ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የሳምንቱ ዐበይት ጉዳዮች አካል በሆነው የአሰልጣኞች ትኩረት በዚህ ሳምንት የታዩ አንኳር ጉዳዮች እና ዋና ዋና አስተያየቶችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

👉 ሽክ በሀገር ባህል ልብስ – አሸናፊ በቀለ

በዕለተ ገና ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ የሀዲያ ሆሳዕናው ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በእግር ኳስ ሜዳ ባልተለመደ መልኩ ነጭ በነጭ የሀገር ባህል ልብስ ሽክ ብለው በሜዳው ጠርዝ ተመልክተናቸዋል።

ከቀናት በፊት በአሰልጣኞች ትኩረታችን ላይ “ሽቅርቅሮቹ አሰልጣኞች” በሚል ሙሉ ልብስ ስለሚለብሱ አሰልጣኞች ሀሳቦችን አንስተን የነበረ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ በሜዳው ጠርዝ ሽክ ብሎ መገኘትን አንድ ደረጃ ወደፊት ከፍ አድርገውት በዕለተ ገና በሀገርኛ አለባበስ እምር ብሎባቸው ውለዋል። አሰልጣኙ ስለ አለባበሳቸው ከጨዋታው በፊት ከሱፐር ስፖርት ጋር ባደረጉት ቆይታ “ዐውደ ዓመት እና እግር ኳስ አንድ ናቸው።” የሚል ይዘት ያለው ንግግራቸውም ትኩረት የሳበ ነበር።

ጨዋታው በዲኤስ ቲቪ እየተላለፈ ከመሆኑ አንፃር በአዳዲስ ተመልካቾች ዘንድ ሊጋችንን ከሌሎቹ ሀገራት በቶሎ እንዲለዩ ከሚያደርጉ እግር ኳሳዊ ጉዳዮች በተጨማሪ እንዲህ ዓይነት ሌሎች ገፅታዎቻችንን የሚያሳዩ ተሞክሮዎችም የሚበረታቱ ናቸው።

👉የማሒር ዳቪድስ አዲስ ሌላ ማንነት

እስከ 6ኛው ሳምንት መርሐ ግብር ድረስ ደቡብ አፍሪካዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ማሒር ዳቪድስ በሜዳው ጠርዝ እጅግ የተረጋጉ እና ቁጥብ የሆነውን ማንነታቸውን ስንመለከት ቆይተናል።

ነገርግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና በሸገር ደርቢ በተረቱበት ጨዋታ ግን በተለይ ከማታሲ ቀይ ካርድ በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ግን እጅግ ስሜታዊ ሆነው ሲቅበጠበጡ ፣ ቡድናቸውን በስሜት ሲመሩ ብሎም ከቡድናቸው በተቃራኒ የሚወሰኑ የዳኝነት ውሳኔዎችን ሲቃወሙ ተመልክተናል።

እርግጥ ጨዋታው የደርቢ ጨዋታ እንደመሆኑ አለፍ ሲል ቡድናቸው በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ለ80 ደቂቃዎች ለመጫወት መገደዱ ራሳቸውንም ያለ ወትሯቸው ቀበጥባጣ ቢያደርጋቸው ይፈረድባቸዋልን?

👉 ትችት በሰነዘረባቸው የግብ አግዳሚና ቋሚ ከጉድ የወጣው ፍሰሀ ጥዑመልሳን

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ወላይታ ድቻን 2-1 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ቡድኑ እስካሁን 13 ያክል ኳሶች በአግዳሚ እና ቋሚ እንደተመለሰባቸው እና ለዚህም የግብ አግዳሚ እና ቋሚዎች አሰራር ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ሲል የተደመጠው አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን በዚህ ሳምንት በእነዚሁ አግዳሚ እና ቋሚ በባህር ዳር ከተማ ከአንድ ጎል በበለጠ ሽንፈት ከማስተናገድ ተርፏል።

በባህርዳር ከተማ 1-0 የበላይነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ባህርዳር ከተማዎች ሦስት ሙከራዎቻቸው የግቡ አግዳሚ እና ቋሚን ለትመው ሊወጡባቸው ችለዋል። ታድያ እግር ኳስ እንዲህ ነው እንዲሉ በቀደሙት ሳምንታት ሙከራዎች በአግዳሚ እና ቋሚዎች ሲከሽፍባቸው የነበሩት ድሬዎች አሁን ባለተራ ሆነው ከጉድ ድነዋል።

👉ለደጋፊዎቻቸው ቅርብ የሆኑ አሰልጣኞች

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች ውስጥ ጅማ ከሰበታ አቻ ከተለያየበት እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን ከረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እና ጳውሎስ ጌታቸው ከደጋፊዎች ጋር የነበራቸው ቆይታ በልዩነት የሚታይ ነበር።

አሰልጣኝ ጳውሎስ የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ አውቶብሳቸው ሲያመራ በተወሰኑ ደጋፊዎች እና በጃኮ ፔንዜ መካከል የነበረውን አለመግባባት ለማርገብ ደጋፊዎችን ቀርቦ ጉዳዩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት የሚበረታታ ሲሆን በአንፃሩ ሙሉጌታ ምህረት ከሀዋሳ ቡድኑን ለማበረታት ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከነበሩ የቡድኑ ደጋፊዎች ጋር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የነበረው ወንድማዊ ቆይታ ሌላኛው ነበር።

በአንድ የእግርኳስ ክለብ ዙርያ ያሉ አካላት በሙሉ እንደ አንድ ቤተሰብ አባል ተጋግዘው እና ተደጋግፈው መጓዝ ከቻሉ ቡድኑ ወደ ውጤት በሚያደርገው ጉዞ ወሳኝ ሚናን መወጣት እንደሚችሉ ይታመናል። በመሆኑም መሰል ለደጋፊዎቻቸው ሆነ ለሌሎች በቡድኑ ዙርያ ላሉ አካላት ቅርበት ያላቸው አሰልጣኞችን ማበረታታት ይገባል።

ዓበይት አስተያየቶች

👉ማሒር ዴቪድስ ከደርቢው ጨዋታ በቀጣይ መውሰድ ስላለባቸው ጉዳይ…

“ተጫዋቾቹ ኃላፊነት ወስደው የተጫወቱበት መንገድ እጅግ ድንቅ ነው። በሰራነው ስህተት ግብ አስተናግደናል፤ እርግጥ ነው ተሸንፈናል። ነገር ግን ወደ ፊት ማሰብ ይኖርብናለ። ውድድሩ በዛሬው ዕለት አይጠናቀቅም። ከጨዋታው በፊትም እንዳልኩት ከጨዋታው ሦስት እንጂ አራት ወይንም አምስት ነጥብ አይገኝም። ስለዚህ በዛሬው ዕለት የነበረውን ብቃት ለቀጣይ ጨዋታዎች መውሰድ ይኖርብናል።”

👉ካሣዬ አራጌ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ድል…

“ውጤቱ ጥሩና የምንፈልገው ነበር። በመሠረቱ ሁሉንም ጨዋታ ለማሸነፍ ነው የምንገባው፤ ጨዋታውም ጥሩ ነበር። እነሱ ገና በጊዜ ነበር አንድ ተጫዋች በቀይ የወጣባቸው። ስለዚህ ያንን ትርፍ ሰው ለመጠቀም ነበር ያሰብነው። መጀመሪያ ላይ ትንሽ መዘናጋት ነበር። ተጫዋች ቢወጣባቸውም እንዲጫወቱ ቦታና ጊዜ ፈቅደንላቸው ነበር። ከዕረፍት መልስ ግን ያንን ክፍተት በመድፈን ያገኘነውን የሰው ብልጫ በአግባቡ ተጠቅመን ለማሸነፍ ነበር የገባነው። በዚህም በመጨረሻ ተሳክቶልናል።”

👉ጫና ውስጥ የሚገኙት ሥዩም ከበደ ኃላፊነታቸውን ሰለማጣት..

“የሚባለው ነገር ለእኔም እንቆቆልሽ ነው። እስካሁን ማኔጅመንቱ ፣ ተጫዋቾቹ እና ቴክኒክ ስታፉ ሁሉም ከጎኔ ነው ያሉት። በእርግጥ ውስን ግለሰቦች የራሳቸው ስሜት ሊኖራቸው ይችላል፤ ትልቁ እና የሚቀድመው ግን ፋሲል ነው። የፋሲል አሰልጣኝ ሆኜ እየሰራሁ ሳለ የምሸኝ ከሆነም በክብር ነው መሸኘት ያለብኝ እንጂ ማንም እንደፈለገ የሚያደርግበት መንገድ የሚኖር አይመስለኝም። ለቡድኑ ካልጠቀምኩ የሥራው አካል እስከሆነ ድረስ መልቀቄ ምንም ችግር የለውም። ነገር ግን አሁንም ለክለቡ ትልቅነት ከአመራሮችም፣ ከተጫዋቾቹም፣ ከስታፉም ጋር በመሆን የምችለውን እየሰራሁ ነው። እንደዛ ሊታሰብ ቢችልም እኔ ግን እንደዛ አስቤው አላውቅም።”

👉 አሸናፊ በቀለ ከተከታታይ ድል በኃላ ነጥብ ስለመጋራት…

“ወደ ውድድሩ ስንገባ አንዳችም የወዳጅነት ጨዋታ አላደረግንም። ይህንን እንደወዳጅነት ጨዋታ ነው የምናየው። ምን ጥሩ ነገር ነበር ? ምን ደካማ ጎን ነበር ? ብለን አሁን ቡድኑ እያሳየ ያለው ነገር ጥሩ ስለሆነ ለተሻለ ውድድር ነው የምንሄደው። ትልቁ ፍልሚያ የሚጠብቀን በሚቀጥለው ነው ፤ አጨራረሱን ማሳመር ያስፈልጋል።”

👉ፍስሐ ጥዑመልሳን ስለ ባህርዳሩ ጨዋታ…

“ዛሬ በአጠቃላይ ጥሩ አልነበርንም። ከዕረፍት በፊትም ከዕረፍት በኃላም ቡድናችን ጥሩ አልነበረም። አንድ ሁለት ተጫዋች ሳይሆን ከግብጠባቂው ውጪ ሁሉም ጥሩ አልነበሩም። በአጠቃላይ በሁለታችን በኩል ጨዋታ ያልታየበት ጎል ከገባ በኃላ ብዙ የሚወድቁ ተጫዋቾችን የምናይበት ጨዋታ ነበር። ህዝብ የሚደሰትበት ጨዋታ አልነበረም። ምንም ጥያቄ የለውም። ምክንያቱም የቡድኔ አጨዋወት በመልሶ ማጥቃት ፈጥኖ ጎል ላይ በመድረስ ነው የምንታወቀው። ዛሬ እኔንጃ ሁለት ጊዜ ጎል ላይ መድረሳችንን አላስታውስም። ፊት ላይ የነበሩት ተቀይረውም የገቡትም ላይ ለውጥ አልነበረም። በአጠቃላይ ዛሬ ቡድኔ ጥሩ አልነበረም።”

👉ሙሉጌታ ምህረት በቀጣይ ቡድኑ ላይ የሚደረጉ ማስተካከያዎች ስለመኖራቸው…

“በእርግጥ በአሁን ሰዓት ማስተካከያ የምንለው ነገር የለም። የሚቀሩን ነገሮች ላይ ልምምዶችን መስራት ነው። የሊጉ ፉክክር በጣም ከባድ ነው ፤ በፉክክር ውስጥ ለመገኘት መስራት ይኖርብናል። አሁንም ብናሸንፍም ሜዳ ላይ ከምናያቸው ነገሮች ተነስተተን ልምምዶችን ጠንክረን መስራት ይኖርብናል።

👉ደለለኝ ደቻሳ በቀጣይ ጨዋታዎች ቡድኑን ስለማሻሻል…

“ቡድናችን በአብዛኛው በወጣቶች የተገነባ ነው ፤ ለዚህም አዕምሯቸው ላይ ብዙ ሥራዎች መስራት እንዳለብን ይሰማናል። ተጫዋቹ ወደ ራሳቸው እንዲመለሱ እኛም የቡድኑ ደጋፊዎችም ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ