​አራት የስሑል ሽረ ተጫዋቾች ወደ አዳማ ከተማ አምርተዋል

ስሑል ሽረ በፕሪምየር ሊጉ እንደማይሳተፍ በክለቡ አሰልጣኝ ሲሳይ አብረሀም አማካኝነት ለተጫዋቾቹ በመገለፁ አራት የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ አዳማ ከተማ ተጉዘዋል፡፡

በትግራይ ክልል በተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ በፕሪምየር ሊጉ አለመሳተፉ እርግጥ የሆነው ስሑል ሽረ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዘንድሮ ወደየትኛውም ክለብ ሄደው መጫወት ይችላሉ መባሉን ተከትሎ አራት የስሑል ሽረ ተጫዋቾች በይፋ አዳማ ከተማን ፌዴሬሽን በመገኘት ተቀላቅለዋል፡፡

የቀድሞው የደደቢት፣ ወላይታ ድቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ወደ አዳማ ካመሩትገመካከል ነክ። በክረምቱ ወደ አዳማ ለማምራት ስማምቶ የነበረው ተጫዋቹ ከዝውውሩ መስኮት መከፈት በኋላ ወደ ሽረ ማምራቱ የሚታወስ ነው። በሰበታ ከተማ ዓምና ቆይታ የነበረው እና ዘንድሮ ለሽረ ፈርሞ የነበረው አማካዩ ደሳለኝ ደባሽ ወደ ቀድሞ ክለቡ የሚመልሰውን ዝውውር ሲፈፅም በተሰረዘው የውድድር ዓመት አጋማሽ ሀድያ ሆሳዕናን ለቆ ወደ ሰሜኑ ክለብ ያመራው ተከላካዩ ደስታ ጊቻሞ እና በተመሳሳይ ወልቂጤን በመልቀቅ በአጋማሹ እንደ ደስታ ሁሉ ሽረን ተቀላቅሎ የነበረው አማካዩ በቃሉ ገነነ   አዳማ ከተማን መቀላቀላቸው ዕውን ሆኗል፡፡

አዳማ ከተማ ከአራቱ የስሑል ሽረ ተጫዋቾች በተጨማሪ በወልዋሎ እና ሊጉ በኮሮና ቫይረስ ከመሰረዙ በፊት ወላይታ ድቻን ተቀላቅሎ የነበረው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሚካኤል ለማ እና በከፍተኛ ሊጉ ዓምና በዲላ ከተማ ቆይታ ያደረገው አምሳሉ መንገሻን አስፈርሟል።

© ሶከር ኢትዮጵያ