ከፍተኛ ሊግ | አቃቂ ቃሊቲ፣ ጋሞ ጨንቻ እና ኮልፌ ቀራኒዮ አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የመጀመርያ ሳምንት በሀዋሳ ሲቀጥል የምድብ ሐ በድሬዳዋ ዛሬ ተጀምሯል።
ሻሸመኔ ከተማ ከ ካፋ ቡና

ጠዋት 2:00 ላይ ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የሻሸመኔ ከተማ እና ካፋ ቡና ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ሜዳ ላይ መገኘት ቢችሉም ሻሸመኔዎች የኮቪድ 19 የምርመራ ውጤትን ይዘው ባለመገኘታቸው ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ በዚህም መሠረት በጤና ህጉ የፕሮቶኮል መመሪያ መነሻነት ካፋ ቡና በቀጣዮቹ ቀናት በደብዳቤ የጨዋታ አሸናፊነቱ በፎርፌ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አቃቂ ቃሊቲ 4-0 ጅማ አባቡና

በመቀጠል 4፡00 ሲል ሁለተኛ የምድቡ ጨዋታ ጀምሯል፡፡ ጅማ አባቡናን ከ አቃቂ ቃሊቲ ያገናኘው ጨዋታም በአቃቂ 4 ለ 0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡በሊጉ እስካለፈው ዕርብ ድረስ እንደማይሳተፉ ሲነገር የሰነበቱት ጅማ አባ ቡናዎች በኦሮሚያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥረት ትናንት አመሻሽ ሀዋሳ በመግባት የኮሮና ምርመራን በአፋጣኝ ካደረጉ በኃላ ነበር የዛሬውን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት።

ፈጣን የመልሶ ማጥቃት በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን ይዘው ለመጫወት ሁለቱም ቢሞክሩም የአቃቂዎች ጨራሽነት ግን የደመቀበት ነበር፡፡ በዚህም 4ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል አየለ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ አሁንም የሜዳውን የጨዋታ መንገድ የተረዱት አቃቂዎች ከስድስት ደቂቃዎች በኃላ ሄኖክ አየለ የአባቡናን የመከላከል ስህተት ተመልክቶ ሁለተኛ ግብን አክሏል፡፡

ወደ ጨዋታ ለመመለስ እና ግብ ለማስቆጠር አባቡናዎች ትጋት ቢታይባቸውም የአጥቂያቸው ተምኪን ፈቱ ተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ መሆን እና ደካማ የሆነው የአጨራረስ ድክመት ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ 40ኛው ደቂቃ ናድር ሙባሪክ ከታዲዮስ አንበሴ መሀል ለመሀል የተላከለትን ኳስ ወደ ግብነት በመለወጥ የክለቡን የግብ መጠን ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል፡፡ በዚህም ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

የዕለቱ ዳኛ ፊሽካቸውን ባሰሙበት ቅፅበት የአቃቂው አጥቂ ብሩክ ሰሙ የአባቡናውን ተከላካይ ይርጋለም ዓለሙን ወደ መልበሻ እያመራ እያለ በግንባሩ በመማማቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ የዕለቱ ረዳት ዳኛ ለዋና ዳኛው ባደረጉት ጥቆማ ከሜዳ ተወግዷል፡፡

ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ የቀዘቀዘ እንዲሁም ረጃጅም ተሻጋሪ ኳሶች የበዙበት ሲሆን አብዛኛዎቹም ብኩኖች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከግብ ጋር ጥሩ ቁርኝት የነበራቸው አቃቂዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ በዳዊት ተፈራ አማካኝነት አራተኛ ጎላቸውን አስቆጥረው ጨዋታው በቀሪ ደቂቃዎች ምንም የጠሩ ዕድሎች ሳይታይበት 4 ለ 0 ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ቤንች ማጂ ቡና 0-1 ጋሞ ጨንቻ

10:00 ሲል ቤንች ማጂ ቡናን ከጋሞ ጨንቻ ያገናኘ ጨዋታ ነበር፡፡ የረባ የጨዋታ ቅርፅ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ረጃጅም ኳስ የበዛበት እንዲሁም ደግሞ ለዕይታ ብዙም ሳቢ ያልነበረ ቢሆንም የሁለቱ ክለቦች የማስቆጠር ፍላጎት ግን ማየት የቻልንበት ነበር፡፡ ቡድኖቹ ኳስን ሲይዙ በተደጋጋሚ መቆራረጦች የሚታዩበት እንደሆነ መመልከት ብንችልም አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ረገድ ጋሞ ጨንቻ የተሻለ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽም አንድ ንፁህ ዕድልን አግኝተው ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ ተብልባቸዋል፡፡

የዳኛን ውሳኔ በየደቂቃው ተቃውሞዎች በተደጋጋሚ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ አቻ ፍለጋ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች የታዩበት ነገር ግን መሀል ሜዳቸው ላይ መሻሻልን አሳይተው ለገቡት ጋሞ ጨንቻዎች እፎይታን የፈጠረ አጋማሽ ነበር፡፡ ተደጋጋሚ የተጫዋቾች የእርስ በእርስ ጥፋቶች በሜዳው ላይ መታየቱ በተወሰነ መልኩ ይህን ክፍለ ጊዜ ቀዝቃዛ ያደረገው ሲሆን 64ኛው ደቂቃ ላይ ወጣቱ አጥቂ ዘላለም በየነ የቤንች ማጂ ተከላካዮችን ስህተት ተመልክቶ ያስቆጠራት ጎል ጋሞ ጨንቻን 1 ለ 0 አሸናፊ አድርጎ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

ጌዴኦ ዲላ 0-2 ኮልፌ ቀራኒዮ

የምድብ ሐ ውድድር አስቀድም እንዲካሄድ መርሐ ግብር የተያዘለት ጅማ ቢሆንም ከፕሪምየር ሊጉ ፕሮግራም ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ወደ ድሬዳዋ እንዲያመራ ተደርጎ ከሌሎቹ በሁለት ቀናት ዘግይቶ እንዲጀምር ተደርጓል። ዛሬ የመክፈቻ ጨዋታ በጌዴኦ ዲላ እና ኮልፌ ቀራኒዮ መካከል የተከናወነ ሲሆን ኤርሚያስ ዳንኤል ከእረፍት በፊት በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ሙሉዓለም በየነ በጨዋታ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ኮልፌ 2-0 ማሸነፍ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ