“መንግሥቱ ወርቁ ለጥቅም ብሎ በሙያው የማይደራደር አሰልጣኝ ነበር” ይልማ ተስፋዬ (ካቻማሊ)

ከቀድሞው ተጫዋቾች ውስጥ ይልማ ተስፋዬ ስለያኔው አሰልጣኙ መንግሥቱ ወርቁ ምስክርነቱን እንዲህ ይሰጣል።

የታላቁን የእግር ኳስ ሰው መንግሥቱ ወርቁ አስረኛ ሙት ዓመት አስመልክተን በሁለተኝነት ያሰናዳንላችሁ ከቀድሞው ተጫዋች ይልማ ተስፋዬ (ካቻማሊ) ጋር የተደገን ቆይታ ነው። በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ በክለብ እና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በርካታ ክብሮችን ያሳካው ታላቁ የእግርኳስ ሰው ወደ አሰልጣኝነት ሙያ መጥቶም እስከ ኢንስትራክተርነት ደረጃ ድረስ ዘልቋል። በአሰልጣኝነት በሰራባቸው ክለቦች ውስጥም እጅግ የሚከበር ባለግርማ ሞገስ አሰልጣኝ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክሩለታል። እኛም ለዛሬ ከ1989 ጀምሮ በአየር መንገድ ፣ በመድን እና በቅዱስ ጊዮርጊስ አብሮት የመሥራት ዕድልን ካገኘው እና አሁን ላይ መኖሪያውን በደቡብ አፍሪካ ካደረገው ይልማ ተስፋዬ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ አቅርበንላችኋል።

ስለ ትውውቃቸው…

“እኔ ከሀዋሳ ዱቄት ወደ አየር መንገድ ስገባ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት። በዛን ወቅት ላይ በነበረኝ አቅም ላይ ትልቅ አቅም ነው የጨመረልኝ። የእግርኳስን መሠረታዊ ዕውቀቶች ያስተማረኝ አባቴ ነው ማለት እችላለሁ። ግንኙነታችንም ልክ እንደ አሰልጣኝ እና እንደ ተጫዋች ከእዛ ባለፈም እንደ አባት እና ልጅም ነበር። በጣም የምወድለት ያመነበትን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የማይል ፣ ለጥቅም ብሎ በሙያውን የማይደራደር አሰልጣኝ ነበር። በህይወቴ ከእሱ የተማርኩት ትልቅ ትምህርት ቢኖር ይሄንን ነው።”

ስለአሰልጣኝነቱ…

“ጋሽ መንግሥቱ የሚከተለው ጨዋታ ዘመናዊ ስልትን የተከተለ ነበር። በሜዳ ላይ ልምምድ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ የሆነ የእግር ኳስ አጨዋወትን በክፍል ውስጥ እየሰጠ የእግርኳስን ዕውቀት የሚያስጨብጥ አሰልጣኝ ነበር። እኔ በህይወት እያለ የእግርኳስ ዕውቀቱን በሚገባ አልተጠቀምንበትም ከሚሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነኝ። በጣም ትልቅ አሰልጣኝ ነበር። በዚያን ወቅት የኢትዮጵያን እግርኳስ ችግር የተረዳ ሰው ይመስለኛል። ምክንያቱም ቡድኖች ሲሰራ በወጣቶች ላይ የሚያምን ብቻ ሳይሆን ቀጥታ መርጦ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አስገብቶ ተጫዋቾች በራሳቸው ዕምነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ፣ ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራ ፣ በሙያው የማይደራደር ትልቅ ባለሙያ ነበር።”

ከተጨዋቾች ስለሚፈልገው መሰረታዊ ነገር…

“መጀመሪያ የተጫዋችን ዕድሜ የሚያይ ይመስለኛል። ከዚያ ደግሞ የተጨዋቹን ብቃት ያያል። ይህን ካየ በኋላ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግን ለዲስፕሊን ነው። ዲስፕሊን የሌለው ተጨዋች በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። የልምምድ ሰዓት ማክበር እና በተሟላ ትጥቅ መገኘትን ይፈልጋል። መጋጫ እንኳን ከዘነጋህ ትመለሳለህ። ከልምምድ በኋላ በቂ ዕረፍት እንድታደርግም ይፈልጋል። ሌላው ሲያሰራ ከእያንዳንዱ ተጫዋች የሚጠብቀው ነገር አለ። ያንን ሜዳ ላይ ቁጭ ብሎ ያያል። ከዛ ሰው የሚጠብቀውን ነገር ካላገኘ ይጠራና ያናግራል። ችግሩ ምን እንደሆነ ይጠይቃል። በዚያን ሰዓት ችግሩ ከዲስፕሊን ጋር የተገናኘ ሆኖ ካገኘው ሊያይህ አይፈልግም። ሲበሳጭ ግን በጣም የሚያስፈራ ነበር ፤ አጠገቡ መቆም ራሱ ጥሩ አይመስለኝም ፤ ሊማታም ይችላል። (እየሳቀ) አሰርቶ ማግኘት የሚፈልገውን ነገር ሲያጣ ይመስለኛል። በሌላ በኩል በጣም ጥሩ አሰልጣኝ እና አባት ነው።”

በታዳጊዎች ላይ ስለነበረው ዕምነት…

“እንደ እኔ ዕምነት ኢትዮጵያ ውስጥ የእሱን ያህል አንድን ተጫዋች ከታዳጊነት ጀምሮ ትልቅ ደረጃ ለማድረስ የሚሰራ አሰልጣኝ ያለ አይመስለኝም። ብዙውን ስራ መስራት የሚፈልገው ወጣቶች ላይ ነበር። ቅድሚያ የሚሰጠው ለውጤት ሳይሆን ቡድኑን መስራት ላይ ነው። ይሰራ የነበረው ወጣቶች ላይ ስለነበርም ውጤቱን በአንድ ዓመት ማየት አይቻልም ነበር። እኔ እንደማየው ከሆነ ስራውን ያበላሽበት የነበረው የቡድኖች ጊዜያዊ ውጤት ፈላጊ መሆን ነበር። ስለዚህ ለስራው ጊዜ አይሰጡትም ነበር። እሱ ደግሞ በዚህ ይበሳጫል። ምክንያቱም እሱ ሙያውን ነው የሚያየው። ደመወዛቸውን ወይም ጥቅም ሳይሆን ሙያውን ነበር የሚያስቀድመው። በዚህ በዚህ ከአስተዳደሮች ጋር አይግባባም ነበር። በአመራሮች ዘንድ ችግሩ እስካሁንም ድረስ ያለ ቢሆንም እሱ ግን በዚያን ጊዜ እንኳን ኃላፊነት ወስዶ ሙያውን ብቻ በማክበር ለመስራት ይሞክር ነበር። ሞክሮም ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች የፈጠረበት ጊዜ ነበር። በዛን ሰዓት የነበሩ አሁን ጥሩ ደረጃ የደረሱ ተጫዋቾችም አሉ።”

በጨዋታ ወቅት ስለነበረው ባህሪ…

“ከእሱ ጋር በምንሰራበት ጊዜ ከጨዋታ በፊት አሰላለፍ አውጥቶ በምን መንገድ መጫወት እንዳለብን እንዲሁም የተቃራኒን ቡድን ደካማ ጎንም ጨምሮ ብዙ ነገር ይመክረናል። ከዚያ በኋላ ሜዳ እንገባለን። በጨዋታ ወቅት ግን ብዙ ጊዜ በምክትል አሰልጣኙ በኩል ነው መደረግ ያለባቸውን ማስተካከያዎች የሚያስተላልፈው።”

ትዝታዎች…

” ከልጁ ላቃቸው ጋር ጊዮርጊስ እያለን አንድ ወቅት ምሳ ሰዓት ላይ ቤታቸው ሄድን። ስንገባ ቆንጆ ምግብ ይሸት ነበር እና ‘ምንድነው የሚሸተው ?’ ብዬው ለእናቱ ነግሮ እና ምሳ በልተን ወደ ልምምድ ስንሄድ ጋሽ መንግሥቱ “አንዱ ዛሬ ቤቴ ሄዶ ምሳዬን በልቶብኝ ነው የመጣው፤ እኔ ምሳ አልበላሁም” ያለበትን ጊዜ አልረሳውም።”

“አንድ ጊዜ ደግሞ በሆነ ጉዳይ ጊዮርጊስ ፅህፈት ቤት ስሄድ እዛ ቁጭ ብሏል። እና ሰላም ብዬው ቁጭ አልኩ። እንዳጋጣሚ የ’ቢ’ ወይ የ’ሲ’ ቡድን ጨዋታን አይቶ ምርጫዎችን ለማድረግ ሲሄድ አብረን እንሂድ ብሎኝ ሄድን። ጨዋታውን ለብቻ ገንጠል ብለን እያየን ቆይተን ጨረስን እና ስለኳስ እያወራን ስንመለስ እኔ “ጋሼ አንተ እኮ የሚጠቅሙህንም ተጫዋቾች የዲስፕሊን ችግር ስታይ ቶሎ ውሳኔ ላይ ደርሰህ ታባርራለህ ሌሎች አሰልጣኞች እኮ እንደዚህ አይደሉም” ባልኩት ወቅት የሳቀውን ሳቅ አልረሳውም ፤ በጣም ነበር የሳቀው። በቦታው የነበሩ ሰዎች ሁሉ “ምን ብሎህ ነው እንዲህ የምትስቀው ?” ብለው ጠይቀውት ነበር።”

“መድን ላይ ጥሩ ቡድን ሰርቶ ነበር። በአየር መንገድ ያሳደጋቸውን ልጆች ሰብስቦ ነበር ያንን ቡድን የሰራው። ዝግጅታችን ናዝሬት ላይ ነበር። ከዛ በመሐል በካፍ ሥልጠና እንዲሰጥ ተጠርቶ ሲሄድ ለንጉሤ ገብሬ “ካቻን ጠይቀው እየሰራን የነበርነውን ሥራ ስለሚያውቅ ይረዳሀል” ብሎ ነግሮት ነው የሄደው፤ ለካ እኔ አላወኩም ነበር። ብዙ ጊዜ ተጫዋቾች ከአሰልጣኝ ጋር ቀረቤታ ሲኖርህ በጥሩ መንገድ አይረዱትም። እና ለእሱም በተጫዋቾች ፊት እንዳያዋራኝ እነግረው ነበር፤ ግን ይስቅብኝ ነበር። እና ያኔ ማታ ላይ ንጉሤ እሱ ያለውን ሲነግረኝ ‘እኔ አላሰራም ባይሆን ከፊት ሆኜ ጀምራለሁ አንተ እያሰራህ ቀጥል’ ብዬ በዛ መንገድ ቀጠልን። እና በእኔ ላይ ልዩ ዕምነት ነበረው በወቅቱ። ያንን ሳስብ ደስ ይለኛል።”

“እዚህ ደቡብ አፍሪካ ከመጣው በኋላ ጋሽ መንግሥቱ ለህክምና መጥቶ ያረፈበት ሆቴል እኔ፣ ባለቤቴ እና የመጀመሪያ ልጄ (ሁለት ወይ አንድ ዓመት ቢሆነው ነበር) ሄደን ጎብኝተነው ነበር። በዚያ ወቅት እያወራን እየተጫወትን ቆየን እና በመሀል ወደ መታጠቢያ ቤት ስሄድ ለባለቤቴ ” በጣም የዋህ ሰው ነው ፤ መቼም አይወድቅም ፤ በጣም ንፁህ ሰው ነው” ብሎ የነገራትን ስትነግረኝ ለእኔ ባለው አመለካከት በጣም ነበር ደስ ያለኝ የነበረው።”

በመጨረሻ…

“ስለእሱ የማውቀውን ያህል እንድገልፅ ስለጋበዛችሁኝ እጅግ አመሰግናለሁ። ትልቅ የሙያ አባቴ ነው። በህይወትም ብዙ ነገርን አስተምሮኛል። ነፍሱን ይማርልን ፤ ነፍሱን በገነት ያኑርልን እላለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ