ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ድሬዳዋ ከተማ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አሳካ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል ተደርጎ በመጨረሻም በድሬዳዋ ከተማ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

10፡00 ሲል የሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሳር ላይ ሁለተኛውን የቀኑን ጨዋታ አስተናግዷል፡፡ ድሬዳዋ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ተጋጣሚ ቡድኖቹ ናቸው፡፡ በእንቅስቃሴ ረገድ ተዳክሞ በታየው እና ተመሳሳይ ይዘት በነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማ በጥልቀት ከመስመር በሚያገኙት አጋጣሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት አርባምንጮች በአንፃሩ ወጥነት ባይታይባቸውም የድሬዳዋን የመከላከል ክፍተት ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡

በመሠረት ወርቅነህ ሙከራ አርባምንጮች ወደ ግብ መጠጋት ቢችሉም ለማጥቃት ያላቸው ጥንካሬ የተቀዛቀዘ በመሆኑ ከዚህች አጋጣሚ ውጪ የጠራ ዕድልን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡የአሰልጣኝ ብዙአየው ጀምበሩው ድሬዳዋ የአርባምንጭን ክፍተት እየተጠቀሙ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት በቀኝ በኩል ባዘነበለ አጨዋወት ወደ ፊት ሲሄዱ ተስተውሏል፡፡ በተለይ ከቀኝ መስመር በመነሳት ፀጋነሽ ወራና ወደ ሳጥን ተጠግታ በመጫወት ስታደርግ የነበረው እንቅስቃሴ እና ቁምነገር ካሳ የአርባምንጭን የተከላካይ ክፍል በመረበሽ ስታደርግ የነበረበት መንገድ በተወሰነ መልኩ ለድሬዳዋ ብልጫ መውሰድ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡

ፀጋነሽ ከቁምነገር ያገኘችሁን በቀጥታ መታ ግብ ጠባቂዋ ድንቡሽ አባ የያዘቻት ከቅጣት ምት ሀሳቤ ሙሶ አክርራ መታ በተመሳሳይ ድንቡሽ የመለሰችባት አጋጣሚ ድሬዳዋ ለመሻሉ ፍንጭ ሰጪ መልካም ሙከራዎች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ይህ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ 36ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጭ ተከላካዮች ባሳዩት ደካማ ቅብብል ጥበበኛዋ አማካይ ማዕድን ሳህሉ የተቋረጠውን ኳስ አግኝታው ጣጣውን ጨርሳ ለቁምነገር ካሳ ሰጥታት አጥቂዋም ወደ ጎልነት ለውጣው ድሬዳዋን መሪ አድርጋለች፡፡ በቀሪው ደቂቃም ምንም ለውጥ ሳይታይ በድሬዳዋ 1 ለ 0 ወደ መልበሻ አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ በነበረው እንቅስቃሴ አርባምንጮች ከመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡበት ቢሆንም ከፊት መስመሩ ላይ የነበራቸው ድክመት ግን እጅጉን ደካማ ነበረ፡፡ ሆኖም በመልሶ ማጥቃት የግራ እና ቀኝ ኮሪደሩን በቀላሉ ሲጠቀሙበት የተስተዋሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በዚህኛው አጋማሽ በቁምነገር ካሳ አማካኝነት ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ቀርበው ታይተዋል፡፡ 65ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ግብ ጠባቂ ሂሩት ደሴ በአርባምንጯ አጥቂ መቅደስ ከበደ ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራችሁን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዋና ዳኛ ምስጋና ጥላሁን የሰጠችውን ፍፁም ቅጣት ምት መሠረት ወርቅነህ በሚገባ ተጠቅማ አስቆጥራ አርባምንጭን አቻ አድርጋለች፡፡

በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ቅርፅ ያለው እንቅስቃሴ ማሳየት ባይችሉም አሰልጣኝ ብዙዓየው ጀምበሩ ያደረገቻቸው ሁለት ቅያሬዎች ቡድኑ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ረድቶታል፡፡ 81ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችሁ እና ከመቐለ ድሬዳዋን ከሰሞኑ የተቀላቀለችሁ ትንቢት ሳሙኤል ከቀኝ በኩል ከሀሳቤ ሙሶ የመጣችን ኳስ አቋቋሟ ጥሩ ለነበረው ፀጋነሽ ወራና አቀብላ የመስመር አጥቂዋም የቀድሞው ክለቧ ላይ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በድሬዳዋ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ድሬዳዋ ከተማም ከሽንፈት መልስ ይሄ ተከታታይ ሶስተኛ ድልም ሆኖለታል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የድሬዳዋ ከተማዋ የተከላካይ አማካይ እታለም አመኑ የጨዋታው ምርጥ ተብላ በልሳን የሴቶች ስፖርት ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ