የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-1 ባህር ዳር ከተማ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት የከሰዓት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል። 

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)

ስለ ጨዋታው

ባለፉት ሁለት ጨዋታ ማሸነፍ ባለመቻላችን የዛሬ ጨዋታን ማሸነፍ እንፈልግ ስለነበር የመጀመርያ አርባምስት ተጫዋቾቼ ከጭንቀት ጋር ስለነበሩ ትንሽ ተቸግረን ነበር። ያም ቢሆን የመጀመርያው አጋማሽ ተጭነን እንደመጫወታችን ጎል ማስቆጠር ሲገባን አብክነናል። ከዕረፍት መልስ ጎል አስቆጥረን ሁለተኛ ለማክል ነበር አልተሳካልንም። በአጠቃላይ ስላሸነፍን ደስ ብሎኛል። ለጀማው ጨዋታ ተጫዋቾቼን በአካልም በአዕምሮ ለማዘጋጀት ጨዋታውን ማሸነፍ ነበረብን።

ከጅማው ውድድር ምን እንጠብቅ?

ሁሌም ነው የምለው። እያንዳንዱ ጨዋታ እየተዘጋጀን እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፍ እንሞክራለን። ዛሬም ማሸነፋችን ደረጃችን ከፍ ብሎ በፉክክር ውስጥ ለመቆየት ያግዘናል። ጅማም ሄደን ይሄን ጉዛችንን እንጠብቃለን።

አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመልሳን ድሬደዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው

ዛሬ በአጠቃላይ ጥሩ አልነበርንም። ከዕረፍት በፊትም ከዕረፍት በኃላም ቡድናችን ጥሩ አልነበረም። አንድ ሁለት ተጫዋች ሳይሆን ከግብጠባቂው ውጭ ሁሉም ጥሩ አልነበሩም። በአጠቃላይ በሁለታችን በኩል ጨዋታ ያልታየበት ጎል ከገባ በኃላ ብዙ የሚወድቁ ተጫዋቾችን የምናይበት ጨዋታ ነበር። ህዝብ የሚደሰትበት ጨዋታ አልነበረም።

የውጭ ተጫዋቾች አለመኖር ተፅዕኖ?

ምንም ጥያቄ የለውም። ምክንያቱም የቡድኔ አጨዋወት በመልሶ ማጥቃት ፈጥኖ ጎል ላይ በመድረስ ነው የምንታወቀው። ዛሬ እኔጃ ሁለት ጊዜ ጎል ላይ መድረሳችንን አላስታውስም። ፊት ላይ የነበሩት ተቀይረውም የገቡት ለውጥ አልነበረም። በአጠቃላይ ዛሬ ቡድኔ ጥሩ አልነበረም።

ስለ ጅማ ጉዞ

አሁን ላይ የውጭ ተጫዋቾቻችን ያላለቀላቸው የወረቀት ጉዳይ በዚህ ዘጠኝ ቀን ውስጥ ያልቃል። የተጎዱም በህክምና ላይ የሚገኙ በተለይ የመስመር ተከላካዮች ዛሬ የተጫወቱት የመሐል ተከላካዮች ናቸው። ይህም የሆነው ችግሩን ለመፍታት የተደረገ እንጂ አራት የመሐል ተከላካይን ነው ደርድሬ ያስገባሁት። ስለዚህ የተጎዱት ስለሚድኑ በዘጠኝ ቀን ውስጥ የመጀመርያ ቡድኔን ጅማ ላይ አገኘዋለው።

የገና ስጦታ አለ ብለህ ነበር ከጨዋታው በፊት ?

አልተሳካም። እንግዲህ ለሚቀጥለው በዓል አዘጋጃለው። (እየሳቁ)


© ሶከር ኢትዮጵያ