“ጎል አግብቼ ደስታዬን የገለፅኩበት መንገድ ከድሬዳዋ ጋር ይያያዛል” – ያሬድ ታደሰ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ወደፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው ድንቅ ተጫዋቾች የሚመደበው እና በዛሬው ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ የሆኑ ሁለት ጎሎች ለወልቂጤ ካስቆጠረው ያሬድ ታደሰ ጋር የተደረገ ቆይታ።

በድሬዳዋው ዋልያ ክለብ ውስጥ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው ያሬድ የከፍተኛ ሊግ ክለብ ተሳታፊ የነበረው እና በአሁኑ ሰዓት በፈረሰው ናሽናል ሲሜንት ከቢ ቡድን እስከ ዋናው ድረስ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን ከ2010 ጀምሮ ለትውልድ ከተማው የፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ድሬዳዋ ከተማ ሲጫወት ቆይቷል። ሆኖም የመሰለፍ እድል በማጣት ወደ ሀድያ ሆሳዕና በማምራት የእግርኳስ እድገቱን ለመጠበቅ ሲጫወት ቆይቷል። በዘንድሮ ዓመት በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በሚመራው ወልቂጤ ከተማ በማምራት በሊጉ የመጀመርያ ሁለት ሳምንት ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት ያለውን አቅም በማሳየት በዛሬው የወላይታ ድቻ ስብስብ ውስጥ በመካተት ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ለቡርትካናማዎቹ የዘንድሮ ዓመት የመጀመርያ ድል አስተዋፆኦ አድርጓል። ከወዲሁ ሦስት ጎል ያስቆጠረው ይህ የተረጋጋ ወጣት አማካይ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

“የውድድር አጀማመሬ አሪፍ ነው። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሬ በመግባት ጎል አስቆጥሬ ነበር። ቡድናችንም ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ ሦስተኛ ጨዋታ ላይ ደርሷል። ከዚህም በኃላ እኔ በግሌ ብቻ ሳይሆን እንደ ቡድን በመንቀሳቀስ ጥሩ የውድድር ዓመት እናሳልፋለን ብዬ አስባለው። ለኔ አሪፍ አጋጣሚ ነው፤ ከአማካይ ቦታ ተነስቼ በሦስት ጨዋታ ሦስት ጎል ማስቆጠሬ። ከዚህም በኃላ ባሉት ቀሪ ጨዋታዎች ጎል አስቆጥራለው ብዬ ነው የማስበው።

“ጎል ካስቆጠርኩ በኋላ ደስታዬን የገለፅኩበት መንገድ የራሱ መልክት አለው። መናገር አልፈልግም፤ ትንሽ አስቸጋሪ ነው። ግን በትንሹ ከድሬዳዋ ጋር ይገናኛል። ብዙ ነገር ውስጣችን አለ፤ ግን ቢሆንም ያንን ብዙም ወደኃላ ማስታወስ አልፈልግም። ከድሬዳዋ ጋር ትንሽ አለመግባባት ተፈጥሮ ነው የወጣሁት። በእግርኳስ ያለ ነው፤ ከአንዱ ወደ አንዱ ክለብ ትሄዳለህ። በዚህ ወቅት ወልቂጤ መጥቼ ጥሩ አጀማመር እያደረኩ ነው። ስለዚህ ከድሬዳዋ በመውጣቴ ብዙም አልከፋኝም።

“በቀጣይም ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ነገር ለመስራት አስባለው። ቡድናችን የሚፈልገውን ውጤት ለማሳካት ከጓደኞቼ ጋር ጥረት አደርጋለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ