ከፍተኛ ሊግ | ሶዶ ከተማ ጣፋጭ ሙሉ ነጥብ ሲያገኝ ሻሸመኔ እና አዲስ አበባ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ ዛሬ በሀዋሳ ረፋዱን የሁለተኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ሲደረጉ ሶዶ ከተማ ነቀምት ከተማን 3 ለ 1 ሲረታ ሻሸመኔ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ 1 ለ 1 ተለያይተዋል፡፡

ነቀምት ከተማ 1-3 ሶዶ ከተማ

ጠዋት 2:00 ሊደረግ ቀደም ብሎ በመርሀግብሩ ላይ የተገለፀ ቢሆንም አስራስምንት ያህል ደቂቃን ዘግይቶ ነበር መጀመር የቻለው። የነቀምት ከተማ እና ሶዶ ከተማ ጨዋታ የዕለቱ ዳኛ ገና ፊሽካን ካሰሙበት የጅማሮ ደቂቃ አንስቶ የዳኛን ውሳኔ በመቃወም ከበባዎች እና የእርስ በእርስ የሁለቱ ክለብ ተጫዋቾች ግጭቶች በርከተው የታዩበት ነበር፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ነቀምት ከተማዎች በአንድ ሁለት እና በተሻጋሪ ኳስ አጥቅቶ መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ሶዶ ከተማዎች ከተሻጋሪ ኳሶች አጥቂዎቻቸውን ማዕከል በማድረግ የተንቀሳቀሱበት ነበር፡፡ የአንድ ሁለት ቅብብላቸው የሰመረላቸው ነቀምቶች 26ኛው ደቂቃ ላይ ከሚል ረሺድ ግብ አስቆጥሮ ነቀምትን መሪ አድርጓል፡፡

በየደቂቃው ዳኛው በተፈጸሙ ጥፋቶች ልክ በተደጋጋሚ በፊሽካ በማስቆም ጨዋታውን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ተጫዋቾች የዳኛውን ውሳኔ ሲቃወሙበት የነበረበት መንገድ ግን ሊደገም የማይገባው ድርጊት ነው፡፡ በተለይ 44ኛው ደቂቃ ላይ የነቀምቱ አምበል ዘነበ ተንታ በግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የዕለቱ ዳኛ የፍፁም ቅጣት ምት ይሰጣሉ ነገር ግን በዳኛው ውሳኔ ደስተኛ ቢሆንም በእጅ የነካው ዘነበ በሁለተኛ ቢጫ መውጣት አለበት በሚል አተካራ በዳኛው ላይ የሶዶ ከተማ ተጫዋቾች ያልተገቡ የመቃወም ሂደትን ሲያሳዩ አስተውለናል፡፡ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሳምሶን ደጀኔ ቢመታውም የነቀምቱ ግብ ጠባቂ ሶፊያን ኑረዲን አድኗት ወደ መልበሻ አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ፍፁም የተሰጣቸውን ዕረፍት በሚገባ የተጠቀሙ የሚመስሉት ሶዶ ከተማዎች ከተሻጋሪ ኳስ እና በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ሲስተም በይበልጥ ከግብ ጋር ቶሎ ቶሎ መገናኘት የቻሉ ሲሆን የነቀምት ከተማ እንቅስቃሴ ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ የማጥቃት ሀይል በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዘው የታዩ ሲሆን አብዛኛዎቹን የኳሱን ፍሰት መሀል ሜዳው ላይ ገድበው ሲንቀሳቀሱ የታየበት ነበር፡፡ ቡድኖቹ ምንም እንኳን የየራሳቸውን የጨዋታ ይዘት ይዘው ቢታዩም አሁንም በሚሰሩ ጥፋቶች እና ሽኩቻዎች የሚቆራረጡ ኳሶች የበረከቱበት ነበር ማለት ግን ይቻላል፡፡ በአጋማሹ በነቀምት ከተማ ላይ ሙከራን በማድረግ ቀዳሚነቱን ወደ መያዙ የተሸጋገሩት ሶዶዎች 77ኛው ደቂቃ አቻ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል፡፡ መልካሙ ቡኤ በረጅሙ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ቁመተ ረጅሙ ርኾቦት ሰለሎ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል፡፡

ፋታ የለሽ እንቅስቃሴን በማድረግ ለነቀምት ተከላካዮች ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር ፈተና እየሆኑ የመጡት ሶዶዎች ከተሻጋሪ ኳስ አሁንም ሁለተኛ ጎላቸውን አስቆጥረዋል፡፡ 80ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ በኩል ተሸራርፋ የመጣችን ኳስ ከመረብ ጋር አዋህዶ ቡድኑን ከተመሪነት ወደ መሪነት ተሸጋግሯል፡፡ የነቀምት ከተማን የጨዋታ መንገድ ሰብረው የገቡት ሶዶዎች በመልሶ ማጥቃት በተገኘ ዕድል በመደበኛው ደቂቃ ፍፃሜ ላይ በሰለሞን ጌታቸው አማካኝነት ሶስተኛ ጎላቸውን አግብተው ጨዋታው በሶዶ ከተማ 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ሻሸመኔ ከተማ 1-1 አዲስ አበባ ከተማ

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በሻሸመኔ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ መካከል 4:00 ላይ ጀምሯል፡፡ለዕይታ ማራኪ በነበረው በዚህ ጨዋታ ቡድኖቹ ይዘው የገቡትን ታክቲክ ቁልጭ ባለ መልኩ ያየንበት የማጥቃት ፍላጎታቸውን በተሻለ የታየበት ነበር፡፡ የመጀመሪያን አርባ አምስት የሻሸመኔ ከተማ አንፀባራቂ እንቅስቃሴ እና የጎላ የግብ ዕድሎችን ያየንበት አጋማሽ ሲሆን በተለይ ከመሀልም ሆነ ከመስመር የሚልኳቸው ኳሶች ለአዲስ አበባዎች አስቸጋሪዎች ነበሩ፡፡ በተለይ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን አድርገው የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ በተደጋጋሚ ባያመክናቸው ዐደ ጎልነት የመለወጥ ዕድላቸው የሰፋ ይሆን ነበር፡፡ 20ኛው ደቂቃ ላይ ሻሸመኔዎች ካደረጓቸው ጥረቶች በኃላ መሪ ሆነዋል፡፡20ኛወው ደቂቃ ላይ እሸቱ መና ያሻማትን በሀይሉ ወገኔ ወደ ጎል ለውጦ ክለቡን 1 ለ 0 መሪ አድርጓል፡፡

አሁንም ያለመታከት ማጥቃት ላይ ሳይታሙ የቀጠሉት ሻሸመኔዎች በአሸናፊ ባልቻ እና በአሸናፊ ጥሩነህ አማካኝነት ሌላ የግብ ዕድልን አግኝተው የሳምሶን አስደናቂ ብቃት እንዳይቆጠሩ ረድቷቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማዎች ርቤል ግርማ ከርቀት መቶ ብረት ከመለሰበት ውጪ በእንቅስቃሴ ካልሆነ በግብ ሙከራ ላይ ያላቸው አካሄድ ግን ደካማ ነበር፡፡ ሁለቱ ክለቦች ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የአዲስ አበባው ተከላካይ ሳሙኤል አሰፋ በሰራሁ ስህተት በሀይሉ ወገኔ አግኝቶ አስቆጠረው ሲባል ሳምሶን አሰፋ አሁንም አድኖ ጨዋታው 1 ለ 0 ተገባዷል፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ ስህተት አርመው የገቡት አዲስ አበባ ከተማዎች ተጫዋቾችን ቀይረው ካስገቡ በኃላ ጨዋታውን የተቆጣጠሩበት መንገድ አስገራሚ ነበር፡፡ በተለይ መሀል ሜዳ ላይ ተቀይሮ የገባሁ ብዙአየው ሰይፉ ኳሶችን ወደ ማጥቃት ዞን ቶሎ ቶሎ እንዲገቡ ሲያደርግም የነበረበት አጨዋወት ድንቅ ነበር፡፡ ረጃጅም ኳሶችን ላይ ትኩረት ያደረጉት ሻሸመኔዎች ለማጥቃት ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ሲጓዙ በቁጥር አንሰው ስለሚደርሱ ያሰቧቸውን ዕድሎች በአግባቡ ሊጠቀሙ አልቻሉም፡፡ ፍፁም ጥላሁን ባደረጋት ሙከራ ወደ ጎል መጠጋት የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች 81ኛው ደቂቃ ላይ ከፍፁም ጥላሁን የተገኘችን የቅጣት ምት ኳስ ብዙአየው ሰይፉ በግንባር ገጭቶ አዲስ አበባን አቻ አድርጓል፡፡በመጨረሻው ደቂቃ ሻሸመኔዎች በመልሶ ማጥቃት በተገኘ ኳስ በበኃይሉ አማካኝነት ዕድል ቢያገኙም ጎል መሆን ሳትችል ጨዋታው 1 ለ 1 ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ