዋወቱን ወጥ በማድረግና የጨዋታውን ፍሰት በመጠበቅ ረገድ ውጤታማ ናቸው፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች የኳስ ቅብብሉን ሒደትም ያሻሽላሉ፡፡ ቢዬልሳ ይህን በአትሌቲኮ ቢልባዖ ሳሉ በሃቪ ማርቲኔዝ አሳይተውናል፡፡”

– ፔፕ ክሎቴት፦ በስዋንሲ የጋሪ ሞንክ ረዳት አሰልጣኝ የነበረና ቀጥሎም በሊድስ ዩናይትድ ቆይታው በማርሴሎ ቢዬልሳ አማካሪነት ሲታገዝ የቆየ

ይቀጥላል…

የመጽሃፉ ደራሲ ጄድ ሳይናን ዴቪስ ይባላል፡፡ ዌልሳዊው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በዋና አሰልጣኝነት፣ በኢስቶኒያ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ በምክትል አሰልጣኝነት ሰርቷል፡፡ የሰላሳ ሁለት ዓመቱ ወጣት በአሁኑ ወቅት <ኦታዋ ፈሪ> በተባለው የካናዳ ክለብ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ከ2019 ጀምሮ በኦታዋ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ የእግርኳስ ፕሮፌሰር ሆኖ Strategy in Association Football ያስተምራል፡፡ ዴቪስ በ2013 ” Coaching the Tiki-Taka Style of Play” የተሰኘ መጽሃፍ አሳትሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ