ጅማ ለፕሪምየር ሊጉ ውድድር መሰናዶ አስፈላጊ ዝግጅት ማድረጓን የከተማው ከንቲባው አረጋገጡ

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቀጣይ ምዕራፍ ጅማ ላይ ይካሄዳል። ይህን አስመልክቶ ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን የከተማው ከንቲባ በላኩት ደብዳቤ አረጋግጠዋል።

በቀደሞ ዘመን የአፍሪካ ክለቦች ዋንጫ ጨዋታ እና ሌሎች መርሐ ግብሮች ታዘጋጅ የነበረችው ጅማ ከተማ ከረጅም ዓመት በኃላ የሀገሪቱ ትልቅ ውድድር የሆነው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከሰባተኛው እስከ አስራ አንደኛው ሳምንት ያሉ ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት ዕድሉን አግኝታለች።

ይህን ተከትሎ በቅርቡ ወደ ሥፍራው ያቀናው የሊግ ኩካንያው የልዑክ ቡድን አብዛኛው ከሆቴል አቅርቦት፣ የልምምድ ሜዳ፣ የፀጥታ እና ከኮቪድ ምርመራ ማዕከል ጋር የተያይዙ ጉዳዮች የተሟሉ እንደሆኑ ጨዋታዎቹ የሚደረጉበት የጅማ ዩኒቨርሲቲ መጫወቻ ሜዳ በተወሰነ መልኩ በቀሩት ቀናት ማስተካከያ እንዲደረግበት ምክረ ሀሳብ ሰጥቶ እንደተመለሰ መዘገባችን ይታወቃል።

ይህን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ የመጫወቻው ሜዳ የማስተካከያ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ እና በቀሩት ጥቂት ቀናት ሙሉ ለሙሉ ለጨዋታ ዝግጁ እንደሚደረግ ለማወቅ ችለናል። የከተማው ከንቲባ አቶ ቲጃኒ በበኩላቸው ጅማ ከተማ ይህን ትልቅ ውድድር እንግዶቿን ተቀብላ ውድድሩን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ለሊግ ኩባንያው በላኩት የማረጋገጫ ደብዳቤ አሳውቀዋል።

አብዛኛው ቡድኖች አስቀድመው የሚያርፉበትን ሆቴል የያዙ ሲሆን ከሰኞ ጀምሮ ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ይሆናል። ጨዋታውን በቀጥታ በቴሌቪዥን የሚያሰራጨው የሱፐር ስፖርት የቡድን አባላትም በሚቀጥለው ሳምንት የመጀመርያ ቀን ወደ ስፍራው የሚጓዙ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ