በሊጉ እየደመቁ የሚገኙት ትንታጎቹ አጥቂዎች – መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ

አዳዲስ ትውልዶችን ለማፍፋት የማይነጥፍ ፀጋ ባለት ሀዋሳ ሁለቱም ተወልደው አድገዋል። መስፍን ታፈሰ ከፕሮጀክት በጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ ከሀዋሳ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ተጫውቶ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ሲችል ከወራት በፊት ወደ ኢኳቶርያል ጊኒው ፉትሮ ኪንግስ ለሙከራ አምርቶ ተመልሷል። ዓምና አምስት ጎል ማስቆጠር የቻለው መስፍን ዘንድሮ አራት ጨዋታ ብቻ አድርጎ አምስት ጎሎችን አስቆጥሯል። በአንፃሩ ብሩክ በየነ በወቅቱ ከፍተኛ ሊግ ወደሚወዳደረው ወልቂጤ ካመራ በኃላ በ2011 መስከረም ወር ወደ ሀዋሳ ተመልሶ ፊርማውን ካኖረበት ጊዜ አንስቶ ሁለት ድንቅ ዓመታትን አሳልፏል። በተለይ ዓምና በተሰረዘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዘጠኝ ጎሎች ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሲፎካካር ቆይቷል።

በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እስካሁን በተደረገ የስምንት ሳምንት ጨዋታዎች ሀዋሳ ከነማ ካስቆጠራቸው 12 ጎሎች መካከል ሁለቱ ወጣት አጥቂዎች 9 ጎሎች በማስቆጠር የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆናቸውን እያረጋገጡ መጥተዋል። ይህ ጥምረት በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ወደፊት ሁለቱንም በትልቅ ደረጃ መመልከታችን የማይቀር ይመስላል።

ሁለቱም የመሐል አጥቂ ቢሆኑም የተለያየ የአጨዋወት ባህርይ ያላቸው መሆኑ ለተከላካዮች ቁጥጥር ፈታኝ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። መስፍን በተክለሰውነቱ ግዙፍ እና ጠንካራ ሲሆን ተሻጋሪ እና ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን የሚጠቀምበት መንገድ አስገራሚ ነው። ብሩክ ደግሞ በሰውነቱ አነስ ብሎ የቴክኒክ ችሎታ እና ታታሪነትን አጣምሮ የያዘ ተጫዋች ነው። በዚህም ሳጥን ውስጥ ያሻውን ለማድረግ እንደማይቸገር በተደጋጋሚ አሳይቷል።

በዛሬው ዕለት ሀዋሳ ሲዳማን በደርቢ ጨዋታ ሲያሸንፍ ሁለቱን ጎሎች በማስቆጠር ልዩነት ፈጣሪ መሆናቸውን ያሳዩት አጥቂዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎች አንስተንላቸው ለድረገፃችን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።

መስፍን ታፈሰ

ከኢኳቶርያል ጊኒው የሙከራ ቆይታ መልስ ያንተ አቋም እንዴት ይገለፃል ?

በጣም ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው። በየጨዋታዎቹ ጎል ለማስቆጠር እየሞከርኩ ነው። እስካሁን ባለው ነገር ደስተኛ ብሆንም ከዚህ በኋላ በተለየ ሁኔታ ከእኛ ብዙ ይጠበቃል። በግሌም እንደ ቡድንም የምችለውን አደርጋለው።

ከውጭ ለሙከራ ሄደህ መመለስህ የጠቀመህ ነገር አለ ?

አዎ ብዙም ባይሆን የጠቀመኝ ነገር አለው። የውጭ ሀገር እና የኛ ሀገር እግርኳስ ልዩነትን ማወቅ ችያለሁ። እዛ ቆይቼ ከመጣው በኃላ እዚህ ቀሎኛል። ያም ቢሆን ኳስ ነው መሥራት ይጠበቅብኛል።

ከፊት መስመር ተጣማሪህ ብሩክ በየነ የምታደንቅለት ምንድነው ?

የኳስ እውቀቱ ከፍ ያለ ጥሩ ተጫዋች ነው። ጎል ያገባል። ከሜዳ ውጭ ሜዳ ላይም ባህሪው ደስ ይላል። ሁሉ ነገሩ ደስ የሚል ተጫዋች ነው።

እንደናንተ ሁሉ ሌሎች ወጣቶች ዕድል እንዲያገኙ ምን መልዕክት አለህ ?

በመጀመርያ በወጣት ተጫዋቾች ማመን ያስልጋልል። እምነት መጣል እድል መስጠት ያስፈልጋል። ክለቦች ለወጣቶች ዕድል በመስጠት መድፈር አለባቸው።

ከኢትዮጵያ ውጭ የመጫወት ዕድል በቀጣይ እንጠብቅ ?

አዎ ግድ ነው። ዕድሎች ይኖራሉ ከኢትዮጵያ ውጭ ያለውን የእግርኳስ ደረጃ በተወሰነ መልኩ አይቻለው። እኔም በግሌ ያለኝን አቅም ተረድቻለው። መስራት የሚገባኝ ነገርም እንዳለ የወሰድኩት ነገር አለ። ክፍተቶቼን ሞላልቼ እንደ ፈጣሪ ፍቃድ ከኢትዮጵያ ውጭ መጫወት አስባለው።

ብሩክ በየነ

ወቅታዊ አቋምህ እንዴት ይገለፃል ?

አሁን ያለሁበት አቋም ጥሩ ነው። ዛሬም አራተኛ ጎሌን አስቆጥሬለሁ። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከዚህ በኃላ ከእኛ ብዙ ነገር ይጠበቅብናል። ያንንም እንደምናደርግ እርግጠኞች ነን።

ጎል አግብታቹ ደስታቹሁን የምትገልፁበት መንገድ እንዴት ነው ?

(እየሳቀ …) ደስታችንን ለመግለፅ ነው። በልምምድ ወቅትም በተመሳሳይ መንገድ ጎል አስቆጥረን በዚህ መልኩ ነው ደስታችንን የምንገልፀው። ተነጋግረን ያደረግነው ባይሆንም ግን የራሳችን የሆነ የዳንስ ስታይል በውድድሩ ላይ ለመፍጠር እየሞከርን ነው።

ከመስፍን የምታደንቅለት ምንድነው ?

መስፍን በጣም የሚተጋ ታታሪ ተጫዋች ነው። ሁሌም ራሱን ጥሩ ደረጃ ለማድረስ የሚፈልግ ሰው ነው። ጎል የሚያገባበት መንገድ ፍጥነቱን አደንቅለታለው።

ከዚህ በኃላ ምን እንጠብቅ?

አሁን ያለንበት ደረጃ ጥሩ ሁኔታ ነው። ከዚህ በኃላ ጥሩ ነገር ለመስራት እንሞክራለን። መጀመርያ የተሰጠን ግምት ዝቅተኛ ነበር። መጀመርያም ነገሬያችሁ ነበር፤ ቡድናችን አየተስተካከለ እንደሚመጣ። ከዚህ በኃላም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን እንመጣለን።

በሀዋሳ ያለውን ጥምረት በብሔራዊ ቡድን እንጠብቅ?

አዎ! ከፈጣሪ ጋር። በሀዋሳ ያገኘነውን የመጫወት ዕድል እና ጥምረት በብሔራዊ ቡድን አብረን በመጫወት ማሳየትን እናስባለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ