“ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር አብሬ መጫወቴ ራሴን በጣም ዕድለኛ አድርጌ ነው የምቆጥረው” – ፉአድ ፈረጃ

ሰበታ ከተማ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ምርጥ ብቃቱን እያሳየ ከሚገኘው እና በዛሬው ጨዋታ አንድ ጎል ካስቆጠረው ፉአድ ፈረጃ ጋር ቆይታ አድርገናል።

የእግርኳስ ጅማሬውን በአዳማ ከተማ ያደረገው እና ዘንድሮ ሰበታ ከተማን የተቀላቀለው ፉአድ ፈረጃ ጥሩ የሚባል የውድድር ጅማሮ እያደረገ ይገኛል። በተከታታይ ሰበታ ባደረጋቸው ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ላይ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሚሰጡትን የተለያዩ ሚናዎች በአግባቡ እየተወጣ የሚገኘው ፉአድ ሰበታ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ላስመዘገበው ውጤት ከነበረው መልካም ተሳትፎ በተጓዳኝ ድላቸውን ያረጋገጡበትን ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። አጀማመሩ ካማረለት ሁለገቡ ወጣት ተጫዋች ፉአድ ፈረጃ ጋር ከዛሬው ጨዋታ ጋር አያይዘን የተወሰኑ ጥያቄዎች አቅርበንለት ተከታዮን ምላሽ ሰጥቶናል።

” ከአዲሱ ክለቤ ጋር እስካሁን ጥሩ ቆይታ እያደረኩ እገኛለሁ። ትልቅ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር አብሬ መጫወቴና አሰልጣኛችን ከሚከተለው የጨዋታ ፍልስፍና ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን ውስጥ መገኘቴና የቡድን አንድነታችን መልካም መሆኑ ጥሩ ጅማሮ እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ሁለገብ ሆኖ መጫወቱ በተፈጥሮ የተሰጠኝ እንደሆነ አላውቅም። ብዙ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች እንድጫወት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በልምምድ ወቅት እያሰራኝ በጨዋታ ጊዜ እየተጠቀመብኝ ይገኛል። እኔም በምችለው አቅም የተሰጠኝን ኃላፊነት ለመወጣት እየሞከርኩ እገኛለሁ። ዛሬም በአዲሱ ክለቤ የመጀመርያ ጎሌን በማስቆጠሬ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከምንም በላይ በእውነት በጣም ደስ ያለኝ ከመንሱድ መሐመድና ከዳዊት እስጢፋኖስ ከሌሎችም ልምድ እና አቅም ካላቸው ተጫዋቾች ጋር አብሬ በመጫወቴ ራሴን በጣም እድለኛ አድርጌ ነው የምቆጥረው። ብዙ ነገሮች ነው እያገዙኝ እየመከሩኝ ያሉት። ያለኝን ችሎታ እንዳወጣ እጅግ እየተባበሩኝ ይገኛሉ። ባለኝ ነገርም እነርሱም ደስተኛ ናቸው። አሁን እያገኘሁት ያለው ስልጠና እና በየጨዋታው የማደርገው ጥሩ እንቅስቃሴ በቀጣይ ከሰበታ ከተማ ጋር ጥሩ ጊዜ እንዳሳልፍ ያግዘኛል። ከዚህ በተጨማሪ በብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ሆኜ የበለጠ ሀገሬን መጥቀም እና ከኢትዮጵያ ውጭ ወጥቶ መጫወትን በጣም አስባለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ