ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ በረድኤት አስረሳኸኝ ጎሎች ጌዲኦ ዲላን አሸንፏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ረፋድ 4:00 በገና በዐል ዕለት ሀዋሳ ከተማን ከጌዲኦ ዲላ አገናኝቶ በሀዋሳ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ሳቢ በነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ጌዲኦ ዲላዎች በቅብብል ወደ ሳጥን ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ሲደርሱ ጠጣር የነበረውን የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል ለማለፍ ያላቸው ጥረት ደካማ በመሆኑ ከርቀት ያገኟቸውን ሙከራዎች ለመሞከር ተገደዋል፡፡ ከግራ መስመር አስፈሪ እንቅስቃሴን በማድረግ ለጌዲኦ ዲላ የማጥቂት ሀይል ጉልበት የሆነችዋ አይደክሜዋ እፀገነት ግርማ ከግራ መስመር አክርራ መታ ዓባይነሽ ኤርቄሎ የያዘችባት እንዲሁም ከቅጣት ምት መንደሪን ክንዲሁን በቀጥታ መታ በተመሳሳይ አባይነሽ የያዘችባት የቡድኑ ጠንካራ የርቀት ሙከራዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ሲስተም በመመለስ ከመስመር እና ከመሀል ተሰላፊዎቹ ዮዲት መኮንን እና ትውፊት ካዲኖ ኳሶች ወደ አጥቂዎች በሚጣሉ ዕድሎችን ወደ መፍጠሩ የገቡት ሀዋሳ ከተማዎች 27ኛው ደቂቃ በዚህ የጨዋታ መንገድ የተገኘን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጠዋል፡፡ ዮዲት መኮንን ለነፃነት መና ሰጥታት ነፃነትም መሐል ለመሀል ሰንጥቃ የሰጠቻትን ረድኤት አስረሳኸኝ የቀድሞው ክለቧ ላይ ግብ አስቆጥራ ሀዋሳን መሪ አድርጋለች፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ይበልጥ ንቃት በውስጣቸው የታየው ዲላዎች በእፀገነት ግርማ ተደጋጋሚ የርቀት ኢላማቸውን የጠበቁ ኳሶች ጥቃቶችን ሰንዝረዋል፡፡እፀገነት ግርማ ሁለት ጊዜ ሞክራ አንደኛውን ግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ስትመልስባት ሁለተኛው ሙከራ ከቅጣት ም ሞክራ የግቡ የላይኛው ቋሚ ብረት ሲመልሰው ሰለማዊት ጎሳዬ የተመለሰውን ኳስ በድጋሚ አግኝታ ሳትጠቀምበት ቀርታለች፡፡

ከእረፍት መልስ ጌዲኦ ዲላዎች አቻ ለመሆን በንክኪ ወደ አጥቂዋ ቱሪስት እና በቀኝ በኩል ወደ እፀገነት በሚጣሉ ኳሶች አድልተው ሲጫወቱ የነበረ ሲሆን ነጻነት መና ሀዋሳዎችም በተመሳሳይ በተሻጋሪ ኳሶች ረድኤት አስረሳኸኝን ማዕከል ያደረገ አጨዋወትን ተከትለዋል፡፡ ሁለቱም ክለቦች ኳስን በሚይዙበት ጊዜ በንክኪ ወደ ጎል ለመድረስ ሲያደርጉት የነበረበት ጥረት እጅግ ማራኪ ነበር፡፡

ምስር ኢብራሂም ቀይረው ካስገቡ በኃላ ይበልጥ የአጥቂ ክፍላቸውን ያጠናከሩት ሀዋሳ ከተማዎች በዚህኛው አጋማሽ የተሻሉ ዕድሎችን አግኝተውበታል፡፡ ምስር ተቀይራ ከገባች በኃላ ሦስት ጊዜ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ያመከነቻቸው አስፈሪ ሙከራዎች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ ሆኖም አቻ ለመሆን ረጃጅም ኳሶቻቸው የጨዋታ መንገዳቸውን ምቹ ያደረገላቸው ጌዲኦ ዲላዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የሆኑበትን አጋጣሚ ማግኘት ችለዋል፡፡ ከቅጣት ምት መንደሪን ክንዲሁን ወደ ጎል አክርራ የመታቻት ኳስ የግቡን የላይኛው ብረት ነክቶ ሲመለስ የሀዋሳ ተከላካዮች ኳስን ለማራቅ የነበራቸው ዕድል የጠበበ በመሆኑ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረችው እፀገነት ግርማ ወደ ጎልነት ለውጣ ጌዲኦ ዲላን አቻ አድርጋለች፡፡

በይታገሱ ተገኝወርቅ እና ቱሪስት ለማ ሌላ ዕድል አግኝተው መጠቀም ያልቻሉት ዲላዎች በመጨረሻ እጅ ሰጥተዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ረድኤት አስረሳኽ ለራሷም ለክለቧም በድንቅ አጨራረስ ጎል አስቆጥራ ሀዋሳን 2 ለ 1 አሸናፊ አድርጋለች፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ለሀዋሳ ሁለት ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈችው ረድኤት አስረሳኸኝ የልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታው ኮከብ ተብላ ተሸልማለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ