ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

በሰባተኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የተመዘገቡ ቁጥራዊ መረጃዎች አና ዕውነታዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

– በሰባተኛው ሳምንት በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች 14 ጎሎች ተቆጥረዋል። በአማካይ 2.3 ጎሎች የተመዘገቡበት ይህ ሳምንትም የውድድር ዓመቱ ከተጀመረ ወዲህ ዝቅተኛው የጎል መጠን ሆኖ ተመዝግቧል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና (3) በርካታ ጎሎችን ያስቆጠሩ ቡድኖች ሲሆኑ ድቻ፣ ሰበታ፣ ሆሳዕና እና አዳማ ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች ናቸው።

– ከተቆጠሩት 14 ጎሎች መካከል አንድ በፍፁም ቅጣት ምት (ጌታነህ) እና አንድ በቅጣት ምት (ሲዲቤ) እንዲሁም አንድ ከማዕዘን ከተሻማ (ጌታነህ) ጎሎች ውጪ ሌሎቹ 11 ጎሎች የተቆጠሩት በክፍት ጨዋታ ነው።

– ከአስራ አራቱ ጎሎች መካከል ሦስት ጎሎች የተቆጠሩት ከሳጥን ውጪ ተመትተው ሲሆን ሌሎቹ 11 ጎሎች ከሳጥን ውስጥ የተገኙ ናቸው።

– 11 ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ጌታነህ በሦስት ቀዳሚ ሲሆን ሲዲቤ ሁለት አስቆጥሯል። ሌሎቹ ዘጠኝ ተጫዋቾች አንድ አንድ አስቆጥረዋል።

– በዚህ ሳምንት ጎል ካስቆጠሩት መካከል ቤካም አብደላ በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ባደረገው ጨዋታ ያስቆጠረው ነው።

– ከጎል አስቆጣሪዎች ጋር በተያያዘ ሀብታሙ ገዛኸኝ፣ ማማዱ ሲዲቤ፣ ቤካም አብደላ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና ሳለአምላክ ተገኝ የመጀመርያ የውድድር ዓመት ጎላቸውን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

– ዘጠኝ ተጫዋቾች ለጎሎች በማመቻቸት ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋል ከነዚህ መካከል አቤል ያለው የውድድር ዘመኑን ስድስተኛ አሲስት ማስመዝገብ ችሏል።

– ጎል በማስቆጠር እና በማመቻቸት የሳምንቱ ብቸኛ ተጫዋች ማማዱ ሲዲቤ ነው። ማሊያዊው የሲዳማ ቡና አጥቂ ሁለት አስቆጥሮ አንድ አመቻችቷል።

– ሙጂብ ቃሲም፣ ሮባ ወርቁ፣ መስፍን ታፈሰ እና ሄኖክ አየለ በተከታታይ ጨዋታ ጎል አስቆጥረዋል።

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በሰባተኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች 21 የማስጠንቀቂያ ካርዶች የተመዘዙ ሲሆን የቀይ ካርድ በዚህ ሳምንት ላይ አልተመዘዘም።

– የባህር ዳር እና ሀዋሳ ጨዋታ ስድስት ካርዶች ተመዘውበት የሳምንቱን ከፍተኛ ቁጥር ሲያስተናግድ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ምንም የማስጠንቀቂያ ካርድ ያልተመለከቱ ቡድኖች ናቸው።

– ተስፋዬ አለባቸው የዓመቱን አራተኛ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል። ይህም ከሀብታሙ ሸዋለም እና ሱራፌል ዳኛቸው ጋር ከፍተኛው ቁጥር ነው።

– ሱራፌል ዳኛቸው በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ የማስጠንቀቂያ ካርድ ከተመለከተ በኋላ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሳይመለከት ወጥቷል።

ዕውነታዎች

– ሙጂብ ቃሲም በተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ላይ ጎል አስቆጥሯል። የፋሲል ከነማው አጥቂ ሆሳዕና፣ ሲዳማ ቡና፣ ባህር ዳር፣ ወላይታ ድቻ እና ጅማ አባ ጅፋር ላይ ማስቆጠር ችሏል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን ባደረጋቸው ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሙሉ ጎል አስተናግዷል። እርካሁን ያስተናገደው የጎል መጠን (10) በተሰረዘው የውድድር ዓመት በ17 ጨዋታ ከተቆጠረበት (13) ጋር ሊስተካከል ሦስት ጎሎች ብቻ ቀርቶታል።

– በዘጠኝ ጎሎች የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየመራ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲም ከ7 የሊጉ ቡድኖች የበለጠ ጎሎች ለብቻው አስቆጥሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ