ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አርባምንጭ እና አዳማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማ ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡

ደካማ የሦስት ሳምንታት ጉዞን አጠናቀው ነበር ሁለቱ ክለቦች የተገናኙት። ልክ 10:00 ሲልም የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ ለማግኘት ጨዋታቸውን ጀምረዋል፡፡ አርባምንጭ ከተማ እና ያለፉት ዓመታት ጥንካሬ የከዳው አዳማ ከተማ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ኳስ በመቆጣጠር ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በፍላጎት እና በእልህ በሚጫወቱት አርባምንጭ ከተማዎች በደንብ መፈተን ችለዋል፡፡ ምርቃት ፈለቀ እና ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ የአመቱን ጨዋታዋን ያደረገችው የምስራች ላቀውን ኢላማ ያደረገው የክለቡ እንቅስቃሴ ከሁለቱ ተጫዋቾች የግል ጥረት ውጪ ወደ ግብ ሲያደርጓቸው የነበሩ ሙከራዎቻቸው ስኬታማ አልነበሩም። ይልቁንም በተሻጋሪ ኳስ እና አማካዩዋ ሜሮን ዘላለምን ያነጣጠረው የአርባምንጭ ረጃጅም ኳስ ለአዳማ ተከላካዮች አስቸጋሪ እንደነበር መመልከት ቢቻልም ኳስን ከመረብ ጋር ሊያዋህድ የሚችል ተጫዋች ግን ሜዳ ላይ አልነበረም፡፡

ምርቃት ፈለቀ እና ናርዶስ ጌትነት ያገኙትን ግልፅ አጋጣሚ በችኮላ ያመከኑበት እና ምርቃት ፈለቀ ነፃ አቋቋም ላይ ሆና ያገኘችሁን ኳስ በቀጥታ መታ ግብ ጠባቂዋ ነህሚያ አብዱ ያዳነችባት የአርባአምስት ደቂቃው የአዳማ ሙከራዎች ናቸው፡፡ እንደ ቡድን ለመንቀሳቀስ በቻሉት እና ካለፉት ጨዋታዎቻቸው በሚገባ የተማሩ የሚመስሉት አርባምንጮች ከርቀት መሠረት ማቲዮን አክርራ መታ እምወድሽ ይርጋሸዋ ያዳነቻት ኳስ ብቸኛው የክለቡ ዕድል ሆኖ ወደ መልበሻ አምርተዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የቀዘቀዘ የሜዳ ላይ ፉክክር የተመለከትንበት እንዲሁም ሁለቱም ክለቦች በአጥቂዎቻቸው የመጨረሻ ሳጥን ገብተው ደካማው የአጨራረስ ብቃታቸው ጎልቶ የታየበት ነበር፡፡ በተለይ የአዳማ ከተማዋ አጥቂ ምርቃት ፈለቀ በተደጋጋሚ በግሏ በምትፈጥረው ታታሪነት ያገኘቻቸውን ኳሶች እንደጥረቷ ሳይሆን በቀላሉ ስታመክነው ውላለች፡፡በአንፃሩ በትጋት ዛሬ የደመቁት አርባምንጭ ከተማዎች ቀላል የማይባሉ ዕድልን አግኝተዋል፡፡ 61ኛው ደቂቃም ግብ አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ የተባለባቸው አጋጣሚ ወደ ግብ ለመድረሳቸው ማሳያ ነው፡፡ ሆኖም ጨዋታው ያለ ግብ ፍፃሜውን ያገኘ ሲሆን ክለቦቹም የዓመቱ የመጀመሪያ አንድ ነጥብን ይዘዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የአዳማዋ አጥቂ ምርቃት ፈለቀን የጨዋታው ምርጥ ብሏታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ