ከፍተኛ ሊግ | መከላከያ አምስት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በከፍተኛ ሊጉ ከሌሎች ክለቦች ቀደም ብሎ በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ወደ ልምምድ ገብቶ የነበረው መከላከያ ተጨማሪ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

ሳሙኤል ሳሊሶ ወደ ቀድሞ ክለቡ የሚመልሰውን ዝውውር ፈፅሟል፡፡ መከላከያን ከለቀቀ በኃላ 2011 ላይ መቐለ 70 እንደርታን በመቀላቀል ሲጫወት የነበረው የመስመር አማካዩ መቐለን ለቆ ዓምና በአጋማሹ በወልቂጤ ቆይታን ካደረገ በኃላ ዳግም ጦሩን ተቀላቅሏል፡፡

ሌላኛው ተጫዋች አሌክስ ተሰማ ነው፡፡ በመቐለ 70 እንደርታ አምስት ዓመታትን ያሳለፈው የመሀል ተከላካዩ ከዚህ ቀደም በኒያላ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ዳሽን ቢራ የተጫወተ ሲሆን ከሁለት ወራት በፊት ለስሑል ሽረ ለመጫወት ቢፈርምም በትግራይ ክልል በነበረው ወቅታዊ ችግር የተነሳ ክለቡን በመልቀቅ ከወልቂጤ ጋር ልምምድ በመስራት ለክለቡ ይፈርማል ተብሎ ቢጠበቅም በመጨረሻ ማረፊያው መከላከያ ሆኗል፡፡

ሰለሞን ሀብቴም ወደ መከላከያ ተጉዟል፡፡ የቀድሞው የደደቢት እና ፋሲል ከነማ አማካይ በክረምቱ ለመቐለ ለመጫወት ፈርሞ የነበረ ቢሆንም በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ክለቡን ለቆ ለመከላከያ ፊርማውን አኑሯል፡፡

ሱራፌል ዳንኤልም የዮሐንስ ሳህሌው ስብስብን ተቀላቅሏል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ዓምና በሀድያ ሆሳዕና ያሳለፈው ተጫዋቹ የክለቡ አራተኛ ፈራሚ ነው፡፡ ሌላኛው ተጫዋች ዘካሪያስ ፅቅሬ ነው፡፡በአርባምንጭ ድሬዳዋ ሀላባ እንዲሁም ዓምና በአክሱም ከተማ ሊጉ እስከተሰረዘበት ጊዜ የቆየው አጥቂው የመከላከያ አምስተኛ ፈራሚ በመሆን ተቀላቅሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ