ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ጌዲኦ ዲላ ተቸግሮም ቢሆን አርባምንጭን አሸንፏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ስምንተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በጌዲኦ ዲላ እና አርባምንጭ መካከል ተደርጎ የእፀገነት ግርማ ብቸኛ ጎል ጌዲኦ ዲላን አሸናፊ አድርጋለች፡፡

ጥሩ ፉክክር በተያበት እና አርባምንጭ ከተማዎች ወደ ጎል በመድረስ ተሽለው በታዩበት ቀዳሚው አርባ አምስት ደቂቃ አርባምንጮች ካለፉት ጨወታዎቻቸው በሚገባ ተምረው የመጡ በሚመስል መልኩ የተንቀሳቀሱ ሲሆን ጌዲኦ ዲላዎች በበኩላቸው ወደ ቀኝ በኩል ባደላ የማጥቂያ አማራጭን ሲጠቀሙ አስተውለናል፡፡ጌዲኦ ዲላዎች ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ጠንካራ የሜዳ ላይ አቅም አንፃር በጨዋታው ቀድመው ግምት ያገኙ የነበረ ቢሆንም በአርባምንጭ ከተማ በሚገባ ተፈትነው ታይተዋል፡፡ 10ኛው ደቂቃ ላይ በጌዲኦ ዲላ ተከላካዮች ፍፁም ዝንጉነት የተገኘችሁን ኳስ ሰርካለም ባሳ አግኝታው ያልተጠቀመችበት ቅፅበት አስቆጪ ዕድል ነበረች፡፡

መንደሪን ክንዲሁን ከቅጣት ምት፣ እፀገነት ግርማ እና ሰላማዊት ጎሳዬ ከርቀት ያደረጉት ሙከራ በአርባምንጯ ግብ ጠባቂ ድንቡሽ ኢባ የተመለሰባቸው ጌዲኦ ዲላዎች ያደረጉት ሙከራዎች ናቸው፡፡ በፍላጎት በሜዳ ላይ ሲጫወቱ ግሩም እንቅስቃሴ የሚይባቸው አርባምንጮች በሰናይት ባሩዳ የመሀል ሜዳ ቅንጅት ወደ ፊት በሚጣሉ ኳሶች አጋጣሚን ለማግኘት የሞከሩበት መንገድ መልካም ሆኖ ቢታይም የአጥቂዎቹ መሠረት ወርቅነህ እና ሰርካለም ባሳ ደካማ የአጨራረስ አቅም ወደ ጎልነት ያገኙትን እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር በተስተናገደበት እና ጌዲኦ ዲላዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበራቸው ደካማ የአጨራረስ ብቃት በተወሰነ መልኩ ተሻሽለው የታዩበት አርባምንጮች በበኩላቸው ወደ ጎል የመድረስ ችግር ባይታይባቸውም በዚህኛው አጋማሽ ኳስን ከመረብ ጋር የሚያገናኝላቸው አጥቂ ያለ መኖሩ ኃላ ላይ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ድርሻዬ መንዛ በረጅሙ ከቅጣት ምት ስታሻጎር ሰርካለም ባሳ በግንባር ገጭታ የግቡ ቋሚ የመለሰባት እና ተቀይራ የገባችሁ መሠረት ማቲዮስ ከክፍት የቅብብል ሂደት የተገኘን አጋጣሚ ከአጨራረስ ድክመት ያመከነችው በአርባምንጮች በኩል የተገኙ ወርቃማ ዕድሎች ነበሩ፡፡

የቀሩት ደቂቃዎች ለመጠቀም የጣሩት ጌዲኦ ዲላዎች ከሰላማዊት ጎሳዬ እፀገነት ግርማ ተደጋጋሚ ሙከራዎች በኃላ ተሳክቶላቸው ጎል አስቆጥረዋል፡፡ 66ኛው ደቂቃ ላይ ይታገሱ ተገኝወርቀ የፈጠረችላትን መልካም አጋጣሚ ተከትሎ እፀገነት ግርማ በግራ እግሯ አክርራ መታ በማስቆጠር ጌዲኦ ዲላን አሸናፊ በማድረግ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ አጋጣሚ ሳንመለከት በጌዲኦ ዲላ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የጌዲኦ ዲላዋን ተከላካይ መንደሪን ክንዲሁንን ምርጥ ብሎ ሸልሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ