ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በሁለተኛዋ አስተናጋጅ ከተማ ጅማ የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የተመለከትናቸው ተጫዋች ነክ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።


👉 ሲዳማ ቡናን ያነቃው ማማዱ ሲዲቤ

በ2002 ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከተቀላቀለ ወዲህ እጅግ ደካማ የሚባለውን የውድድር ዘመን ጅማሮ እያደረገ የነበረው ሲዳማ ቡና በዚህ የጨዋታ ሳምንት ግን በፍፁም መነቃቃት ድሬዳዋ ከተማን ከመመራት ተነስቶ 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በጨዋታው ቡድኑ ላሳየው መነቃቃት በወረቀት ጉዳዮች ቡድኑን እስካሁን መገልገል ሳይችል ቀርቶ የነበረው ግዙፉ የማሊያዊ አጥቂ ማማዱ ሲዲቤ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መመለስ እጅግ ከፍተኛ ነበር።

ሲዲቢ በጨዋታው ሁለት ግሩም ግቦችን አንዱን ከቅጣት ምት እንዲሁን ቀሪዋን ደግሞ በግል ጥረቱ የድሬዳዋ ተከላካዮችን አልፎ ሲያስቆጥር ሀብታሙ ገዛኸኝ ላስቆጠራት ጎል ጣጣውን የጨረሰ ኳስ በማቀበል እጅግ ውጤታማ ቀንን አሰልፏል።

በግቦቹ ላይ ከነበረው አበርክቶ ባለፈ በላይኛው የሜዳ ክፍል ኳሶችን እየያዘ የቡድኑ ተጫዋቾችን ወደ እንቅስቃሴ ለማስገባት የሚጥርበት መንገድ እንዲሁም በቀደሙት ጨዋታዎች ከተፈጥሯዊው የመስመር አጥቂነት ሚና ተሸጋሽጎ በፊት አጥቂነት በመጫወቱ መነሻነት ተፅዕኖው ተዳክሞ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝን በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴን ለማድረጉ የማማዱ ሲዲቤ መመለስ አይነተኛ ሚና ነበረው።

በቅርብ ዓመታት ከተመለከትናቸው የውጭ ሀገር ዜግነት ካላቸው አጥቂዎች የተሻለ እንደሆነ የሚነገርለት ማማዱ ሲዲቤ ቡድኑ አጥቶት የነበረውን የፊት መስመር ስልነትን ዳግም ያጎናፀፈ ይመስላል። ምንም እንኳ ከአንደኛው ሳምንት በኋላ ገና የመጀመሪያው ጨዋታ ቢሆንም የድሬዳዋው ጨዋታ ቡድኑ ምን ያህል ተጫዋቹን አጥቶት እንደነበረው ማሳያ ነው።


👉ሌላኛው ዱላ ሙላቱ – ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ

ተስፈኛው የፋሲል ከነማ ታዳጊ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከተቀያሪ ወንበር በመነሳት የጨዋታዎችን ውጤት መቀየሩን ቀጥሎበታል። ተቀይሮ በገባባቸው ሦስት ጨዋታዎችም ፋሲል ሰባት ነጥብ እንዲያሳካ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

በዚህ የጨዋታ ሳምንት በሁለተኛው አጋማሽ ሳሙኤል ዮሐንስን ቀይሮ የገባው ናትናኤል ሙጂብ ቃሲም ላስቆጠራት ወሳኝ የማሸነፊያ ግብ ኳሷን አመቻችቶ በማቀበል ወሳኝ ሚናን ተውጥቷል። ከዚህ ቀደምም ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ሲለያዩ ሱራፌል ዳኛቸውን ተክቶ በመግባት ሁለት አቻ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ሲችል ተፈትነው ባሸነፉበት የወላይታ ድቻው ጨዋታም ሙጂብ ላስቆጠራት የመጨረሻዋ የፍፁም ቅጣት ምት መገኘት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።


👉የወንድማገኝ ኃይሉ ፈጣን ዕድገት

ለወትሮም ቢሆን ወጣቶችን ከእድሜ እርከን ቡድኖች በማሳደግ የማይታማው ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ ደግሞ በመጪዎቹ ዓመታት በቡድኑ የመሐል ሜዳ ላይ መንገስ የሚያስችል አቅም ባለቤት የሆነው ተስፈኛ ወንድማገኝ ኃይሉን እያስመለከተን ይገኛል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወደ ዋናው ቡድኑ ያደገው ወጣቱ አማካይ ከወዲሁ እያሳየ የሚገኘው እንቅስቃሴ የበርካቶችን ትኩረት የሳበ ነው። ሀዋሳ ከተማ በቅርብ ጨዋታዎች ላይ ላሳየው ማንሰራራት የወንድማገኝ ኃይሉ ሚና ከፍተኛ ነው ቢባልም ማጋነን አይሆንም።

ወንድማገኝ ከወዲሁ የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ተመራጭ የመሐል ሜዳ ተጫዋች መሆን የቻለ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሀገራችን አማካዮች ያልታደሉትን ታታሪነትን ከላቀ የቴክኒክ ችሎታ ጋር አጣምሮ የያዘ ሲሆን ከእድሜው በማይጠበቅ ደረጃ ኃላፊነት ለመውሰድ ያለው ዝግጁነትም አስገራሚ ነው።

ተስፋ ሰጪ ወጣቶችን ቢያሳይም በርካቶቹ ከማበብ ይልቅ ሲከስሙ በሚስተዋሉበት የሀዋሳ ከተማ ቡድን ውስጥ ይህ ተጫዋቾች ይበልጥ እየጎለበተ እንዲሄድ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን ጨምሮ በዙርያው የሚገኙ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችም ሆነ ሌሎች አካላት በሙሉ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።


👉 የኤፍሬም አሻሞ እና ሮባ ወርቁ የደስታ አገላለፅ

በ7ኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተደረጉ ስድስት ላይ ከተቆጠሩ ግቦች በኃላ ከተስተዋሉ የደስታ አገላለፆች መካከል የኤፍሬም አሻሞ እና ሮባ ወርቁ ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ የተለዩ ነበሩ።

ጅማ አባጅፋር በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 በተረታበት ጨዋታ ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከሳጥን ውጭ ያገኘውን ኳስ የጅማው የመስመር አጥቂ ሮባ ወርቁ በአስደናቂ መልኩ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችን ግብ አክርሮ በመምታት ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኃላም ተጫዋቹ ደስታውን እንደ ቦክሰኛ እጆቹን እያፈራረቀ ቡጢዎችን በመሰንዘር የገለፀበት መንገድ የተለየ ነበር።

በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማ ባህርዳር ከተማን 2-1 በረታበት ጨዋታ ለሀዋሳ ከተማ የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረው ኤፍሬም አሻሞ አስደናቂዋን የረጅም ርቀት ግብ ካስቆጠረ በኃላ እየሮጠ በመሄድ የመጫወቻ ኳስን ከመለያው ውስጥ በመክተት ለነፍሰ ጡሯ ባለቤቷ መታሰቢያ የሚሆን የደስታ አገላለፅን አስመልክቶናል።


👉እውነተኛው መሪ – ጌታነህ ከበደ

በ3ኛው የጨዋታ ሳምንት ከጉዳት መልስ ቡድኑን ከተቀላቀለ ወዲህ ጌታነህ ከበደ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል። በዚህኛውም ሳምንት ቡድኑ ጅማ አባጅፋርን ሲረታም ሐት-ትሪክ መስራት የቻለ ሲሆን በድምሩም በሊጉ እስካሁን ሰባት ግቦችን በማስቆጠር በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

ዘንድሮ ጌታነህ ከበደ ሐት-ትሪክ መስራቱም ሆነ ግቦችን ማስቆጠር መቀጠሉ ለዓመታት ካሳየን ምርጥ አጥቂነቱ አንፃር አስገራሚ አይደለም። ይልቁንም ቡድኑን በመምራት እና በማነሳሳት ረገድ እየተወጣ የሚገኘው ሚና በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። ተጫዋቹ ቡድኑ በሚያጠቃበት ወቅት ተጫዋቾች ወደ ማጥቃት ዞኑ እንዲቀርቡ የሚጋብዝበት መንገድ እንዲሁም በጨዋታ መሐል ትኩረት ሲያጡ የሚያነሳሳበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ነው።

ከደጉ ደበበ እና አዳነ ግርማ ቡድኑን መልቀቅ በኃላ ቡድኑ አጥቶት የነበረውን እውነተኛ አምበልነትን በጌታነህ ከበደ እያገኘ ይመስላል።


👉ትዕግስቱን ፍሬ ያጣጣመው ዳንኤል ተሾመ

በ2010 የውድድር ዘመን አዲስ አበባ ከተማ ለቆ ወደ አዳማ ከተማ ካመራ ወዲህ በሦስተኛ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂነት አመዛኙን ጊዜ አሳልፏል። ዘንድሮ ግን ለእሱ የተለየ የውድድር ዘመን ይመስላል። ከታሪክ ጌትነት እና ኢብሳ አበበ ጋር ለመጀመሪያ ተመራጭ ግብ ጠባቂነት ፉክክር እያደረገ የሚገኘው ዳንኤል ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ያገኘውን የመሰለፍ እድል በአግባቡ እየተጠቀመ ይገኛል። ለዓመታት ተጠባባቂ ወንበር ላይ የሚያሳልፉ ግብ ጠባቂዎች ዕድሉን ሲያገኙ ጥሩ አቋም ለማሳየት መቸገራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም ዳንኤል ላይ የሚታየው ብቃት ግን ከሳምንት ሳምንት ጨዋታ ሲያደርግ የኖረ አስመስሎታል።

ቡድኑ በወልቂጤ ከተማ 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ዳንኤል ሰባት አደገኛ የግብ ሙከራዎችን በአስደናቂ ብቃት አዳነ እንጂ ቡድኑ አሰቃቂ ሽንፈት ባስተናገደ ነበር። ለዓመታት ይህን ጊዜ በትዕግስት የጠበቀው ዳንኤል አሁን ላይ ያገኘውን ይህን ዕድል በቀላሉ አሳልፉ የሚሰጥ አይመስልም።


👉ሲያሟሙቁ የሚዘንጡት ተጫዋቾች…

ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች ለማሟሟቅ ወደ ሜዳ በወጡበት ወቅት ያልተለመዱ ሁለት ክስተቶችን ለመታዘብ ችለናል።

በዚህም የሲዳማ ቡናው ተጠባባቂ ግብጠባቂ ፍቅሩ ወዴሳ ለማሟሟቅ በወጣበት ወቅት አንገቱ ላይ ረጅም ሰንሰለት የሚመስል የአንገት ጌጥ አድርጎ ልምምዱን የሰራ ሲሆን በተመሳሳይ የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ ጁንያስ ናንጄቦም እንዲሁ ለፀሐዩ ይሁን ሹሩባ የተሰራውን ፀጉር ለመሸፈን ባይታወቅም ቀይ ሻሽ ለብሶ ልምምድ ሲሰራ ተስተውሏል። ይህም በየትኛውም ዓአለም በእግርኳስ ሜዳዎች ላይ ያልተለመደ እንግዳ የሳምንቱ ክስተት ነበር።


👉አነጋጋሪው ቤካም አብደላ

በዚህ ሳምንት ወጣት ተጫዋቾች ያሳዩት ብቃት ከሌላው ጊዜ በተለየ ትኩረት የሚስብ ነበር። የጅማ አባ ጅፋሩ ቤካም አብደላም የሳምንቱ መነጋገርያ ከሆኑ ወጣቶች አንዱ ነው።

ቡድኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ በተሸነፈበት ጨዋታ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተቀይሮ በመግባት ጨዋታ ያደረገው ቤካም ወጣት ከመሆኑ አንፃር የነበረው የመጫወት ፍላጎት ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ቡድኑ የማጥቃት ጉልበት እንዲያገኝ ከማድረግ ባሻገር ጊዮርጊስን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና ውስጥ የከተተች ግሩም ጎል አስቆጥሯል። በሳጥን ውስጥ ራሱን ነፃ አድርጎ ከወንድማገኝ የተቀበለውን ኳስ አስቻለው ታመነ እና ግብ ጠባቂው ለዓለምን አልፎ ያስቆጠረበት መንገድ የበርካቶችን አድናቆት አስገኝቶለታል።

ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ የተገኘውና በመጠርያ ስሙ የተለየው ቤካም በአጀማመሩ ከቀጠለ ብዙ ጥያቄ የሚነሳባቸው አካዳሚዎቻችንን ስም በበጎ የሚያስጠራ እንደሚሆን ይጠበቃል።


👉ሳላዲን ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሷል

ከሚሌኒየሙ ወዲህ ከታዩ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ሳላዲን ሰዒድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባተኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን በረታበት ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ተቀይሮ ገብቶ መጫወት ችሏል። ይህም በተቋረጠው የውድድር ዘመን 17ኛ ሳምንት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሜዳ የገባበት ጨዋታ ሆኗል። በወቅቱ (መጋቢት 2012) ሳላ ከዳኛ ጋር በገባው ሰጣ ገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶ የነበረ ሲሆን በቅርቡ ከጉዳት አገግሞ በተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጥ ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል። በዚህ ሳምንት ደግሞ ተቀይሮ በመግባት መጫወት ችሏል።

የሳላዲን መመለስ በስብስቡ በርካታ አጥቂዎችን ለያዘው ቡድኑ ተጨማሪ አማራጭ እንደሚፈጥር ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ