የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-0 ሰበታ ከተማ

ከሲዳማ እና ሰበታ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ይህንም ብለዋል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ከጫና ስለመውጣት

መጀመርያም ጫና ውስጥ አይደለሁም። ግን ጫና ውስጥ የከተተኝ ውጤት ማጣቴ ነው። ስለዚህ ውጤቱን በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል። ተጫዋቾቼ በተጋድሎ ባመጡት ውጤት በጣም ኮርቻለሁ።

ጎሎች ካስቆጠሩ በኋላ ጥንቃቄ ስለመምረጣቸው

ነጥቡ በጣም ያስፈልገን ስለነበር ጎሉን ካስቆጥርን በኋላ አፈገፈግን። ውጤት እያስመዘገብን መጥተን ቢሆን ኖሮ ይህን አንመርጥም ነበር። ካፈገፈግን በኋላ ተጋጣሚያችን በተደጋጋሚ ወደ ጎል ደርሰው ስህተቶቻችን ለመጠቀም ጥረት አድርገው ነበር። ዕድለኞች ነበርን ማለት ይቻላል። ምክንያቱም አቻ የመሆን እድሉ ነበራቸው። ፍፁም ቅጣት ምት አምክነዋል።

ስለ ስሜታዊ እንቅስቃሴዎቹ

አንዳንድ ተጫዋቾቼ የሰጠኋቸውን ታክቲክ ሲተገብሩ አልነበረም። በተለይ ተቀይሮ የገባው እሱባለው በተደጋጋሚ ቦታውን ሲለቅ ነበር፣ የአቋቋም ችግር ነበር፣ ኳስ ለማስጣል የሚያርገው ጥረት ደካማ ስለነበር እሱ ላይ በተደጋጋሚ ስጮህ ነበር። በተጨማሪ ተከላካዮቼ እሱ ኳሱን ካገኙት በኋላ ነበር ሲደርሱ የነበረው። በዛ ነው እየተነሳሁ መልዕክት ሳስተላልፍ የነበረው።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለፍፁም ቅጣት ምቱ መሳት

አንድ ለዜሮ እየተመራን ስለነበር ለኛ መነሻ ይሆን ነበር ማለት እችላለሁ። ፍፁም የቡድናችን የመጀመርያ መቺ ስለሆነ መምታት ነበረበት። እግርኳስ ነው፤ ይሳታል። ግን ከተሳተ በኋላም በሁኔታው ተጫዋቾቼ ሳይወርዱ ብዙ የጎል ሙከራ አድርገዋል። ማግባት አለመቻላችን ፍፁም ቅጣት ምቱን ካለመጠቀማችን ጋር ዋጋ አስከፍሎናል። በአንፃሩ የገባብን በጥንቃቄ ስህተት ነው። ሲዳማም ካገቡት ጎል በስተቀር እኛ ላይ የሞከሩት ሙከራ አልነበረም። ስለዚህ አንዳንዴ በኳሱ በልጠህ ወይም በሙከራ ተሽለህ ተሸንፈህ ትወጣለህ። ይህ የእግርኳሱ ባህርይ ነው። ሲዳማን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።

ተከታታይ የቀይ ካርድ እና የተጫዋቾች ሥነ-ምግባር

የዲሲፕሊን ችግር የለም። ሁለቱም የወጡብን ተጫዋቾች ክለቡ ውሰረጥ ባላቸው ዲሲፕሊን በጣም የተመሰገኑ፣ የልምምድ ሰዓት አክብረው የሚሰሩ ተጫዋቾች ናቸው። ነገር ግን ሜዳ ውስጥ ውጤት ከመፈለግ አንፃር ባለ ጉጉት የሚወስዱት እርምጃ ለጉዳት ዳርጓቸዋል። ይህ እንደ ትምህርት የሚወሰድ ይሆናል።

የሽንፈት መደጋገም ቀጣይ ጨዋታዎች ፈተና

ከሽንፈት እና ጫና ለመውጣት ብርቱ ጥረት እናደርጋለን። መግቢያዬ ላይ እንደተናገርኩት ዛሬ ተጫዋቾቼ ከሽንፈት ለመውጣት የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያርጉ ተናግሬ ነበር። ሜዳ ላይም የተመለከትከው ያንን ነው። ተጋጣሚያችን ላይ ሙሉ ብልጫ ወስደናል። ሙከራዎች አድርገናል። ነገር ግን እግርኳስ አንዳንዴ አይሳካልህም። ጅማ ከመጣን ወዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየን ነው። ዛሬ ደግሞ የተሻለ አቋም ነው ቡድኔ ላይ ያየሁት። ያንን መሻሻል ጠብቀን ሄደን ለቀጣይ ጨዋታ በሚገባ ተዘጋጅተን ካለብን ጫና ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ