“ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ እያለቀስኩ ወጥቻለው” ዳንኤል ኃይሉ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ዛሬ ጀምሮ ሲዳማ ቡና ሰበታ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ሜዳ ላይ አነጋጋሪ ክስተት ካስተናገደው ዳንኤል ኃይሉ ጋር ቆይታ አድርገናል። 

በተደጋጋሚ በዘንድሮ ዓመት ተጫዋቾች ከቀይ ካርድ በሚመለከቱበት ወቅት ከዳኞች ጋር አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ ከመግባት ይልቅ በፀፀት ስሜት እያለቀሱ ከሜዳ መውጣት እየተለመደ መምጣት ለሊጉ ሌላ አዲስ ክስተት እየሆነ መጥቷል። በዛሬው ዕለትም ሁለት ከሽንፈት የመጡ ሲዳማን ከሰበታ ባገናኘው የዛሬው የማለዳ ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ብሎ ቢጀምርም ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተጋግሎ የተለያዩ ድራማዊ ትዕይንቶችን አስመልክቶን በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ከባህር ዳር ከተማ ጋር አስደናቂ የውድድር ዓመት ያሳለፈው አማካይ ዳንኤል ኃይሉ ጥፋት ሰርቶበት የነበረው ያስር ሙገርዋ ላይ በሰነዘረው የአፀፋ እርምጃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። በዚህ ቅፅበት የተደናገጠው ዳንኤል ለደቂቃዎች ያህል ሜዳ ውስጥ ተንበርክኮ በማልቀስ በቡድን አጋሮቹ ተይዞ እያለቀሰ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል። ይህ ስሜቱ ከምን የመነጨ እንደሆነ ለማወቅ አግኝተን አናግረነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

” አጋጣሚ እንደሚታወቀው ለማሸነፍ ያለን ጉጉት እና ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ ዛሬ ከፍተኛ ነበር። ሁሌም ለማሸነፍ ያለን ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም ውጤቱ ከዚህ ቀደም አልተሳካም ነበር። ዛሬ ግን ለማሸነፍ ሁላችን ቃል ገብተን ነው ወደ ሜዳ የገባነው። አጋጣሚ ሆኖ ለማሸነፍ የነበረን ፍላጎት ከልክ ያለፈ ሆኖ በተጨማሪም ከኃላ ጥፋት እየሰሩብኝ በተደጋጋሚ ኳሱን ያቋርጡብኝ ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን እነርሱ ኳሱን ይገፉታል። ወደ ውጭ ያወጡታል። ጥፋት ተሰርቶብኝ ኳሱን ቶሎ ልጀምር ስል ኳሱን ሲገፋው እጄን ወደ ልጁ ሰደድኩኝ። እርሱ ግን እንደመታሁት አድርጎ እየጮህ ወደቀ። እኔ በምንም መንገድ ይወድቃል፤ ኃይልዬም ቀይ ካርድ ያሳየኛል ብዬ አላሰብኩም። ቶሎ ለመጀመር ነበር ሀሳቤ። ያው ኃይለየሱስ መጥቶ ቀይ ሲያሳየኝ አላመንኩም።

” በተጫዋችነት ጊዜዬ ቢጫ ካርድ እንኳን አላይም። ለጓደኞቼ አብረውኝ ለሚጫወቱትም ሌሎች በተቃራኒ ለሚጫወቱትም የምመክር ነኝ። ሆን ብዬ የተቃራኒ ተጫዋችን የምጎዳ የተለየ ነገር የማሳይ ተጫዋች አይደለሁም። ፀሎት አድርጌ ነው ወደ ሜዳ የምገባው። አይደለም ቀይ ካርድ ቢጫ እንኳን የማይ አይደለውም። ከዳኞች ጋር ተግባብቼ ከተቃራኒ ተጫዋች ሲጎዳ አይዞህ የምል ሁልግዜም በጎ ነገር የማስብ ነበርኩ። ዛሬ ግን በህይወቴ ያጋጥመኛል ብዬ የማላስበው እኔን የማይገልፅ ነገር በመፈፀሙ እንዲሁም ለማሸነፍ ከነበረን ከፍተኛ ፍላጎት አንፃር ቡድኔን ዋጋ የማስከፍለው ነገር ይኖራል ብዬ በማሰቤ ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ እያለቀስኩ ወጥቻለው።

” ኢተርናሽናል ዳኛ ኃይልዬ በጣም የማከብረው ከሜዳ ውጭ ባለው ህይወቱ የተረጋጋ በአጠቃላይ የማደንቀው የማከብረው ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለበት መልካም ሰው ነው። ሀገራችን ካሉ ጎበዝ የተሻሉ ዳኞች መካከል አንዱ ነው። እርሱ ሜዳ ላይ ይሆናል ብሎ ያሰበውን ማድረግ ያለበትን ውሳኔ ወስኗል። የአንድ አካባቢ ሰዎች በመሆናችን የተለየ ነገር እንዲያደርግልኝ አልጠብቅም። ለሙያው ያለውን ታማኝነት ጥንካሬ ስለማቀው ውሳኔውን ደግሞ አከብራለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ