ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

መቀመጫቸውን በሀዋሳ ያደረጉትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ሮድዋ ደርቢ ተብሎ የሚጠራው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ነገ በቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስደረግ በድኖቹ ከሚገኙበት ወቅታዊ አቋም አንፃር ተጠባቂነቱ ከፍ ብሏል። ከደካማ አቋማቸው መነቃቃት አሳይተው የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት ጨዋታ እንደሚያስመለክቱ ከወዲሁ ዕምነት ተጥሏል።

አስጊ የነበረው የውድድር ዓመት አጀማመሩን እያስተካከል የመጣው ሀዋሳ ከተማ ከሽንፈት ከራቀ አራት ጨዋታዎች አልፈውታል። በተለይም በተከታታይ ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማን አሸንፎ ለዚህ ጨዋታ መድረሱ የቡድኑን በራስ መተማመን ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ በመከላከልም ሆነ በማጥቃት የነበሩበትን ችግሮች ወደ 3-5-2 ከመጣ በኋላ ማስተካከል ሲችል በመሀል ወደ 4-3-3 በተመለሰበት የባህር ዳሩ ጨዋታም ውጤት ይዞ መውጣት ችሏል። ከቡድን እንቅስቃሴው ባለፈ በግለሰብ ደረጃም የሚታይ ዓይነት ለውጥ የተስተዋለባቸው የሀዋሳ ተጫዋቾች በነገው ጨዋታም እንቅስቃሴያቸው ተጠባቂ ሆኗል።

በሁለቱም አደራደሮች የግቦች መነሻ እየሆነ የመጣው የግራ መስመር ተከላካዩ ደስታ ዮሀንስ ነገም የሲዳማን የመስመር ጥቃት በመቋቋምም ሆነ አደገኛ ተሻጋሪ ኳሶቹን ለነመስፍን ታፈሰ በማድረሱ በኩል የሚኖረው ሚና ትኩረትን የሚስብ ነው። ተስፈኛው አማካይ ወንድምአገኝ ኃይሉ የወትሮው ታታሩነቱ ቡድኑ አማካይ ክፍል ላይ በዳዊት ተፈራ ከሚመራው የሲዳማ የመሀል ክፍል የሚገጥመውን ፈተና ለመቋቋም ተስፋ የሚጣልበት ነው። በጥቅሉ ተለዋዋጭ ባህሪ እየታየበት ያለው ሀዋሳ የሚመርጠው የተጨዋቾች አደራደር ይለያይ እንጂ የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ያደረገ በአመዛኙ ከመስመሮች የሚነሱ ጥቃቶችን ምርጫው ያደረገ ዓይነት ቡድን እንደሚሆን የገመታል።

እንደ ሀዋሳ ተከታታይ ድል አያስመዝግብ እንጂ ሲዳማ ቡናም የእስካሁኑ አካሄድ እየተሰተካከለ እንደሆነ የሚያሳይ ድል በድሬዳዋ ከተማ ላይ ማስመዝገብ ችሏል። በተለይም በማጥቃቱ ረገድ የማማዱ ሲዲቤ ወደ ጨዋታ መመለስ ለአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን ዘርፈ ብዙ ጥቅም አስገኝቶለታል። አጥቂው ግብ ከማስቆጠሩ ባለፈ ለሀብታሙ ገዛኸኝ ነፃ መሆን ምክንያት ሆኖ መታየቱ ነገ በቅርብ ጨዋታዎች ጠንካራ ሆኖ ከታየው የሀዋሳ ከተማ የተከላካይ ክፍል ጋር የሚኖረውን ፍልሚያ አጓጊ አድርጎታል። በተቃራኒው አሁንም የተከላካይ ክፍሉ ክፍተቶች እንዳሉበት የድሬው ጨዋታ አሳይቷል። በመሆኑም ሲዳማ የፈቱዲን ጀማልን ሀነኛ ተጣማሪ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ ማግኘት አለመቻሉ ለሀዋሳ ከተማ ተሻጋሪ ኳሶች ምላሽ መስጠት እንዳያዳግተው ያሰጋዋል።

የሲዳማ ሌላው መሻሻል የታየበት አማካይ ክፍሉ ነው። የብርሀኑ አሻሞ ፣ ዳዊት ተፈራ እና ያስር ሙገርዋ መልካም ጥምረት ያጠናከረው አማካይ ክፍሉ በነገው ጨዋታ በማጥቃቱ ረገድ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ አቋም ካሳየው ዳዊት ታደሰ እና ከኋላው ከሚገኙት ሦስት ተከላካዮች ጋር ከባድ ትንቅንቅ ይጠብቀዋል። ሲዳማዎች በፍጥነት ማጥቃትን አስጀምረው በተጋጣሚ ሜዳ ላይ የመገኘት ብቃታቸው ዳግም ተገልጦ እንዲታይ ምክንያት የሆኑት እነዚህ ተጫዋቾች ነገም የሀዋሳን የኋላ ክፍል በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች በመፈተን ተፅዕኗቸው ቋሚ ይሆን እንደሆነ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳርን ሲገጥም ጉዳት ያስተናገደው ኤፍሬም ዘካርያስ የመሰለፍ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን የረጅምበ ጊዜ ጉዳት ያለበት ሀብታሙ መኮንን ለነገውም ጨዋታ አይደርስም። በተመሳሳይ የሲዳማ ቡናዎቹ አጥቁዎች አዲሱ አቱላ እና ይገዙ ቦጋለም እንደማይደርሱ ሰምተናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 20 ጊዜ ተገናኝዋል። ሲዳማ ቡና 7 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሀዋሳ 5 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– በአጠቃላይ 20 ግንኙነቶቻቸው 42 ጎሎች ሲቆጠሩ ሲዳማ 23 ፣ ሀዋሳ 19 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ወንድምአገኝ ማዕረግ – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – ኤፍሬም ዘካርያስ – ዳዊት ታደሰ – ወንድምአገኝ ኃይሉ –ደስታ ዮሐንስ

ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ሙቱኩ – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – ያስር ሙገርዋ

ተመስገን በጅሮንድ – ማማዱ ሲዲቤ – ሀብታሙ ገዛኸኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ