ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አዲስ አበባ ከተማ በጎል ተንበሽብሾ ዓመቱን በድል ጀመረ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የመክፈቻ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ ዛሬ ተደርጎ አዲስ አበባ ከተማ ነቀምት ከተማን አሸንፏል፡፡

በሦስት ምድብ ተከፍሎ በተለያዩ ከተሞች የሚደረገው ይህ ውድድር የምድብ ለ ውድድር መክፈቻ ሀዋሳ አርቴፊሻል ሳር ሜዳ ላይ ከሰዓት 7:00 ሲል ተጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን እንዲሁም የፅህፈት ቤት ኃላፊው ባህሩ ጥላሁን እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመገኘት የአዲስ አበባ ከተማ እና ነቀምት ከተማን ጨዋታ አስጀምረዋል፡፡

በዚህ የመክፈቻ ዕለት አዲስ አበባ ከተማ ከሀላባ ከተማ እንደሚጫወቱ አስቀድሞ መርሀግብር ወጥቶ የነበረ ቢሆንም ሀላባ ከተማዎች የመመዝገቢያ ክፍያን መፈፀም ሳይችሉ በመቅረታቸው ነው በምትኩ ነቀምት ከተማ ተተክቶ መጫወት የቻለው፡፡ ከተያዘለቴ 7:00 ሰአት ሀያ ያህሉን ዘግይቶ በጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ግጭት እና ጉልበት በተጨማሪም አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች የታየበት ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ረጃጅም ኳሶች የበዙበት ከጨዋታ እንቅስቃሴ ይልቅ የእርስ በእርስ ሽኩቻወች የበረከቱበት ነበር፡፡

ሁለቱም ቡድኖች ተሻጋሪ ኳሶቸን ከሁሉም የሜዳው ክልል ወደ አጥቂዎች ባዘነበለ መልኩ መጣልን አማራጭ አድርገው ቢገቡም ስኬታማ ያደረጋቸው አልነበረም። ደቂቃዎች እየገፋ ሲመጣ ግን አዲስ አበባ ከተማዎች በቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ተሽለው ታይተዋል፡፡ የዕለቱ ዋና ዳኛ የነበራቸው የጨዋታ አመራር በሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች የበረታ ቅሬታ ሲቀርብባቸው እና በተጫዋቾች ሲገፈተሩ መመልከት ችለናል፡፡ በተለይ ሁለቱም ክለቦች አጥቂዎቻቸው በሳጥን ውስጥ ተጠልፈው ወድቀው ዳኛው በዝምታ ያለፉበት መንገድ የተቃውምው መነሻ የሆነ ድርጊት ነበር፡፡

33ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ አበባ ከተማዎች በጥሩ የቅብብል ፍሰት ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ተክሉ ተስፋዬ ብልጠቱን ተጠቅሞ የሰጠውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን የነቀምት ተከላካዮችን ስህተት ተመልክቶ ማራኪ ግብ በማስቆጠር ክለቡን መሪ አድርጓል፡፡በሒደት የነቀምት ከተማን የመከላከል ድክመትን በሚገባ እየተረዱ የመጡት አዲስ አበባዎች በድጋሚ ሁለተኛ ግብ አከለዋል፡፡ 42ኛው ደቂቃ ላይ የግራ ተከላካዩ ሮቤል ግርማ ከግራ በቀኝ በኩል ያሻገረለትን ኳስ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና ኤሌክትሪክ አጥቂ ተክሉ ተስፋዬ በድንቅ አጨራረስ ወደ 2 ለ 0 አሸጋግሯል፡፡ ኃይል የተቀላቀለበት እና ፍፁም ለዕይታ ቀዝቃዛ የነበረውም አጋማሽ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ተጫዋቾችን በጉዳት ለማጣት የተገደዱት ነቀምት ከተማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ የነበራቸው ተስፋ በዚህ ዕክል የተስተጓጎለባቸው ይመስላል፡፡ ኢብሳ በፍቃዱን መሠረት ባደረገው ተሻጋሪ ኳሶች ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም የተጫዋቹ መጎዳት ግን በእንቅስቃሴ ብለጫ ለወሰዱት አዲስ አበባዎች የቀለለ ሆኗል፡፡59ኛው ደቂቃ አምበሉ ተክሉ ተስፋዬ እየገፋ ወደ ጎል ገብቶ የመታት ኳስ የነቀምቱ ግብ ጠባቂ ሶፍኒያስ መቆጣጠር ባለመቻሉ አቡበከር ወንድሙ ደርሶ ወደ ጎልነት ለውጧት የክለቡን የግብ መጠን ወደ ሦስት አሳድጓል፡፡ አሁንም ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያልተለያቸው አዲስ አበባ ከተማዎች 63ኛው ደቂቃ አቡበከር ወንድሙ በሚገባ ተመልክቶ ያሻገረውን ሰይድ ሰጠኝ አራተኛ ግብ አክሎ ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 4 ለ 0 ተደምድሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ