የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ነገ ይጀምራል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድሮች ከነገ ጀምሮ በአዳማ እና በሀዋሳ ከተሞች ይቀጥላሉ፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ እና የሁለተኛ ዲቪዚዮን ሻምፒዮና ውድድር ከነገ የካቲት 6 ጀምሮ በይፋ በሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ይጀምራል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ከታህሳስ 11 እስከ ጥር 21 ሲደረግ የሰነበተው የፕሪምየር ሊጉ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ከአስራ አምስት ቀናት ዕረፍት በኋላ ነገ በአዳማ የሁለተኛውን ዙር ውድድር በአስር ክለቦች መካከል መካሄድ ይጀምራል፡፡ በተመሳሳይ አስር ቡድኖችን የሚያሳትፈው የሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድር ከአዳማ የተረከበችው ሀዋሳ የፊታችን ዕሁድ የካቲት 7 ውድድሯን ማስተናገድ ትጀምራለች፡፡

በተያያዘ መረጃ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር የአንደኛው ዙር ግምገማ ይደረግ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ግን ይህ አለመኖሩ ክለቦችን አስቆጥቷል፡፡ በዋናነት ክለቦች በቅሬታ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የኮቪድ 19 ጥንቃቄ ጉድለት መታየቱ እንዲሁም ‘በተደጋጋሚ በዳኞች በደል እየደረሰብን በዚህ ግምገማ ላይ ድምፃችንን ለማሰማት በተዘጋጀንበት ወቅት አለመዘጋጀቱ ረብሾናል’ በማለት የገለፁ ሲሆን በክፍተቶቻቸው ላይ ሳይነጋገሩ ወደ ውድድር በቀጥታ መግባታቸው ቅር እንዳሰኛቸውም አስረድተዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ከሁለቱም ዲቪዚዮን አመራሮች ባገኘችው መረጃ መሠረት ግምገማው ያልተደረገው በጊዜ እጥረት መሆኑን ለማወቅ ችላለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ