“ሜዳ ውስጥ ሁሉን ነገር የማደርገው በድፍረት ነው” – ፍፁም ዓለሙ

በ2013 የውድድር ዘመን ባህር ዳር ከተማ የመጀመርያ ጨዋታውን በድል እንዲጀምር ካስቻለው እና ሁለት አስደናቂ ጎል ካስቆጠረው ከፍፁም ዓለሙ ቆይታ አድርገናል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በባህር ዳር እና በሲዳማ ቡና መካከል ሲካሄድ ከተመዘገበው ውጤት በላይ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን አሳይቷል። ፍፁም በይበልጥ ባህር ዳርን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ በየጨዋታዎቹ ለቡድኑ አስፈላጊውን እያደረገ ይገኛል። በትናንቱም ጨዋታ ሁለት አስደናቂ ጎል በማስቆጠር ከወዲሁ አጀማመሩን አሳምሯል። በጉዳት ተቀይሮ መውጣቱን ተከትሎ በቀጣይ ጨዋታ ስለመድረሱ እና ወደፊት ስለሚያስበው ነገር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አግኝተን አዋርተነዋል።

” ከጨዋታው አስቀድሞ ተረከዜ ላይ ጉዳት ነበረኝ፤ ሆኖም አሰልጣኜ ነው አምኖበት እንድገባ ያደረገኝ። ከፈጣሪ ጋር ጉዳቴ ማገገም ከቻልኩ በቀጣይ ጨዋታ የምደርስ ይመስለኛል። አንዳንዴ ተደጋጋሚ ጎል ስታገባ በራስ መተማመንህ ከፍ ይላል። ሁሉን ነገር ሜዳ ውስጥ የማደርገው በድፍረት ነው። ግብጠባቂዎችንም የማልፈው እና ጎል ያስቆጠርኩት ለዛ ነው። ይህን በትናንትናው ጨዋታ ብቻ ያሳየሁት አይደለም። ሁሌም በልምምድ የምሰራቸው ናቸው። ለእኔ እንዲህ ያለ ጎል ማስቆጠሬ ምንም አልገረመኝም። ብዙ ጊዜ እንዲህ ያለ ነገሮችን ስለምሰራ ከሥራ የመጣ ነው ብዬ አምናለው። ሁሉም ነገር ፈጣሪ ሲፈቅድ ነው የምናረገው እና በዚህ ዓመት ጎል በማግባት ውድድሩን ጀምሬያለው። ከዚህ በኋላ ባሉ ጨዋታዎች ከጓደኞቼ ጋር ተጋግዤ ከባህር ዳር ጋር ጥሩ ጊዜ እንደማሳልፍ በርግጠኝነት እናገራለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ