ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ እና ኮከቦች ሽልማት በቅርቡ ይወሰናል

የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለውድድሩ አሸናፊዎች እና ኮከቦች ያለ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት የሊግ ኩባንያው ቦርድ በቅርቡ የሚወስን ይሆናል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስያሜ ለውጥ በማድረግ ሊግ ካምፓኒው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በማለት ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ማግኘቱ ይታወሳል። የሊግ ካምፓኒው ቦርድ ባሳለፍነው ሳምንት ስብሰባ ተቀምጦ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ውይይት ካደረገ በኋላ እንደመነሻ ሀሳብ ተወያይቶ በይደር በቀጠሮ ያሳደረው ጉዳይ አለ። ይኸውም በውድድሩ ከአንድ እስከ ሦስት ለሚወጡ እና ኮከብ ተብለው ለሚሸለሙ የተለያዩ አካላት ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት ማውጣቱን ሰምተናል።

እርሱም በውድድሩ ላይ ቻምፒዮን ሆኖ ለሚያጠናቅቀው ቡድን ለየት ያለ ዋንጫ ዲዛይን ወጥቶለት በትዕዛዝ የሚሰራ ዋንጫ እንዳለ ሆኖ አንድ ሚሊዮን ብር፣ ሁለተኛ ሆኖ ለሚያጠናቅቀው ቡድን ሰባት መቶ ሺህ ብር፣ ሦስተኛ ሆኖ ለሚያጠናቅቀው ቡድን አምስት መቶ ሺህ ብር ለመስጠት ማሰባቸውን ሰምተናል። ከዚህ በተጨማሪ የክለቦቹን አቅም ለማጠናከር ከአንድ እስከ 13ኛ ለሚያጠናቀቁ ቡድኖች እንደ የደረጃቸው በፐርሰት ተከፋፍለው ገንዘብ እንደሚያገኙ ለማወቅ ችለናል።

ኮከብ አሰልጣኝ፣ ኮከብ ተጫዋች፣ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ፣ ኮከብ ግብጠባቂ፣ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋች እንዲሁም ምስጉን ዳኞችን ጨምሮ ከሁለት መቶ ሺህ ብር ጀምሮ በየደረጃው ለመሸለም እንዳሰቡ ሰምተናል።

ከላይ ያስቀመጥናቸውን መነሻ የሽልማት መጠን ዛሬ አልያም ነገ በሚኖረው ስብሰባ ቦርዱ ያፀድቀዋል ወይስ ሌላ የሽልማት መጠን ይቀይራል የሚለውን ጉዳይ ካለ ተከታትለን የምናሳውቅ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ