ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋቾች ትኩረት

የ5ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዓበይት ተጫዋች ነክ ጉዳዮች የቀጣዩ ፅሁፋችን አካል ነው።

👉የምኞት ደበበ አይረሴ ውሎ

በ5ኛ ሳምንት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ አባ ጅፋር ከሀዋሳ ከተማ ጋር 1-1 በተለያዩበት ጨዋታ በምኞት ደበበ የእግርኳስ ታሪክ ከማይረሳቸው ቀናቶች መካከል ይካተታል።

ጅማ አባ ጅፋር እና ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ የጅማን የግብ ድንበሩን አላስደፍር ማለት የሀዋሳን ክፍተት ፍለጋ መዋተት አስመልክቶን ያለግብ ለመጠናቀቅ ተቃርቦ ነበር። ሆኖም በዕለቱ ጥሩ ብቃት በማሳየት የጅማን የመልሶ ማጥቃት ሙከራዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነት ሲያከሽፍ የቆየው ምኞት ደበበ የኤልያስ አታሮን ቅጣት ምት ጨርፎ በራሱ ላይ ግብ አስቆጠረ። ግዙፉ ተከላካይ በድጋሚ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው መነሻዋን ከማዕዘን ምት ያደረግችው ኳስ ተመቻልችታለት ወሳኟን ግብ አስቆጥሮ ከፀፀት ድኗል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ምኞት ተከታዩን አስተያየት ለድረ-ገጻችን ሰጥቶ ነበር።

“ቅጣት ምት ኳሱ ሲመታ ለማውጣት ነበር ሀሳቤ፤ እንዳጋጣሚ ሆኖ መጋጫዬን አላሰርኩትም ነበር። ኳሱ መጋጫዬን ጨርፎ ተቆርጦ ጎሉ ሊቆጠር ችሏል። ጎሉ ሲቆጠርብን በጣም ነበር ያዘንኩት። ማሸነፍ እያለብን እኛ ላይ ጎል ሲቆጠር እና እኔ ራሴ ላይ ጎል ሳስቆጥር በጣም ነው የተሰማኝ። ሆኖም ዳኛው የጭማሪ ደቂቃ ካሳየ በኃላ ቡድናችንን ከሽንፈት የታደገ ጎል ራሴ መልሼ በማግባቴ ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። ያው እንዲህ ያለ ነገር በእግርኳስ የሚያጋጥም ገጠመኝ ነው።”

👉ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ለማካተት የበቃው ጅማ

5ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ አባጅፋር በዚህኛው ሳምንት በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ በጨዋታ ዕለት ስብስቡ ውስጥ በቋሚነት ከሚጀምረው ግብ ጠባቂ ባሻገር በተጠባባቂነት ሁለት ግብ ጠባቂዎችን ይዞ ጨዋታ የጀመረበት ሳምንት ነው።

በተጠባባቂነት በመጀመሪያው ጨዋታ ገና በማለዳው በቀይ ካርድ በመውጣቱ የሜዳ ላይ ተጫዋች በግብጠባቂነት እንዲጠቀሙ ያስገደደው አቡበከር ኑሪ ከሦስት ጨዋታዎች ቅጣት ሲመለስ በተጨማሪም ክለብ አልባ የነበረውና በቅርቡ ጅማ አባጅፋርን የተቀላቀለው የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ወልዋሎ ግብጠባቂ የነበረው አንጋፋው ዮሀንስ ሽኩር የጄኮ ፔንዜ ተጠባባቂዎች ነበሩ።

👉የተመስገን ደረሰ የሚና ለውጥ

በሚፈለገው መጠን የተጫዋቾች አማራጭ የሌለው ጅማ አባ ጅፋር የሚና ለውጦችን በማድረግ ያሉትን ተጫዋቾች ሲጠቀም ይታያል። በዚህ ሳምንትም በመጀመሪያ አሰላለፍም በቅያሪም በአጥቂነት ቡድኑን ሲያገለግል የሰነበተው ተመስገን ደረሰ ቀድሞ ወደሚታወቅበት የመስመር ተከላካይነት ሚና ተመልሶ ተመልክተነዋል።

በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ቡድኑ በአዳማ ከተማ ሲሸነፍ የዓመቱን የመጀመሪያ ግቡን ለጅማ ያስቆጠረው ተመስገን በግራ መስመር ተከላካይነት ነበር ጨዋታውን የጀመረው። አሰልጣኝ ጳውሎስ የቦታው ቀዳሚ ተመራጫቸው የሆነው ኤልያስ አታሮን በከድር ኸይረዲን ጉዳት ሳቢያ በመሀል ተከላካይነት እየተጠቀሙበት ሲገኙ በግራ በኩል በአዳማው ጨዋታ ግብ ጠባቂም ሆኖ የነበረው አዳላሚን ናስርን አሁን ደግሞ ተመስገን ደረሰን አሰልፈዋል።

👉ሦስቱን ወንድማማቾች ያገናኘው ጨዋታ

በ5ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ከሰበታ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ሦስት ወንድማማቾችን በተቃራኒ ያገናኘ ነበር።

አቡበከር ናስር እና ሬድዋን ናስር ኢትዮጵያ ቡናን ሲወክሉ ምንም እንኳን በጨዋታ ዕለት ስብስብ አይካተት እንጂ ታላቃቸው ጅብሪል ናስር ደግሞ በሰበታ ከተማ ወገን ሆነው ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በኢትዮጵያ ቡና 3-2 የበላይነት በተጠናቀቀው ጨዋታ አቡበከር ናስር ሁለት ግቦችን ለኢትዮጵያ ቡና አስቆጥሮ ታናናሾቹ አቡበከርና ሬድዋን ታላቅ ወንድማቸው ላይ ድል እንዲቀዳጁ አስችሏል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንትም ሶስቱን የጉግሳ ልጆች ባገናኘው ጨዋታ ሽመክት ጉግሳ ታናናሾቹ ቸርነትና አ

ንተነህ ጉግሳን በተመሳሳይ የ3-2 ውጤት ማሸነፉ ይተወሳል።

👉የተነቃቃው ታፈሰ ሰለሞን

በሀገራችን እግርኳስ ባለፉት ዓመታት በቴክኒኩ ረገድ ጥሩ አቅም እንዳላቸው ከሚታወቁ ተጫዋቾች መካከል የሆነው ታፈሰ ሰለሞን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአንድ ጨዋታ ጥሩ በሌላው ደግሞ መጥፎ ቀን ማሳለፍ መገለጫው እስከመሆን ደርሶ ነበር።

በኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው አማካዩ ዘንድሮ በተሻለ የተነቃቃ የውድድር ዘመን ጅማሮን እያደረገ ይገኛል። እስካሁን አንድ ግብ በስሙ ማስመዝገብ የቻለው አማካዩ በጎሎች ላይ ያለው ተሳትፎም ካለፉት ዓመታት የተሻለ ይመስላል። በሰበታው ከተማ ጨዋታ ለአቡበከር ናስር የመጀመሪያ ግብ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴውን በማስጀመር ቁልፍ ሚናን ሲወጣ አቡበከር ናስር ላስቆጠራት የመጨረሻ ግብም ኳሷን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ከፕሮፌሽናሊዝም አስተሳሰብና ከፍላጎት አንፃር ጥያቄ ይነሳበት የነበረው አማካዩ ዘንድሮ ሊጉን የጀመረበት መንገድ ግን ተስፋ ሰጪ የሚባል ነው።

👉መፍትሔ የታጣለት የተጫዋቾች አጉራዘለልነት

እርግጥ ነው በሀገራችን እግርኳስ በዳኞች የሚወሰኑ ውሳኔዎች ተከትሎ ዳኞችን መክበብ እና ማዋከብ ባስ ሲልም ለፀብ መጋበዝ የተለመደ ድርጊት ነው። በጉዳዩ ዙርያ ለዓመታት ብዙ ተብሏል፤ ነገርግን ይህ ነው የሚባል መሻሻል ሜዳ ላይ መመልከት አልቻልንም።

ዘንድሮም እንደቀደሙት አመታት ሁሉ መሰል አጉራዘለል ድርጊቶችን እየታዘብን እንገኛለን። በዚህኛው ሳምንት ባህርዳር ከተማ ከፋሲል ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በባህር ዳር ከተማ በኩል ሁለት ተጫዋቾች በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግደዋል።

ቢጫ ካርዶቹን የተመለከቱበትን መንገድና ተገቢነቱን ወደ ጎን ትተን ሁለተኛ ቢጫ ካርዳቸውን ከተመለከቱ ወዲህ የነበረው ሒደት ብቻ ብንመለከት አንድ በከፍተኛ ደረጃ እግርኳስን ከሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚጠበቅ አይደለም።

በቪድዮ የታገዘ የዳኝነት ሒደት በሌበት የሀገራችን እግርኳስ በዳኞች የተወሰኑ ውሳኔዎች ምንም እንኳን ስህተት ቢኖረም የመጨረሻ በሆነበት አግባብ ከካርዶቹ በኋላ የሚታዩት ማዋከቦችና ዳኞችን መጎነታተልና ሌሎች ረብ የለሽ ድርጊቶች አሁንም ትኩረት ይሻል።

አክሲዮን ማኅበሩም ሆነ ክለቦች እንዲሁም የዲሲፕሊን አካል ይህን ድርጊት በመዋጋት ረገድ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን በመውሰድ በእግርኳሳችን የገነገነውን ይህን ጉዳይ እንዲታረም ሊሰሩበት ይገባል።

👉በድጋሚ ስህተት የሰራው ሀሪስተን ሄሱ

ከ2008 የውድድር ዘመን አንስቶ በኢትዮጵያ ፕሪምየር በግብ ጠባቂነት እያገለገለ የሚገኘው ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ሀሪስተን ሄሱ የሚሰራቸው ተደጋጋሚ ስህተቶች ቡድኑን ዋጋ ማስከፈላቸውን ቀጥለዋል።

በኢትዮጵያ ቡና በነበረው ቆይታ ተደጋጋሚ ስህተቶች ይሰራ የነበረው ግብጠባቂ በባህርዳር ቆይታው በዚህ ግዴለሽነቱ ቀጥሎበታል። በተሰረዘው የውድድር ዘመን በተለይ ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ከመጫወቱ በፊት በዕለቱ ጨዋታውን ከመራው የመሀል ዳኛው ቴዎድሮስ ምትኩ ጋር ከለበሰው የመለያ ቀለም ጋር በተያያዘ በፈጠረው ሰጣ ገባ ከጨዋታ በፊት በቀይ ካርድ መሰናበቱ በቅርብ የምናስታውሰው ክስተት ነበር።

ይህ ቤኒናዊ የግብ ዘብ ዘንድሮም ይሄ እጅግ ከልክ ባለፈ የራስ መተማመን በሚሰራቸው የግዴለሽነት ስህተቶች ባህር ዳር ከተማ ለተከታታይ ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት ውጤት ለማጣቱ ምክንያት ሆኗል። ባለፈው ሳምንት ቀላል የቅጣት ምት ኳስን መቆጣጠር ባለመቻሉ ቡድኑ በወልቂጤ እንዲሸነፍ ምክንያት ሲሆን በዚህኛው ሳምንት ደግሞ የቡድን አጋሮቹ በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር በከፍተኛ ተጋድሎ ከተጠባቂው የፋሲል ከነማ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት በተቃረቡበት አጋጣሚ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሳጥን ውጭ የተመታበትን ኳስ በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሉ በተቆጠረበት ግብ ቡድኑን ነጥብ እንዲጋራ አስገድዷል።

ባህር ዳር ከተማዎች በስብስባቸው ውስጥ በተጠባባቂ ግብ ጠባቂነት በሀገራችን እግርኳስ ተስፋ ከተጣለባቸው ወጣት ግብ ጠባቂዎች አንዱ የሆነው የቀድሞውን የአርባ ምንጭ ከተማ ግብ ጠባቂ ፅዮን መርዕድን እንደመያዛቸው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በዚህ ወጣት ግብ ጠባቂ ላይ እምነት በማሳደር በቋሚነት በጎሉ መካከል ለመጠቀም የሚያጤኑበት ወቅት ላይ የደረስን ይመስላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ