ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

በ7ኛ ሳምንት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ በሄኖክ አየለ ብቸኛ ግብ አዳማ ከተማን አሸንፏል።

አዳማ ከተማዎች በሀዲያ ሆሳዕና ከተረታው ስብስብ ውስጥ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ዳንኤል ተሾመ ፣ እዮብ ማቲዮስ ፣ ዘሪሀን ብርሀኑ፣ በቃሉ ገነነ እና ፍሰሀ ቶማስ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ሲያካት በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ከሀዲያ ሆሳዕና አቻ የተለያየውን ስብስብ መሉ ለሙሉ በዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የወልቂጤ ደጋፊዎች የወሩ የክለቡ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ለተመረጠው ጀማል ጣሰው የ10,000 ሽልማት ተበርክቶለታል።

ወልቂጤ ከተማ እጅግ የተሻሉ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ ኳስ ተቆጣጥረው ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል በማሳደግ እንዲሁም ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች የግብ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ አዳማ ከተማዎች ተከላክለው ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ ከሚከላከለው የወልቂጤ ተከላካዮች ጀርባ በሚጣል ኳስ ግቦችን ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።

በ2ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወርቁ በአዳማ የመከላከል መስመሮች መሀል ተገኝቶ ያሳለፈለትን ኳስ ተከትሎ ያሬድ ታደሰ አግኝቶ ባመከነው ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ወልቂጤዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የአዳማ ከተማው ግብጠባቂ ዳንኤል ተሾመ የሚቀመስ አልሆነም።

በ16ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወርቁ ከሳጥን ውስጥ ያሻማው ኳስ በትዕግስቱ አበራ ተጨርፉ ወደ ጎል ያመራችውን ኳስ እንዲሁም 25ኛው እና 42ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከሳጥን ውጭ በቀጥታ እንዲሁም ከቅጣት ምት በቀጥታ ያደረጋቸውን ሙከራዎች በተመሳሳይ ዳንኤል ተሾመ በአስደናቂ መልኩ አድኖባቸዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በአዳማ ከተማ በኩል የተደረገው ብቸኛ ሙከራ በ43ኛው ደቂቃ በቃሉ ገነነ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ መሬት ለመሬት ወደ ግብ የላከውና ጀማል ጣሰው በቀላሉ ያዳነበት ሙከራ ብቻ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከጨዋታው ውጤት ይዞ ለመውጣት ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር።

በ50ኛው ደቂቃ የኃላሸት ፍቃዱ ከግራ የወልቂጤ ሳጥን ክፍል የሞከረውና ጀማል ጣሰው በቀላሉ በያዘበት ሙከራ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ71ኛው ደቂቃ በጨዋታው ልዮነትን የፈጠረችው አጋጣሚ ተከስታለች።

በወልቂጤ ሳጥን ጠርዝ የኃላሸት ኳስ ለማቀበል ሲል ኳስ በቶማስ ስምረቱ በእጅ ቢነካም የእለቱ አልቢትር ዝምታን በመምረጣቸው ኳስን መልሰው ያገኙት ወልቂጤ ከተማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ፍሬው ሰለሞን አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሄኖክ አየለ በተረጋጋ አጨራረስ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል።

በተቀሩት ደቂቃዎች ወልቂጤዎች ኳሱን በመያዝ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ አዳማዎች በቀጥተኛ አጨዋወት የአቻነቷን ጎል ፍለጋ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በተለይም በ74ኛው ደቂቃ ጀማል ጣሰው ከሳጥን ውጭ ኳስ ለማቀበል ሲል ፍሰሀ ቶማስ በፍጥነት ደርሶ ነጥቆት ወደ ግብ ሞክሮ ዳግም ንጉሤ ያወጣበት ኳስ እንዲሁም በ89ኛው ደቂቃ ጀሚል ያዕቆብ ከሳጥን ውስጥ ያመከነው አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማዎች በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች አህመድ ሁሴን እና በሄኖክ አየለ እጅግ አስቆጭ ሙከራዎችን ቢያደርጉም አስደናቂ ብቃቱን ያሳየው ዳንኤል ተሾመ የሚቀመስ አልሆነም። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በወልቂጤ አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ