የተጫዋቾች ዝውውር የሚጀመርበት እና የሚጠናቀቅበት ቀን ታውቋል

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመኑ አጋማሽ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የሚጀመርበት እና የሚጠናቀቁባቸው ቀናት ታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው የተለመደ አካሄድ የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ እረፍት በመስጠት የተጫዋቾች ዝውውር ይካሄድ እንደነበረ ይታወሳል። ሆኖም ግን በዚህ ዓመት በተለየ ሁኔታ ከ12ኛ እስከ 16ኛ ሳምንት መርሐ ግብር መቋረጥ ሳይኖር የሁለተኛ ዙሩን ሦስት ሳምኝት ጨዋታዎች ጨምሮ ባህር ዳር ላይ እንዲካሄድ ማሻሻያ በማድረጉ ይታወቃል። ሆኖም 13ኛው ሳምንት የዓመቱ አጋማሽ በመሆኑ የተጫዋቾች ዝውውር ክለቦች ማድረግ ስለሚገባቸው አወዳዳሪው አካል የዝውውር መስኮቱን ከየካቲት 19 እስከ መጋቢት 18 ለአንድ ወር እንደሚቆይ ለክለቦች በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።

በዚህም መሠረት ክለቦች ያለባቸውን ክፍት ለመድፈን በስፋት ወደ ዝውውሩ እንደሚገቡ ሲጠበቅ የዛኑ ያህል የተለያዩ ተጫዋቾችን ያሰናብታሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ