​ስሑል ሽረ በፕሪምየር ሊጉ አለመሳተፉ እርግጥ ሆኗል

በአሠልጣኝ ሲሳይ አብርሃ የሚመሩት ስሑል ሽረዎች በ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመሳተፋቸው ነገር አክትሞለታል።

በወቅታዊ የሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታ የቅደመ ውድድር ዝግጅታቸውን ያላከናወኑት ስሑል ሽረዎች ከቀናት በፊት ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ወደ መሐል ከተማ መምጣታቸው ይታወሳል። 16 ተጫዋቾችን ብቻ ይዞ አዲስ አበባ የደረሰው ክለቡ በዘንድሮ የፕሪምየር ሊግ ውድድር ለመሳተፍ ማረጋገጫ አልሰጠም። እርግጥ ሽረዎች በ16 ተጫዋቾቹ እየተመራ ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ቅደመ ሁኔታዎችን ቢያሟላም ውድድሩን ታህሣሥ 3 ለመጀመር አላሰበም። ይህንን ተከትሎም ባሳለፍነው ዓርብ ክለቡ ለሊግ ኩባንያው ቢያንስ የሊጉ ጨዋታዎች ለሁለት ሳምንታት እንዲገፉለት ደብዳቤ አስገብቶ ነበር።
የክለቡን ጥያቄ የተመለከተው የሊጉ ኩባንያ የወጣው መርሐ-ግብር እንደማይገፋ ለክለቡ በይፋ ምላሽ ሰጥቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ባደረገው ስብሰባ ክለቡን በተመለከተ ሀላፊነት የሚወስድ አካል ባለመኖሩ ስሑል ሽረ በውድድሩ የመሳተፉ ነገር አክትሞለታል። ስለዚህም ስሑል ሽረ በይፋ የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ አይሆንም። 
በተያያዘ ዜና ስሑል ሸረ በርካታ ተጫዋቾቹን በውሰት እየሰጠ እንደሆነ እየተሰማ ይገኛል። የሌሎቹን ትግራይ ክልል ተሳታፊ ክለቦችን በተመለከተ ሊግ ኩባንያው እስካሁን ግንኙነት እንደሌለው የሰማን ሲሆን እስከ ዓርብ ምሽት ድረስም ለውድድሩ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው ከተገኙ በውድድሩ እንደሚሳተፉ መገለፁ ይታወሳል።
©ሶከር ኢትዮጵያ