ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ እና ሶዶ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ አንደኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በሀላባ ከተማ እና ወላይታ ሶዶ ከተማ መካከል ተደርጎ 1 ለ 1 ተጠናቋል፡፡

በቅርቡ ህይወታቸው ላለፈው የቀድሞ ዓለም አቀፍ ዳኛ ዓለም ነፀበ የህሊና ፀሎት ተደርጎ ነበር ከተያዘለት አሰር ደቂቃ ቀደም ብሎ የጀመረው። ለዕይታ ሳቢ በነበረው ጨዋታ ክለቦቹ ኳስን መሠረት ያደረገ የማጥቃት እንቅሰሰቃሴ ሲከተሉ የነበረ ሲሆን በተሻጋሪ ኳሶች ጫናን በመፍጠሩ እንዲሁም ወደ ግብ በመድረሱ ሶዶ ከተማዎች የሚስተካከላቸው አልነበረም። ለዚህም ገና በ2ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯት ጎል ማሳያ ናት፡፡ጥላሁን በቶ በቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ የቀድሞው የወላይታ ድቻ አጥቂ አላዛር ፋሲካ በግንባር ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ በቀኝ መስመር አዘንብለው በአቡሽ ደርቤ ቀስ በቀስ ማጥቃት የጀመሩት ሀላባዎች የኳሳቸው ፍሰት ወጥ ባለመሆኑ የሚቆረጡ የቅብብል ሂደቶች በቶሎ በሶዶ ከተማ ተጫዋቾች እየተነጠቁ በመልሶ ማጥቃት ሲጠቁ አስተውለናል፡፡ ሆኖም አቡሽ ደርቤ ከርቀት አክርሮ መቶ ኤልያስ ዘ አማኑኤል በያዘበት አጋጣሚ ሀላባዎች ወደ ግብ መጠጋት ችለዋል፡፡ ከሀያ ደቂቃዎች በኃላ በአንድ ሁለት ቅብብል ሀላባዎች ወደ መጫወቱ የገቡ ሲሆን ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀሙ ረገድ ደግሞ ሶዶ ከተማ ተጠቃሽ ነው። ሶዶ ከተማዎች በተደጋጋሚ ሲያደርጓቸው የነበሩት የግራ እና ቀኝ ረጃጅም ኳሶች ለሀላባ ከተማ ከብደው የታዩ ሲሆን በአጋማሹም ደካማ የማጥቃት ሒደት የነበረው ሀላባ 1 ለ 0 እየተመራ አጋማሹ ተገባዷል፡፡

ከእረፍት መልስ ሀላባዎች አቻ ለመሆን ያሰቡ በሚመስል መልኩ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው ካስገቡ በኃላ መጠነኛ መነቃቃት ቢታይባቸውም ወጥነት የሌለው የመቀባባል አጨዋወታቸው ነጣቂ ለነበሩት ሶዶዎች አልከበዷለውም፡፡ 47ኛው ደቂቃ ላይ የሶዶው ተከላካይ ሮቦት ሰለሎ በግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አቡሽ ደርቤ ቢመታውም የሶዶው ግብ ጠባቂ ኤልያስ አድኖበታል፡፡

አሁንም ግብ አስቆጠሮ አቻ ለመሆን ታታሪነት የታየባቸው ሀላባ ከተማዎች ምንም እንኳን ብልጫ መውሰድ ባይችሉም አቻ ለመሆን ያገዳቸው አልነበረም፡፡ 57ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል ቴዎድሮስ ወልዴ ሲያሻማ ፉአድ አቢኖ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ አቻ ውጤት አሸጋግሯል፡፡

በቀሪዎች ደቂቃዎች የደመቀ የሜዳ ላይ የጨዋታ ፉክክርን ያየንበት እና አጋጣሚዎች በግልፅ የተገኙበት ነበር። 60ኛው ደቂቃ ላይ የሀላባው ሰለሞን ብሩ በግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የእለቱ ዳኛ ለሶዶ የፍፁም ቅጣት ምት ቢሰጡም አላዛር ፋሲካ መቶ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል፡፡ ከዚህች የፍፁም ቅጣት ምት ውጪም አላዛር ፋሲካ በጨዋታ የተገኘችን ዕድል አምክኗል፡፡ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ በቀረበት ወቅት ልመንህ ታደሰ ሀላባን አሸናፊ የምታደርግ የግንባር ኳስ አግኝቶ የሶዶው ግብ ጠባቂ በሚገርም ብቃት አምክኖበታል፡፡ ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳንመለከትበት 1ለ 1 ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ